የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ከመጨረሻው ይጀምራል

እግዚአብሔር ከመጀመሪያ ይጀምራል ፥ ከመጨረሻም ይጀምራል ። ኦሪት ዘፍጥረት ከዮሐንስ ወንጌል ጋር ተመሳሳይ መሆኑን አንሥተናል ። ኦሪት ዘፍጥረት ሲጀምር ፡- “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” በማለት ነው /ዘፍ. 1፥1/ ። ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ ከመሠረቱ ሳይሆን ከጉልላቱ መሥራት ጀመረ ይላል ። ምድራዊ ባለሙያ መጀመሪያ መሠረቱን ይደለድላል ፥ ከዚያ ወደ ጉልላቱ ይሄዳል ። እግዚአብሔር ግን ከሰማያት ጀምሮ ምድርን ይመሠርታል ። እግዚአብሔር ከመጨረሻው መጀመር ይችላል ። በቃና ዘገሊላ የሆነውም ይህ ነው ። ባለቀ ነገር ላይ ለዘመናት የሚተረክ ተአምራት ሠራ ። ጌታችን ለራሱ አንድ ቀን እንኳ አልኖረም ። ሠላሣ ዓመት እናቱን ሲያገለግል ነበረ ፥ ከሠላሣ ዓመት በኋላ ሰማያዊ አባቱን ሊያገለግል ወጣ ። ከሦስት ቀን በፊት በገዳመ ቆሮንቶስ ተርቦ ነበረ ። ረሀቡን ለማስታገሥ ግን ተአምራት አላደረገም ። አሁን ግን የሰዎችን ጉድለት ለመሙላት አምላካዊ ኃይሉን ይጠቀማል ። እርሱ በዘመኑ ሁሉ አንድ ቀን እንኳ ለራሱ አልኖረም ። ዛሬ ለራሴ አልኖርኩም የሚሉ ብዙ እሮሮዎች ይሰማሉ ። ለራሳቸው በእውነት ያልኖሩ ሰዎች ክርስቶስን መስለውታል ።
ያሳለፍነውን ሕይወት ስንገመግመው የተረፈን የለፋንበት ሳይሆን እግዚአብሔር ተሟግቶ የሰጠን ነው ። የእስራኤል ልጆች 400 ዓመታት የለፉበትን አልተቀበሉም ። እግዚአብሔር ሲዋጋላቸው ግን ግብጻውያን ወርቅና ብራቸውን አራገፉላቸው ። ምድራዊው እንጀራችን እንኳ እግዚአብሔር የሰጠን እንጂ በትግላችን ያገኘነው አይደለም ። የለፋንበትማ ብዙ ነገር ይባክናል ። ጉልላቱን የደመደምነው የመሰለን ነገር ገና መሠረቱ ያልተጣለ ነው ። ዓለም ጨረስኩ ሲባል ገና ጅምር ነው ። አወቅሁት የምንለውም ነገር ገና የማናውቀው ነው ። በማወቅ ውስጥ ብዙ አለማወቅ አለ ። ጨበጥነው የምንለውም የጉም ስፍር ነው ። እግዚአብሔር ከመጨረሻም ስለሚጀምር ደስታችን ብዙ ነው ።
እግዚአብሔር መጨረሻ ላይ ቆሞ ይጀምራል ። ከነዓን ላይ ቆሞ እስራኤልን ከግብጽ ይጠራል ። የጠላት ብዛት ፥ የዓመፅ ግሣት ሊያስቆማቸው ያልቻለው እግዚአብሔር መጨረሻው ላይ ቆሞ ስለጠራቸው ነው ። እርሱ በመካከል ስላለው ነገር ዝርዝር መረጃ አይሰጠንም ። ስለ መጨረሻው ግን ይናገራል ። የመካከሉ ኃላፊ ነውና እግዚአብሔር ስለሚያልፈው አይናገርም ። የመጨረሻው ግን ዘላለማዊ ነውና ስለ እርሱ ይናገራል ። የመካከሉ የጠላት አሳብ ነው ፥ የመጨረሻው ግን የእግዚአብሔር አሳብ ነው ። ብዙ የጠላት ምክር ቢኖር የሚጸናው የእግዚአብሔር አሳብ ነው ። የሚታገሠንም ፍጻሜው ላይ ቆሞ ስለሚጠራን ነው ። ዛሬ ደከሙ ፥ ሰነፉ፥ ወደቁ ፥ መከኑ ብሎ የማይተወን ፍጻሜአችንን ስላየልን ነው ። እርሱ የሆንነውን ሳይሆን የምንሆነውን ያይልናል ። ማንነታችን ሳይገርመው በፍቅር ከእኛ ጋር የሚኖር ፥ እንዴት ልስበረው ሳይሆን እንዴት ልጠግነው ? የሚል እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ዛሬ የንስሐ ስብከቶች የበቀል ስብከቶች የሚመስሉት በእግዚአብሔር ድምፅ ስለማይነገሩ ነው ። የተጠነቀቅንላቸው ስለ እኛ ብዙ ጉርምርምታ አላቸው ። ያልተጠነቀቅንለት እግዚአብሔር ግን እኛን በፍቅር ቅላፄ ይጠራናል ። የቃና ዘገሊላ ሠርግ የሰው ጅምር ሲያልቅ የእግዚአብሔር ግብዣ የቀጠለበት ነው ። በጉድለቱም እንጋብዘው ሳይታዘብ ይሞላል ፥ በራቁትነቱም እንጥራው ሳያወራ ይሸፍናል ።
ይገርማል የአገራችን ሰው ድንጋይን ምን ያናግረዋል ? ቢሉ ውኃ ይላል ። አሁንም የሚያናግረን ያ ውኃ ነው ። ሙሉ ሠርግ ቢሆን ኖሮ እስካሁን አይነገርም ነበር ። እግዚአብሔር የሞላው በመሆኑ ግን ሲነገር ይኖራል ።
አዎ በሕይወት ውስጥ ብዙ ብስጭቶች ሊኖሩብን ይችላሉ ። የጀመርኩት ለምን አላለቀም ? ያሰብኩት ለምን አልተፈጸመም ? እንል ይሆናል ። ነገር ግን የምንፈልገው ባይሆንም የፈቀደው ግን እየሆነ ነው ። ወደ መንፈሳዊ ብስለት ስንመጣ ስላጣነው ነገር አመስግነን መፈጸም ያቅተናል ። ያልነው ሁሉ ቢሆን በሕይወት እንቆይም ነበር ። በመስጠት ብቻ ሳይሆን በመንሣትም ፍቅሩን የገለጠልን እግዚአብሔር ይመስገን ። ያ ፍቅር የመኖራችን ምሥጢር ነው ። ዘመኔ አለቀ ፥ አሳቤ ራቀ አትበሉ ። የዓለም ፍጻሜ ቢሆንም አትስጉ ። የዓለም ፍጻሜ የቊጥር ፍጻሜ እንጂ የእውነት ፍጻሜ አይደለም ።
በዚያ ዘመን ብዙ ሠርጎች ተከናውነዋል ። ይህን ሠርግ ልዩ ያደረገው ምንድነው ?
1-  ቅዱሱና ቅዱሳኑ የተጠሩበት በመሆኑ
2-  ሠርጉ አደጋ የገጠመው በጅምር በመሆኑ
3-  ጌታችን ክብሩን የገለጠበት በመሆኑ ነው ።
የሚጸልዩልን ወዳጆች ካሉ ጉድለት ያን ያህል አስፈሪ አይደለም ። በማንኛውም ጉዳያችን እግዚአብሔርን መጋበዝ መልካም ነው ። ቢበላሽ እንኳ ዋስትና አለው ። በጅምር ሠርክ የሆኑ ጉዳዮች ቢኖሩ መፍትሔው ግን እግዚአብሔር ነው ። የችግሩ ምንነት ባይገባንም አንወቀስም ። የመፍሔውን አምላክ ማወቅ ግን ይጠበቅብናል ። እኛ ያወቅነውን አልፈየድነውም ። ስለዚህ አዲስ ለማወቅ አንጓጓም ። እግዚአብሔር ግን መፍትሔ ባለው እውቀቱ ይረዳናል ። ጉድለታችን የጸሎት ርእስ ከሆነን የተባረከ ጉድለት ነው ። ትልቁ ጉዳት ከእግዚአብሔር መራቅ ነውና ። እርሱ ጉድለታችንን የክብሩ አደባባይ ካደረገው ደስ ሊለን ይገባል ። ስለ ጥያቄአችን ሳይሆን ስለ መላሹ ፥ ስለ ችግሩ ሳይሆን ስለ ረዳቱ ማሰብ መልካም ነው ። እግዚአብሔር ከጥያቄአችንም ከመልሳችንም ፥ ከችግራችንም ከደስታችንም በላይ ነው።
 የችግሩን መንስኤ ካወቅሁት ይበቃኛል እንላለን ። እግዚአብሔር ግን በእውቀቱ እያጽናናን ነው ። እርሱ ሁለት ጊዜ ያስደስተናል ። ሲናገረንና ሲፈጽምልን ። ሠርግና ሞት አንዴ ነው ይባላል ። የአንዴው ሲበላሽ አይረሳም ። እግዚአብሔር ግን ይክሳል ። በገደሉና በወለሉ መካከል ያለው ርቀት ለሚወርደው ሰው በጣም ቅርብ ነው ። እግዚአብሔር ግን ውድቀታችንን ቀድሞ ያድነናል ። የተዘጋ ደጅ እኛን እንጂ ጌታን አይመልሰውም ። ግድግዳው ደጃፉ የሆነው ፥ የፈንጂ ወረዳ የማይመልሰው ፥ በባሕር ውስጥ መተላለፊያ የሚሰጠው እግዚአብሔር ዛሬም ሕያው ነው ። አዎ ድንግል ዮሐንስ ስለ ሠርግ ለመግለጥ የተጨነቀው ፡-
1-  እውነተኛውን ሙሽራ ለማብራራት ነው ።
2-  የልመናን ዋጋ እንድንረዳ ነው ። ጊዜው ባይደርስም የእመቤታችን ልመናዋ ሠምሯል ።
3-  እምነታችንን ለማጠንከር ነው ።
 ይህን የቃና ዘገሊላ ተአምር ለማስተባበል በዘመናት ብዙዎች ጥረዋል ። በኮሚኒዝም ርእዮተ ዓለም ዘመን አንድ ከሃዲ ሕዝቡን ሰብስቦ “ኢየሱስ ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ ለወጥኩ ያለው ኬሚካል ተጠቅሞ ነው ። ይኸውላችሁ” በማለት ውኃውን በኬሚካል ለወጠው ። አንድ ክርስቲያን ግን ብድግ ብሎ “እስቲ ይጠጡት” አለ ። ከሃዲውም “ይገድለኛል” አለ ። ክርስቲያኑ ግን መለሰ ፡- “ኢየሱስ የለወጠው የሚጠጣ ወይን ጠጅ ነበረ” አለ። ጌታ የሚለውጠው የሚጠጣ ነው ።
ስሙ ይቀደስ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ