የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

… የውኃ በዓል

13- የሰላም ውኃ ፡-
 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚሞት በተናገረ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ልባቸው ታወከ ። ፍጹም ወደውታልና ፍጹም ተስፋ አድርገውታልና ሁሉም ነገር ጨለማ ሆነባቸው ። መሞቱ ብቻ ሳይሆን መሄዱም ተጨማሪ ስቃይ ሆነባቸው ። እርሱ ግን መንፈስ ቅዱስን እንደሚልክላቸው በመንገር አጽናናቸው ። መጽናናት ከኪሣራው እኩል ወይም የሚበልጥ ካሣ በማግኘት ማረፍ ነው ። የሚሄደውን ጌታ በሙሉነት በመተካት ሊያጽናናቸው የሚችለው መንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው ። ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ ከወልድ ጋር እኩል ነውና ። ጌታችን ሌላም ተስፋ ሰጣቸው ፡- ሰላሜን እሰጣችኋለሁ ሰላሜን እተውላችኋለሁ በማለት አረጋጋቸው /ዮሐ. 14፥26/ ። ሰላም የእርሱ መለኮታዊ ገንዘብ ናት ። የሰላም አድራሻዋ ከሰማይ ነው ። በዓለም ላይ ያለው ሰላም የሚመስል እንጂ እውነተኛ ሰላም አይደለም ። የውስጡን ጩኸት ላለመስማት በውጫዊ ጩኸት ውስጥ መደበቅ ነው ። ማደንዘዣ መፈወሻ አይደለም ። ማደንዘዣ ሲለምድ የማደንዘዝ አቅሙን እያጣ ይመጣልና ተጠቃሚው መሰቃየት ይጀምራል ። የእግዚአብሔር ሰላም እንደ ወንዝ ነው ። በነቢዩ በኢሳይያስ ፡- “ትእዛዜን ብትሰማ ኖሮ፥ ሰላምህ እንደ ወንዝ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር” ይላል /ኢሳ. 48፥18/ ። ወንዝ የማያቋርጥ ነው ፥ የእግዚአብሔርም ሰላም ለዘወትር ነው ። ወንዝ ግዛት አልፎ ያረካል ፥ የእግዚአብሔርም ሰላም ለሌሎች ይተርፋል ። ወንዝ ሳይሰስት ይፈስሳል ፥ የእግዚአብሔርም ሰላም በነጻ ለሁሉ ይናኛል ። ወንጌላዊው ስለዚህ የሰላም ወንዝ ይናገራል ። የሰላም መሠረቱ በእግዚአብሔር ማመን ነው ።
14- የፍሬ ውኃ ፡-
 እውነተኛው የወይን ሐረግ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። አዳም የወይን ሐረግ ነበረ ። በበደል ምክንያት መራራ ፍሬ አፈራ ። ልጆቹን ለሞት ወለደ ። ኢየሱስ ክርስቶስ ግን እውነተኛው የወይን ሐረግ ነውና በእርሱ ላይ የተተከሉ ቅርንጫፎች ጣፋጭ ፍሬ ያፈራሉ ። ወንጌላዊው ስለዚህ ግንድ ፥ ቅርንጫፍና ፍሬ ይናገራል ። ፍሬ በውስጥ ጣፋጭ ውኃ ይዟል ። ውኃው እንዲወጣ ግን መጨመቅ አለበት ። ክርስቲያንም ጣፋጭነቱና አርኪነቱ እንዲወጣ በትግል መጨመቅ አለበት ። ፍሬ ቅርንጫፉንና ግንዱን ይገልጣል ። መልካም ሥራችንም ክርስትናችንንና ክርስቶስን ይገልጣል ። ቅርንጫፍ የሚያፈራው ከግንዱ በሚመጣለት ምግብ ነው ። ክርስቲያንም በክርስቶስ ኃይል መልካም ሥራ ይሠራል ። ቅርንጫፍና ግንዱ ያለማቋረጥ ተያይዘዋል ፥ ምእመንና ክርስቶስም ያለማቋረጥ መያያዝ አለባቸው ። ቅርንጫፍ ግንዱን እንደማይሸከም ፥ ግንዱ ግን ቅርንጫፉን እንደሚሸከም ፤ ያለነው በጌታችን ትከሻ ላይ ነው ። ወንጌላዊው ስለ ፍሬ ውኃ ይናገራል ።
15- የምሥጢር ውኃ ፡-
 መንፈሳዊ ዓለም የምሥጢር ዓለም ነው ። አስደናቂና በእምነት የምንቀበላቸው ነገሮች ያሉበት ዓለም ነው ። ምሥጢር ነውና በጥንቃቄ መያዝ አለበት ። ጌታችን ብዙ ምሥጢር ሊነግራቸው ፈልጎ ደቀ መዛሙርቱ ግን አቅም እንደሌላቸው ባየ ጊዜ እስከ መንፈስ ቅዱስ መምጣት አዘገየው /ዮሐ. 16፥13/ ። ውኃ የማያፈስ ነገር ይፈልጋል ። ውኃን ለመያዝ ቀዳዳን መድፈን ግድ ይላል ። ወደ ዓለም የሚያፈስሱ ብዙ ቀዳዳዎች ያሉት ሰው የእግዚአብሔርን ምሥጢር ሊገነዘብ አይችልም ። ጌታ ምሥጢሩን የሚነግረው ለታመኑ ወዳጆቹ ነው /ዮሐ. 15፥15/ ። በታማኝነት ለሚያገለግል ባሪያም ምሥጢር አይነገርም ፥ የምሥጢር መስፈርቱ ወዳጅነት ነው ። ጌታን በእውነት እንወደዋለን ? ስንወደው ምሥጢሩን እናውቃለን ። ወንጌላዊው ስለ ምሥጢር ውኃ ይናገራል ።
16- የአንድነት ውኃ ፡-
ጌታችን ከሞቱ በላይ ያሳሰበው የደቀ መዛሙርቱ አንድነት ነው ። ለዚህ ነው በምሴተ ሐሙስ በጌቴሴማኒ ስለ አንድነት የጸለየው /ዮሐ. 17/ ። እግዚአብሔር የሚከብረው በአንድ ልብ ነው ። አንድነት በአንድ አዳራሽ የመሆን ሳይሆን በአንድ ልብ የማሰብ ውጤት ነው ። አብሮ መብላት ሳይሆን አብሮ መዝመት ነው ። ዓላማን ፊት ለፊት አድርጎ እርስ በርስ ከመተያየት ወይም ከመነቃቀፍ ወጥተን ለአንዱ ዓላማ መኖር ነው ። ጌታችን ስለዚህ አንድነት ጸለየ ። አንድነታችን እንደ ውኃ ነው ። ውኃ እሳትን ያጠፋል ፥ አንድነትም ክፉ ነገርን ያርቃል ።  ውኃ ያለመልማል ፥ አንድነትም ምድርን ይለውጣል ። ዛሬ የጎደለን አንድነት ነው ። አንድ ያድርገን ።
17- የቄድሮን ውኃ ፡-
 የቄድሮን ወንዝ ጌታችን የተያዘበት ስፍራ ነው ። ጌታችን በዚህ ስፍራ ያዘወትር ነበር ። ይሁዳ ጌታን ለመያዝ ሳይሆን ለማስያዝ ገንዘብ ተቀበለ ። ራሳቸው የማይዙ ግን የሚያሲዙ ቅጥረኞች አሉ። ይሁዳ እንዲያ ነበር ። ጌታችን በዚያ የጭንቅ ሰዓት በቄድሮን ወንዝ አጠገብ ሆነ ። ያ ስፍራ ለጌታችን የጽሞናና የጸሎት ስፍራ ነው ። ይሁዳ የመጣው እዚያው ነው ። ጠላት የሚመጣው የምንረካበትና የምናርፍበት ስፍራ ላይ ነው ። ወንጌላዊው ስለ ቄድሮን ወንዝ ይነግረናል /ዮሐ. 18፥1/ ።
18- የድንግል ውኃ ፡-
 እመቤታችን ድንግል ማርያም በመስቀሉ ሥር በታላቅ ኀዘን እንደ ተሰበረች ፥ ብርቱ እንባ እንዳፈሰሰች የምንረዳው ጌታችን በመስቀል ላይ ሆኖ ለዮሐንስ አደራ ሲሰጣት ነው /ዮሐ. 19፥26/ ። ምንም እንኳ ለቤዛ ዓለም መምጣቱን ብትረዳም የእናትነት አንጀቷ ግን አልቻለም ነበር ። ጌታችንም ለእርሱ በሚታሰብለት ሰዓት ለእርሷ አሰበ ። በመስቀል ላይ ሆኖም ዮሐንስን ልጅ አድርጎ ሰጣት ። ለእንባዋና ለኀዘኗ ዋጋ ሰጠ ። ለዮሐንስ ብቻ አይደለም በክርስቶስ ለሚያምኑ ሁሉም እናት ናት ። ዮሐንስን እነሆ እህትህ አላለውም ፥ እነሆ እናትህ አለው ። የጌታችን እናት ለዮሐንስ እናት ለመሆን አታንስም ። ከጌታችን ሌላ ልጅ ቢኖራት ኖሮ የእናቴን ነገር ለወንድሞቼ አደራ ይለው ነበር ። ዮሐንስ ግን አደራ መቀበሉ ብቻ አይደለም ወደ ቤቱም ይዟት መሄዱ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ መሆኑን የሚገልጥ ነው ። ወንጌላዊው ስለ ድንግል እንባ ይናገራል ።
19- የታጣው ውኃ ፡-
 ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ ተጠማሁ አለ ። የሰው ልጅ ግን የሰጠው ውኃን ሳይሆን ሆምጣጤን ነበር ። ደሙ ፈስሶ ላለቀው ጌታ ምን ያህል የውኃ ጥም እንደነበረበት መገመት እንችላለን ። ባሕርና ውቅያኖስን ወንዝና ምንጮችን ለፈጠረው ጌታ የሰው ልጅ ውኃን ነፈገው ። ዓለም የሰጠው መስቀል ብቻ ነበር ። ውኃ ለለመነ ሆምጣጤ ከመስጠት ዝም ማለት ይሻል ነበር ። ሆምጣጤ ሥራቸውን የተቀበለ ጌታ የሆምጣጤውን ውኃ ተቀበለ ። ከክፋታቸው በላይ ደግነታቸው ክፉ ነበር ። አንዳንድ ወገኖች ደግነታቸው ራሱ መዘዝ አለው ። ወንጌላዊው ስለታጣው ውኃ ይናገራል ። ውኃው ግን የታጣው መስቀል ላይ ብቻ አይደለም ፥ ያቺን ሳምራዊት ሴት ውኃ አጠጪኝ ሲላት ውኃን አልሰጠችውም ። እርሱ ግን የተጠማው የሰዎችን መልካምነት ነበር ። ሁለት ጊዜም ውኃን አልወሰደምና /ዮሐ. 19፥29፤4፥7/።
20- የፍቅር ውኃ ፡-
 መግደላዊት ማርያም የጌታን መቃብር ፍለጋ በሌሊት ገሰገሰች ። ባጣችው ጊዜ በአትክልቱ ውስጥ እየዞረች ታለቅስ ነበር ። ጌታዬን ወስደውታል በማለት ተናገረች ። ሞቶም ጌታዋ ነው ። ሞት ጌትነቱን አልሻረባትም ። አበቃ ብላም እንድትቀመጥ አላደረጋትም ። ፍቅሯ ከሞት የሚያልፍ ነበር /ዮሐ. 20፥11/ ። ዛሬ ያጡ ሰዎች ለጊዜው የሞቱ ናቸው ፥ የወደቁ ሰዎችም ለጊዜው ያንቀላፉ ናቸው ። እኛስ ስማቸውን ለመሻር ቸኩለን ይሆን ? ንብረቱን የማይጥል ጌታ ያስነሣቸዋል ። ወንጌላዊው ስለ ፍቅር ውኃ ይናገራል ።
21- የጥብርያዶስ ውኃ ፡-
 ጴጥሮስ ደቀ መዛሙርቱን አስተባብሮ ወደ ጥብርያዶስ ገሰገሰ ። መሞቱን በርግጥ አምኖ መነሣቱን ግን በርግጥ ማመን አቃተው ። ጌታ ግን ካለሁበት ይምጡ ብሎ ቢተዋቸው ኖሮ ጠፍተው ይቀሩ ነበር ። ካሉበት ድረስ ሄደ ። ጥብርያዶስ ማኩረፊያ አይሆንም ። ስለዚህ ምንም አላገኙም ። የተጨበጠ ድካም አለ ፥ የተጨበጠ ድል ግን የለም ። ጌታ ግን በተአምራት ዓሣን ሰጥቶ ወደ ጥሪያቸው መለሳቸው ። ዓለም ማኩረፊያ አይሆንም ። ጴጥሮስ ሲጠራ ይህን ተአምር አይቶ ነበር /ሉቃ. 5፥5/ ። ሲኮበልልም ያንን ተአምር ደገመለት ። የመጀመሪያውን ቀን ፍቅር ማስታወስ ለከዳ ሰው ግድ ነው ። የመጀመሪያውን ቀን ማንም ቢያስብ ዛሬ የሚያደርገውን አያደርግም ነበር ። ወንጌላዊው በሃያ አንድ ምዕራፍ 21 የውኃ ዓይነቶችን ይዘረዝራል ። ጸጋው ይብዛልን  ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ