አካል የሌለው ራስ እንደሌለ ፥ ሙሽሪት የሌለችውም ሙሽራ የለም ። ጌታ በቅርበት ድምፅ አካል ፥ በፍቅር ድምፅ ሙሽሪት ያለን እኛ ነን ። በሰው ዓለም ሠርግ ይቀድማል ፥ ኑሮ ይከተላል ። ከሠርግ በኋላ ሙሽሪት ሚስት ፥ ሙሽራም ባል ይሆናል ። በክርስትናው ዓለም ግን ኑሮ ይቀድማል ፥ ሙሽርነት ይከተላል ። ሙሽርነት ለአንድ ቀን ነው ። የአንድ ቀን ንጉሥ ፥ የአንድ ቀን ንግሥት መሆን ነው ። ከዚያ ወዲያ ኑሮና ግብግብ ይጀምራል ። በመንፈሳዊው ዓለም ግን ኑሮ ይቀድማል ፥ ሙሽርነት ይከተላል ። ጌታችን ዳግም የሚመጣው አካሉ የተባለችውን ቤተ ክርስቲያን ሊሞሽራት ነው ። አንድ ሰው ሲያገባ ሙሽሪትን ከአባቷ ቤት ወደ አባቱ ቤት ይዞ ይሄዳል ። ጌታችንም ከምድራዊው ዓለም ወደ ሰማያዊ አባት የሚጠቀልለን ሙሽራችን ነው ። የወላጅ ቤት ምንም ቢጣፍጥ ቆይቶ ግን ቋንቋው የሚያቀያይም ፥ መቼ ነው የምትወጣው ? እየተባለ ቀን የሚቆጠርበት ፥ ቆሞ ቀር እየተባለ ስድብ የሚጎርፍበት ፥ ምንም ይሁን ብቻ ውጪልኝ የሚባልበት ነው ። ዓለም እንደ ወላጅ ቤት ነው ። ምንም ቢጣፍጥ መለየት አይቀርም ። ቋንቋ አላግባባ እያለ የተሳሳመ የሚነካከስበት የማለዳ ፀሐይ ነው ። ሰዎች በሰላም መኖር እያቃታቸው በሰላም በተለያየን እያሉ የሚሳሉበት ፥ሥራው አገልግሎቱ ቆሞ ቀር እየተባለ የሚተችበት ነው ። የነገሠም የጰጰሰም እኩል ከምስኪኑ ጋር የሚያነባበት ነው ። ጣሩ ሲበዛ “የተጨነቀችውን ነፍስ አሳርፍ” እየተባለ ጣፋጭ ጸሎት የሚጸለይበት ነው ። ዓለም የወላጅ ቤት ናት ። እንኳን መከራዋ ምቾቷም ይቆረቁራል ። የቀጠረን ያ ሙሽራ መጥቶ ወደ አባቱ ቤት ሲወስደን እረፍት ነው ። ምንም ይሁን የሚባልለት ሳይሆን ከማንም በላይ የሆነ ሙሽራ ነው ።
ዓለሙ ምጽአት እያለ የሚፈራውን ያን ቀን ቤተ ክርስቲያን ደግሞ የሰርግ ቀን አድርጋ ትጠብቀዋለች ። በቃና ዘገሊላ ሰርግ ላይ ታላቁና አማናዊው ሙሽራ ክርስቶስ ተገኘ ። በዚያ ሰርግ ላይ በገነት የተመሠረተውን የአዳምና የሔዋንን ጋብቻ ፥ በመጨረሻው ቀን የሚጀምረውን የአካሉን ሰርግ ሳያስብ አይቀርም ። በሦስቱም ሠርግ እርሱ አለ ። እርሱ ሺህ ዓመትን እንደ አሁን የሚያስብ ነው ። በዘለላለም አሁን የሚኖር በመሆኑ ያለፈውን ለማስታወስ ቆይ ብሎ ማሰብ ፥ የሚመጣውን ለማወቅ መገመት አያስፈልገውም ። የጊዜ ጌታ ነውና ሁሉም ዘመናት ፥ ያለፉትና የሚመጡት ሺህ ዓመታት በፊቱ እንደ አሁን ይታሰባሉ ።
በዚያ ዘመን የነበረው ሙሽራ ራሱ ደጋሽ ፥ ራሱም አስተናጋጅና ራሱም ሙሽራ ነው ። ክርስቶስም ራሱ ደጋሽ ሆኖ ሁሉን ያዘጋጀ ፥ ራሱ አስተናጋጅ ሆኖ በማዕድ ታጥቆ የሚያገለግለን ፥ ራሱም ሙሽራ ሆኖ የሚያስደስትን የምንጠብቀው ትልቅ እንግዳ ነው /ዕብ. 3፥4 ፤ ሉቃ. 12፥37 ፤ ራእ. 19፥9/ ። ሙሽራ የሌላት ሙሽሪት እንደሌለች ፥ ክርስቶስ የሌላት ቤተ ክርስቲያንም ልትኖር አትችልም ። ሰው ብዙ አሽከሮች እያሉለት አካሉን እንደሚፈልግ ብዙ መላእክት የከበቡት ጌታ አካሉን ቤተ ክርስቲያንን ይፈልጋታል ። ሙሽራይቱ እንድታምርለት ሙሽራ ሁሉ ይመኛል ። መንፈስ ቅዱስም የሚኩል ፥ የሚድር ፥ የውበት የበላይ ጠባቂዋ ሆኖ ተሰጥቷል ። በጥንቱ ዘመን አንዲት ልጅ ያለ ዕድሜ ትዳራለች ። ሙሽርነቷን ሳታውቀው በእንኮኮ ከቤት ትወጣለች ። አሳቡ ለባሏ እንድትሰጥ ሳይሆን በእናቱ እቅፍ ውስጥ ሁና አብረው ያድጋሉ ። ጠባዩን ታውቃለች ፥ እንደ ወንድሟም ታየዋለች ። ጊዜው ሲደርስም ከእናቱ እቅፍ ወጥታ ትሰጣለች ። ዛሬም አማኝ አንዳንዴ በእቅፍ ይዳራል ። በሕጻንነቱ ይጠመቃል ፥ ለክርስቶስ ይሰጣል ። ላያውቅ ይችላል ። ግን በቤቱ ያድጋል ። በመንፈስ ቅዱስ ከለላ ውስጥ ይኖራል ። ያቺ ሙሽራ የልጅነት ወንድሟን የኋላ ባለቤቷን እስከ ሞት አትለይም ። አማኙም እንደ ወንድም ጋሻ ሆኖ የመከተለትን ፥ በምሥጢራት የተባበረውን ጌታውን እስከ መጨረሻው አይለይም ። እስከ ማታ የሚቆዩ በጠዋት የገቡ ናቸው ። እስከ ሰርጉ ቀን እስከ ምጽአት ድረስ የቤተ ክርስቲያን ባለ አደራ መንፈስ ቅዱስ ነው ። የእርሱ እቅፍ ፥ የእርሱ ከለላ ከእናት በላይ ፍቅርና ጥበቃ ያለው ነው ።
የእስራኤል ዘመን የእጮኝነት ዘመን ነው ። ቤተ ክርስቲያን ከዑር ምድር ከከለዳውያን አገር ከአብርሃም ሰፈር ታጨች ። ሰርግን ስታናፍቅ ትዳርን ከሁለት ሺህ ዓመት በኋላ በክርስቶስ ሥጋዌ ጀመረች ። ትዳር ነውና ጉዞዋ መስቀል የበዛበት ሆነ ። መቼ ነው ሰርጉ ? እያለች ብዙ ወልዳ ሠርግ ያምራታልና ሠርጉን በመጨረሻው ቀን አደረገላት ። ከሠርግ ማግሥት ግብግብ የለባትም ። ሰርጉ መጨረሻ ሆነላት ዘላለም ሙሽሪት እንድትሆን ነው ። በሰርግ ሥርዓት ሁለት ሰዎች ይሞሸራሉ ፥ ሺህዎች ደግሞ ያጅባሉ ። በላይኛው ቤት ግን ሁላችንም ሙሽሮችና ሰርገኞች ነን ። በዚህ ዓለም ሰርገኛ ቡራቡሬ ነው ። ጥቁርና ነጭ ጤፍ በአንድነት ሠርገኛ ይባላል ። በዚያኛው ዓለም ግን ሁሉም ነጭ ልብስ ይለብሳሉ ። የሚገርመው በቀይ ደም ታጥቦ ልብሱ ነጭ መሆኑ ነው ። እጮኛዋ እስራኤል በእቴጌ ቤተ ክርስቲያን ተተካች ። እቴጌ ቤተ ክርስቲያንም ክብርት ሙሽሪት ሁና ንግሥትነት ከሙሽርነት ጋር ተቀብላ በቀኙ ትኖራለች ።
የመጨረሻው ቀን በሰርግ መመሰሉን መጽሐፍ ይነግረናል /ማቴ. 22፥1-14/። ያ ሰርግ አስደናቂ ጠባዩ ይመጣሉ የተባሉ የሚቀሩበት ፥ ይቀራሉ የተባሉ የሚመጡበት ነው ። ይመጣሉ የተባሉ እስራኤል ቀርተው አሕዛብ የተገኙበት ፥ ሐናና ቀያፋ ቀርተው ወንበዴው የገባበት ነው ። መንግሥተ ሰማያት አስደናቂ ነው ። የሉም የተባሉ ሰዎች የሚኖሩበት ፥ ይኖራሉ የተባሉ የሚቀሩበት ነው ። ዮሐንስ በራእዩ ፡- “እርሱም፦ ወደ በጉ ሰርግ እራት የተጠሩ ብፁዓን ናቸው ብለህ ጻፍ አለኝ። ደግሞም፦ ይህ የእግዚአብሔር እውነተኛ ቃል ነው አለኝ” ብሏል /ራእ. 19፥9/ ። አሁን ደግሞ የቃናውን ሰርግ ይዘግብልናል ። ዮሐንስ ምድራዊ ሙሽርነት የለውምና የላኛውን ሰርግ የናፈቀ ይመስላል ። ማጫውን የላከ ቀጥሎ ራሱ ይመጣል ። ኦሪት ማጫ ነበረች ። በሐዲስ ግን በረከትን ሳይሆን ራሱን ሰጠን ። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሆነው በስጦታ ሳይሆን በሥጋዌ ነው ። ተስፋ ማጫ ነው ። ፍጻሜው ደግሞ አካላዊ ነው ።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃና ዘገሊላ ሰርግ በመገኘቱ የእውነተኛው ሰርግ ዘመን መከፈቱን ገለጠ ። እውነተኛው ሙሽራ በምሳሌው ላይ ተገኘ ። ምሳሌ በባሕርዩ ጎዶሎ ነው ይባላል ። በባሕርዩ ጎዶሎ ካልሆነ ስለ ሙሉ እውነት መናገር አይችልም ። ምሳሌ በሰው አፍ አይደለም የሚጎድለው ። በባሕርዩ ጎዶሎ ነው ። ምድራዊ ሙሽርነትም ጎዶሎ ነው ። የሙሉ ጌታ የክርስቶስ ምሳሌ ነውና ። ጉድለት ያስደነቃችሁ ፥ ለጉድለቱ እገሌ እና እገሊት ተጠያቂ ናቸው የምትሉ ምሳሌ በባሕርዩ ጎዶሎ መሆኑን እወቁ ። ይልቁንስ ወደ በጉ ሰርግ ተጠርታችኋልና ደስ ይበላችሁ ። ቤተ መንግሥት የተጠራ ሳይሄድ ኩሩ ነው ። ጥሪውን ያወራል ። የንጉሥ ጥሪ ነውና በሰበብ አይቀርም ።
እናንተ ሰርገኞች የጥሪው ካርድ እምነት ነውና እንዳይጠፋባችሁ ። ጥሪው ካርዱ እንዳይለያችሁ ይላልና ። ድግሱ ሰፊ ነውና ለሕጻናት ቦታ የለንም አይልም ። ስለዚህ ሕጻናትንም አምጡ ። ካርዱ መግቢያ ብቻ ሳይሆን ዕዳችን የተከፈለበት ደረሰኝም ነው ። እናንተ ሰርገኞች ልብሳችሁን የሚያነጻውን ቀዩን ምንጭ የክርስቶስን ደም አትዘንጉ ። የምድሩማ ገና በሙሽርነት ቀን ይጎድላል ። የሰማዩ ግን በፍጹሙ ጌታ ተዘጋጅቷልና ሙሉ እንደሆነ ፥ እንዳበራ ይቀጥላል ። ወደ በጉ ሰርግ የተጠራችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ ።