የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ወላዲተ አምላክ

ወንጌላዊው ዮሐንስና ወንጌላዊው ሉቃስ የኢየሱስ እናት በማለት ይጠሯታል /ዮሐ. 2፥1፤የሐዋ. 1፥14/። ኢየሱስ ሰውና አምላክ የተዋሐዱበት የተዋሕዶ ስም ነው ። ሥጋን ከሰማይ ይዞ ወረደ የሚሉ መናፍቃን የኢየሱስ እናት በሚለው መጠሪያ ይረታሉ ። ባልወለደችው እናቱ ልትባል አትችልምና ። ከእርሷ ሥጋን እንጂ ነፍስን አልነሣም የሚሉም ከእናታችሁ ሥጋን ብቻ ነው የነሣችሁት ? በማለት እንጠይቃቸዋለን ። ድንግል ማርያም የወለደችው ሰው ነው ፥ በሠላሳ ዓመቱ የአምላክ ልጅ መጥቶ አደረበት ወይም በቅባት ልጅ ሆነ የሚሉም በዚህ መጠሪያ ይረታሉ ። ማርያም ከማለት የኢየሱስ እናት ማለታቸው ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክነቱን ስለሚገልጥላቸው ነው ። እርሷ የኢየሱስ እናት ናት ። የወለደችው አምላክ ባይሆን ኖሮ በድንግልና መጽነስ አትችልም ነበር ። ሲወለድም አማኑኤል አይባልም ነበር ። አማኑኤል ማለት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ማለት ነው ። ኢየሱስ እግዚአብሔር ባይሆን ኑሮ በልደቱ አማኑኤል አይባልም ነበር ። መጠን በሌለው ክብር ያከበሯት መስሏቸው አንዳንዶች ከሰማይ በወረደ መልክ ያቀርቧታል ። እነርሱን ለመቃወም የቆሙት ደግሞ ከድንግል ማርያም ጋር የግል ጠብ ያላቸው እስኪመስል ያናንቋታል ። ክብሩንም ንቀቱንም የሚሽረው ግን የኢየሱስ እናት የሚለው ነው ። የኢየሱስ እናት ከመሆን በላይ ክብር የለምና ።
ንስጥሮስ “ወላዲተ ሰብእ” እንጂ “ወላዲተ አምላክ አትባልም” ብሎ ተነሣ። ሊቃውንቱ ግን ክርክሩን ከእርስዋ አንሥተው ወደ ክርስቶስ  አምላክነት ወሰዱት ። የእርሱን አምላክነት ላመነ እርሷን ወላዲተ አምላክ ለማለት አይፈተንም ።
ከእርስዋ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን  መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በብሥራት ጊዜ ተናግሯል /ሉቃ. 1፥35/። ስለዚህ አንዱ የእግዚአብሔር ልጅ ነው የሰው ልጅ የሆነው ። የተወለደውም ሕጻን ፡- “ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል” በማለት ኢሳይያስ ተናግሯል /ኢሳ . 9፥6/ ። በተወለደ ጊዜም ሰብአ ሰገል ሰግደውለታል /ማቴ. 2፥11/። የተወለደው ኃያል አምላክ ነውና ሰብአ ሰገል የአምልኮ ስግደት አቅርበውለታል ። እርሱ በሥጋ የመጣ አምላክ መሆኑን ሐዋርያው ይገልጻል ፡- “ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ፥ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው፤ አሜን” ይላል /ሮሜ. 9፥5/ ።
ቤተ ክርስቲያንን ሲያውክ የኖረው የእነ ፕላቶንና ከዚያም የግኖስቲኮች ግሪካዊ ፍልስፍና ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ አያምንም ። ምክንያቱም ለፍጥረተ ዓለም ሁለትነትንና ሁለት አማልክትን የሰጠው የግሪክ ፍልስፍና ግዙፉ ፍጥረት የንዑሱ አምላክ ሥራና ደግሞም የረከሰ ነው ። ረቂቁ ፍጥረት ግን የደጉ አምላክ ሥራ ነው ። ደጉ አምላክ እንኳን ሥጋ ሊለብስ ሥጋን መንካት ያረክሰዋል ብለው ያስባሉ ። ይህ ፍልስፍና ወደ አንጾኪያ ትምህርት ቤት ገብቶ ብዙዎችን አጥምቆ ነበር ። ንስጥሮስም እመቤታችን ድንግል ማርያምን ወላዲተ ሰብእ እንጂ ወላዲተ አምላክ አይደለችም በማለት ሲነሣ በዚህ ግሪካዊ ፍልስፍና ውስጥ ወድቆ ነበር ። ይህ ስህተትም ክብረ ድንግልን የሚነካ ብቻ ሳይሆን ክብረ ክርስቶስንና የሰውንም መዳን የሚነካ ነበር ። ከእርስዋ የተወለደው ሰው ብቻ ከሆነ ቃል ሥጋ ሆነ የሚለው ምሥጢረ ሥጋዌ ዋጋ ያጣል ። ባሕርያችንን ካልተዋሐደ ደግሞ መዳናችን እውን ሊሆን አይችልም ። በመስቀል ላይም የተፈጸመው የአንድ ፍጡር ሞት በመሆኑ በፍጡር ዓለም ዳነ ማለት አይቻልም ። ይህንንም የንስጥሮስን ስህተት አባቶች ከክርስቶስ አምላክነትና ከነገረ ድኅነት ጋር በማየት በኤፌሶን ጉባዔ በ431 ዓ.ም አውግዘውታል ። ታዲያ በቃና ዘገሊላ ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ የለውጠው እርሱ አምላክ ከሆነ የኢየሱስ እናት ወላዲተ አምላክ መባሏ ትክክል ነው ።
ንስጥሮስ የክርስቶስን አምላክነት አጥብቆ የሚቀበልና አርዮሳውያንንም ለማጥፋት የሚጥር ሲሆን በዚህ በኩል ደግሞ ወላዲተ አምላክ አትባልም በማለት ሲወድቅ እናየዋለን ። ልክ እንደ ንስጥሮስ የክርስቶስን አምላክነት እየተቀበሉ የእርስዋን ወላዲተ አምላክነት አለመቀበል ተገቢ አይደለም ። ንስጥሮስ በኋላ ላይ የተመለሰ ለማስመሰል “ወላዲተ ሰብእ” የሚለውን “ወላዲተ ክርስቶስ” በማለት ተክቶት ነበር ። አሁንም አሳቡ “ክርስቶስ ሰው ብቻ ነውና ሰው ብቻ የሆነው የክርስቶስ እናት ናት” ለማለት ነው ። ይህ ትምህርት ግን የክርስቶስን አምላክነት የሚነካ መዳንን ከንቱ የሚያደርግ ነው ። የኤፌሶን ጉባዔ የእርስዋን ወላዲተ አምላክነት ያረጋገጠ ሲሆን ንስጥሮስን በሌላ መልክ ይዞ የመጣውና ካቶሊካዊ ትምህርትን የወለደው የኬልቄዶን ጉባዔ የአይሁድን ሰቃልያነ አምላክነት እንዲያምን የተጠየቀ ነው። አይሁድ የሰቀሉት አምላክን ከሆነ የተሰቀለው አንድ አካል አንድ ባሕርይ መሆኑን መቀበል ግድ ይላል ። አምላክ ብቻውን ሊሰቀል ፥ ሰውም ብቻውን ሊያድን አይችልምና ። በተዋሕዶ ግን አንድ አካል አንድ ባሕርይ የሆነው እርሱ ተሰቅሎ አድኖናል ።
የብዙ ቅዱሳን ሕይወት ምሳሌ እየተደረገ ትምህርት ይሰጣል ። ሣራም ፥ ርብቃም ፥ ራሔልም ፥ ሃናም ፥ አብርሃም ፥ ይስሐቅ ፥ ያዕቆብን አብነት አድርጎ ይሰበካል ። በዚሁ አንጻር የድንግል ማርያምን ሕይወት አብነት አድርጎ መስበክ ተገቢ ነው ። አንድ የፕሮቴስታንት ጸሐፊ ስለ መላእክት መጽሐፍ ጽፈው ለመጻፍ ያነሣሣቸውን አሳብ ሲገልጡ “ስለ አጋንንት መደርደሪያ ሙሉ መጽሐፍ ተጽፎአል ። ስለወደቀው መልአክ ይህን ያህል ሲጻፍ ስለ ጸኑት ግን የተጻፈ አንድ መጽሐፍ ግን ላገኝ አልቻልኩም ስለዚህ ይህንን መላእክት የሚለውን መጽሐፍ አዘጋጀሁ” ብለዋል /ቢሊ ግርሃም መላእክት/። ስለ ጸኑት ማሰብ ያጸናል ። ዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ሁለት ለዘመናት የሚያራብሽ ክፍል ነው። ምንም የሚያራብሽ ነገር የለውም ። የተጻፈውም የእግዚአብሔርን ሥራ ለማክበር ነው ። ስለ ሣራ ስለ ሃና ሲጻፍ ያልተከፉ ስለ ድንግል ማርያም ሲጻፍም ሊከፉ አይገባቸውም ። ያከበራት እርሱ ነው ። ኃይለ አርያማዊት ወይም ከሰማይ የወረደች ናት ብለው የሚያስተምሩትን የሚረታው “አንቺ ሴት” በማለት ጌታ የጠራትን ማስታወስ ነው /ዮሐ. 2፥4/ ። ምክንያቱም ድንግል ማርያም የአዳም ዘር ፥ የሴት ወገን ናትና ። ለመናቅ የሚሹትም ጊዜው ባይደርስም ስለ ልመናዋ ውኃውን ወይን ጠጅ ማድረጉን ማሰብ ያስፈልጋቸዋል። እንደሚያከብራት እየታዘዘ ማደጉ ፥ እንደሚወዳት በመስቀል ላይ ሳለ ስለ እርስዋ ማሰቡ ያስረዳናል ።
እመቤታችን ድንግል ማርያምን በሚመለከት የሚነሡት ተቃውሞዎች የመጀመሪያው ማንኛችንም እንደ እርስዋ መሆን እንችላለን የሚለው አስተሳሰብ ነው ። ድንግል ማርያም ግን የአምላክ እናት የሆነችው በድንገት አይደለም ። በገነት “የሴቲቱ ዘር” በሚለው በኢሳይያስ “እነሆ ድንግል ትጸንሳለች” በሚለው ተስፋና ትንቢት ትልቅ ዝግጅት የነበረው ነው /ዘፍ. 3፥15፤ ኢሳ. 7፥14/ ። ለድንግል ማርያም የተሰጠው ጸጋ የማይደገም ጸጋ ነው። ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላ አምላክን የወለደችና የምትወልድ ሴት የለችም አትኖርምም ። በዚህም ምልእተ ጸጋ ናት ። እግዚአብሔርን ሁሉ አምላኬ  ይለዋል ። ከተስፋነቱም “ልጄ እርሱ ነው” የሚሉም ይኖራሉ ። እርስዋ ግን በመብትና በቀጥተኛ መንገድ ወላዲተ አምላክ ናትና ልጄ ብላዋለች ። ሥጋዌንም ድንቅ ያደረገው ሁሉን የሚችልና የማይወሰን አምላክ በእርስዋ ማኅጸን መወሰኑ ነው ። ንስጥሮስን የከበደው ነገር ፡- “ፈጣሪ ከፍጡር ሊወለድ አይችልም” የሚለው ነው ። የጌታችንን ፍቅሩንና ቸርነቱን ማሰብ ካልቻልን ሥጋዌን መቀበል ይከብዳል ። ድንግል ግን ፈጣሪዋን ወለደች ። ሁለተኛው የተሳሳተ አስተሳሰብ ተጠቅሞ ጥሏታል የሚል ነው ። እርሱ ግን ያገለገሉትን የማይረሳ ነው ። ዛሬ የምናገለግለውንስ ተጠቅሞ ይጠለናል ወይ ? ተጠቅሞ የሚጥል ቢሆን ኑሮ በመስቀል ላይ እያጣጣረ እናቱን ለዮሐንስ አደራ ይሰጥ ነበር ወይ ? የእመቤታችን ሕይወቷ ብዙ የምንማርበት ፥ ትዕግሥቷ ዛሬውን ግልብልብ ክርስትና የሚገስጽ ነው ። እውቀቷም ተራ እውቀት ሳይሆን በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ትርጓሜ የበረታች እንደሆነች በጸሎቷ ፥ ከመልአኩ ጋር ባደረገችው ምልልስ የምንረዳው ነው ። በርግጥም ቅድስትና የእምነት እናት ናት ።
 የቃና ዘገሊላው ውሎ ብዙ ነገሮችን የሚቀሰቅስ ነው ። በክርስትናው ውስጥ ትልቅ ዋጋ ያለውን ምሥጢረ ሥጋዌን እንደ ገና እንድናስታውስ ይጋብዘናል ። ምሥጢረ ሥጋዌ እስከዚህ እንዴት ተወደድን ? ብለን በአሳብ የምንጠፋበት ፥ በፍቅር የምናለቅስበት ነው ። ምሥጢረ ሥጋዌ ከብዙ የስህተት ትምህርቶች የምንተርፍበት ጋሻ ነው ። ምሥጢረ ሥጋዌ ለመዳናችን የተደረገውን ጉዞ መሠረታዊ የምናደርግበት የጸና ዓለት ነው ።
                                    በጸጋው ያግዘን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ