ወንጌላዊው ዮሐንስ ስለ ሰርጉ ለመተረክ ያሰበበት ዓላማ ምንድነው ? ዓላማው ሰርገኞቹን ለማድነቅና ለማወደስ እንዳልሆነ ስማቸውን እንኳ ባለመጥቀሱ ይታወቃል ። ዓላማው ግን በአጭሩ ሦስት ነው ፡-
1- የእመቤታችን የድንግል ማርያምን የእምነት ጸሎት ለማብራራት ነው ፡- እመቤታችን ድንግል ማርያም ያቀረበችው ጸሎት ተራ ጸሎት አይደለም ። በእምነት የተሞላ ጸሎት ነው ። የቅዱሳን ታሪክ የተጻፈልን መንፈሳዊ ኑሮ በምድር ላይ የሚኖር መሆኑን ለመግለጥ ነው ። የቅዱሳን ታሪክ የእምነት ጉልበትን የሚያበረታ ነው ። ለእግዚአብሔር ብዙ ያደረግንና ስለ እግዚአብሔር ብዙ መከራ የተቀበልን ሲመስለን ያጋነንነውን ነገር በመጠን እንድናየው የሚያደርገን የቅዱሳን ታሪክ ነው ።
2- ስለ ክብሩ ለመናገር ነው ፡- የሰዎች ችግር እየተፈታ ፥ ጉድለታቸው እየሞላ ቢሆንም ግቡ ግን ክብሩን መግለጥ ነው ። የእግዚአብሔር ክብሩ በኃይሉ ውስጥ አለ ። ክብሩ መገለጥ የሚያስፈልገው ለምንድነው ? ስንል ያመነው እንዲጸና ያላመነው ልቡ እንዲነሣሣ ነው ። በቃና ዘገሊላ ያመኑት ተአምር የተደረገላቸው ሰርገኞች ሳይሆኑ ደቀ መዛሙርት ናቸው ። ብዙ ተአምራት ቢደረግ ሰዎች ወደ እምነት ዓለም የሚመጡ ይመስለናል ። የሚያምነው ያመነው ነው ። ብዙ ተአምራቶች አይሁድን ለግድያ አነሣሥተዋል ። ዛሬ ተአምራት የማያደርጉ ሙሉ የእግዚአብሔር ሰዎች አይመስሉን ይሆናል ። ነገር ግን ዮሐንስ መጥምቅ ትልቅ የእግዚአብሔር ሰው ነው ። በእጁ ግን አንድም ምልክት አልተደረገም ። ቃሉ፡- “ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጥተው ፡- ዮሐንስ አንድ ምልክት ስንኳ አላደረገም፥ ነገር ግን ዮሐንስ ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ነበረ አሉ” ይላል /ዮሐ. 10፥41/። በዮሐንስ እጅ ግን ብዙዎች ወደ ንስሐና ወደ ክርስቶስ መጥተዋል ። የተአምራት ግቡም ይህ ነው ። የተአምራት ግቡ ተአምር ይዞ መሮጥ ሳይሆን ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው ።
3- የደቀ መዛሙርቱን ማመን ለመግለጽ ነው ፡- ደቀ መዛሙርቱ የተከተሉት አምነው አይደለም ወይ ስንል ? ገና እምነታቸው ሙሉ አልሆነም ነበር ። ለሌሎች የተደረገው ተአምራት ግን ለእነርሱ ማመን ጉልበት ሆነ ። እግዚአብሔር እንዲሠራ እንጸልይ በዚያ ውስጥ አንዱ ጋኑ ሲሞላለት አንዱ እምነቱ ይሞላለታል ። የእመቤታችን ጸሎት ይህንን ወልዷል ። በእምነት ስፍራ ላይ ያለ እምነት የሚኖሩ ብዙ አሉ ። “እኛም አንተኛ ሰውም አናስተኛ” እንደሚባለው የማይተኙ የማያስተኙ አሉ ። ሰይጣን ሰዎችን ከቤተ ክርስቲያን ማስወጣት ብቻ ሳይሆን የማስገባት ሥራም ይሠራል ። ቤቱን ለማተራመስ ። አዎ ዮሐንስ ጭንቀቱ ስለ ሰርግ ለማውራት አይደለም ። የሰርገኞቹ ስማቸው እንኳ አለመጠቀሱ ይህን ያስረዳል ።
ጌታችን ቀጠሮ የማይረሳ ነው ። ስለ ሰርጉ የሰማው ከዐርባ ቀን በፊት ነው ። በሰዓቱ ተገኘ ። እርሱ የማኅበራዊ ኑሮ መሥራችና ቀዳሽ ነው ። የሰዎች የፍቅር ግንኙነት ያስደስተዋል ። ከዐርባ ቀን በፊት ከተለያት እናቱ ጋርም በዚህ ሰርግ ተገናኙ ። ሠላሳ ዓመት ሙሉ ለአንድ ቀን ተለይቷት የማያውቀው ልጇ ወደ ተልእኮው ሲገባ አልተከላከለችም ። እርሷ እናት ብቻ ሳትሆን የእምነትም አርበኛ ናትና ። በዮርዳኖስ አብ የመሰከረውን ምስክርነት በናዝሬት ሁና ሰምታለች ። እርሷ ግን ገና ሳይጸነስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አውቃለች ፥ አምናለች ። በገዳመ ቆሮንቶስም በታላቅ ተጋድሎ ሲከርም ልቧ ሳያስብ አይቀርም ። ዘመኗን በሙሉ ኀዘነተኛ ናት ። የመከረኛ እናት መከረኛ ናትና ። እኛ በመከራው እንደሰታለን ። እርሷ ግን ለድኅነተ ዓለም መምጣቱን ብታውቅም የእናትነት አንጀቷ ግን ያዝንለት ነበር ። ስምዖን አረጋዊ እንደ ተናገረው በነፍሷ ሰይፍ አልፏል /ሉቃ. 2፥35/። ስለዚህ ሰማዕት ናት ። ሰማዕታት በአንገታቸው ሰይፍ አለፈ ፥ እርሷ ግን በነፍሷ ሰይፍ አለፈ ። የእርሷ መከራ ይበልጣል ። በዮርዳኖስ እርሷ ብቻ የምታውቀውን ልጅነቱን አባቱ ከሰማይ ሲመሰክር ደስ ይላታል ። መሰወሩ ይቆጫታልና ። የቃና ዘገሊላ ልመናዋም ቊጭት የቀላቀለ ነበር ። ከሁሉ በላይ በቃና ዘገሊላ ደስታዋ ተወዳጅ ልጇን ከዐርባ ቀን በኋላ ከበረሃ ኑሮ መመለሱ ያስደስታታል ።
መልአኩ ገብርኤል የነገራት የምሥራች ለእርሷ ደስታ ነው ። ዓለሙ ግን አያውቀውምና ውስጧ ያዝናል ። ስለዚህ ቊጭቷ እንዲፈጸም ተአምራትን አደረገ ። አነስተኛ የናዝሬት ኑሮዋ ፥ የግብጽ ስደቷ ፥ መከራ የበዛበት ቤቷ እንዲለወጥ ሠላሣ ዓመት ተአምራትን አለመነችውም ። እንዴት የወለድኩት አምላክ ከሆነ ይህ ሁሉ ደረሰብኝ ? አላለችም ። ስለሚድነው ዓለም ብቻ ታስባለች ። ከቃና ዘገሊላ በኋላ ዳግም ቃል ስትናገር አይሰማም ። ልጇን ገልጣዋለችና እርሱ ይናገር ብላ አርፋለች ። ቊጭቷ ይኸው ተፈጸመ ። በዘመኗ ሁሉ የሚወጋት ያ ሰይፍ ዐርባ ቀን ሲለያትም ወግቷት ነበር ። ዛሬ ቊስሉ ባይድንም ጥዝጣዜው ይቀንሳል ። ቃና ዘገሊላ ሠላሳ ዓመት የታሰረ አንደበት የተፈታበት ፥ የታፈነው ምሥጢር የተገለጠበት ነው ። አባቱ ሲመሰክርለት ሰምታለች ፥ አሁን ተራው የእርሷ ነው ። የመጀመሪያዋ ወንጌላዊት ናትና በእርሷ ስብከት ይኸው ደቀ መዛሙርቱም አመኑ ። ሰው እኩያ እናት ስላለው ይደሰታል ። እናቴ ዘመናዊት ናት ። እናቴ የተማረች ናት እያለ ይመካል ። ድንግል ማርያም የእምነት እናት ናት ። ቃና ዘገሊላ ኢየሱስ የቤት ልጅነቱ የሚያበቃበት ፥ እርሷም የቤት እናትነቷ የሚያበቃበት ነው ። ቃና ዘገሊላ ትልቅ አስተርእዮ ነው ።
ብቻውን የምታውቀው ጭምቱ ልጇ ፥ የመላእክት አምላክ የምድር ብቸኛ መሆኑ እንኳን እርሷን እኛንም እያሳዘነን ነው ። ዛሬ ግን በደቀ መዛሙርት ተከቦ ሲመጣ ደስ አላት ። እርሷ ብቻ ማመኗ አላስደሰታትም ፥ ዛሬ ግን ብዙዎች እንዲያምኑት መጋረጃውን ገለጠች ። መምህር ሆይ ብለው የተከተሉት አምላክነቱን አይተው አመኑ ። ቊጭት ከሌለ ሥራ አይሠራም ። ዛሬ ደቀ መዛሙርት አስከትሎ ሲመጣ በናዝሬት የሚያውቁት ምን ይሉ ይሆን ?