የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የአርምሞ ትሩፋቶች

4   ትዕግሥት
 ትዕግሥት ዝምታ አይደለም ። እንደ ፍግ እሳት ውስጥ ውስጡን እየተቃጠሉ ከላይ ሰላም መምሰል ይህ ትዕግሥት አይደለም ። ትዕግሥት መቀመጥ ፥ የቀን ቸርነትን መጠበቅም አይደለም ። ትዕግሥት በጸሎት አደባባይ ሆኖ እግዚአብሔርን ተስፋ ማድረግ ነው ። በትዕግሥታቸው የተመሰከረላቸው ብዙ ሰዎች ቢኖሩም ትዕግሥት ግን ከእያንዳንዱ አማኝ የሚጠበቅ መንፈሳዊ ፍሬ ነው ። የታገሡ ሰዎች የትዕግሥታቸው ምሥጢር ምን ነበረ ? ስንል ፡-
1-  የአሁኑ ገጠመኝ የመጨረሻዬ ነው ብለው አልተቀበሉትም ።
2-  የሄደው ለምን ሄደ ? ለማለት የባለቤትነት ስሜት አልነበራቸውም ።
3-  የሚፈልጉትንም እንደ ፈቃዱ ይጠብቁ ነበር እንጂ ቀን ቆርጠው በዚህ ጊዜ ይሁን አይሉም ነበር ።
4-  ሁሉም ነገር ኃላፊ መሆኑን ሲረዱ እግዚአብሔር ብቻ ቋሚ መሆኑን ያምናሉ ።
5-  ስለ እግዚአብሔር ብለው የሚቀበሉትን ነገር እንደ ሙሉ ክብር ይቆጥሩት ነበር ። በዚህ ዓለም ላይ ያሉ ሰዎች ከትልቅ ሰው ጋር አብረው ሲከሰሱ በታላቅ ደስታ እንደሚቀበሉት ።
6-  በእግዚአብሔር እውቀት ስላረፉ እርሱ ባወቀው ነገር ዋስትና አለኝ ብለው ያምኑ ነበር ።
7-  ብርሃኑ ጨለማ እንደሆነ ጨለማውም ብርሃን ይሆናል ብለው ያምኑ ነበር ። ከሌሊት በኋላ ሌሊት አይመጣምና ።
 በዚሁ ተቃራኒ ትዕግሥት ማጣትን የሚወልደው ምንድነው ስንል?
1-  መሰናክሎችን እንደ መጨረሻ መቊጠር
2-  ይህ ለምን ሆነ ? በማለት አየር መጎሰም
3-  ፈቃደ እግዚአብሔርን አለመቀበል ማለት ጊዜን ፥ ቦታንና መንገድን ለእግዚአብሔር ማመልከት
4-  ያላለፈ ነገር እንደሌለ ላያልፍም የመጣ ነገር የለም ። ትዕግሥትን ያጡ ሰዎች ግን አምላካቸውን እንዳለፈ ታሪክ ፥ ችግራቸውን እንደ ሕያው አምላክ ይቆጥሩታል ።
5-  እውነተኛ መሆን ማለት እውነትን ባላወቁና በማይወዱ ሰዎች መገፋት መሆኑን አለመረዳት
6-  ለእግዚአብሔር በጸሎት ከነገሩ በኋላ ከማረፍ እንደገና እኔው ላብጀው በማለት በአሳብ መዋተት
7-  የደስታው ጊዜ እስኪረሳ እንዳለፈ ፥ የመከራውም ጊዜ እስኪረሳ ያልፋል ብለው አለመቀበል የትዕግሥት ማጣት ችግር ነው ። በርግጥ ዛሬን ዛሬ ያለነው ብዙ አልፎ ነው ። ዛሬ ያሳላፊው ጌታ በረከት ናት ።
 እመቤታችን ድንግል ማርያም የአርምሞ ሕይወት ብቻ ሳይሆን የትዕግሥት ሕይወትም ነበራት ። ስለዚህ ከላይ የጠቀስነው ጠባይ ይታይባታል ማለት ነው ። ስምዖን አረጋዊ የአራስ ጥሪ አድርጎ የሰጣት ሰይፍ ነበር ። ስምዖንም ባረካቸው እናቱን ማርያምንም ፡- እነሆ፥ የብዙዎች ልብ አሳብ ይገለጥ ዘንድ፥ ይህ በእስራኤል ላሉት ለብዙዎቹ ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሾሞአል፥ በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል አላት” /ሉቃ. 2፥34-35/ ። ሰዎች የመጨረሻ ክፋታቸውን ያለ ይሉኝታ ይገልጡበታል ። የልባቸው አሳብ ያለ ከልካይ ይገለጣል ። በመጨረሻው ክፋታቸው ላይ እርሱ የመጨረሻውን ደግነት ያሳያል ። ለሚቃወሙትም ለምልክት ተሹሟል ። በዚህ ጊዜ የመከረኛ እናት መከረኛ ናትና ፡- “በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል” አላት ። ስምዖን አረጋዊ ይህን ቃል ሲናገር ጌታችን የዐርባ ቀን ሕጻን ነበረ ። ልጅዋን ይህች ዓለም የምትቀበለው አበባ ይዛ ሳይሆን አፈር ይዛ መሆኑን ነገራት ። ስለ ውድ ልጅዋ ይህን መስማት በራሱ መከራ ነው ። በነፍስ ላይ የሚያልፍ ሰይፍ ብርቱ ኀዘን ነው ። ክርስቶስ መከራ በተቀበለ ዘመን ሁሉ እርስዋም ትሰቀቅ ፥ በኀዘንም ትወጋጋ ነበር ። እንደ ስምዖን ትንቢት እንዲሁ ሆነ ። ዘመኗ በሙሉ የኀዘንና የመከራ ነበር ። የቃና ጉድለት እንዲሞላ የለመነችው ይህ የመከራ ኑሮዋ እንዲለወጥ ግን አልለመነችም ። ይህ ሁሉ መሆን እንዳለበት አምናለች ። በታላቅ ትዕግሥትም በታላቅ ዝምታም ዘመኗን አሳልፋለች ። በነፍሷ ላይ ያለፈው ሰይፍ ምን ነበር ?
1- በፀነሰች ጊዜ ፡-
 አንዲት ሴት ያለ ጋብቻ ፀንሳ ብትገኝ እንድትሞት ኦሪት ታዛለች ። ያለ ወንድ ዘር የፀነሰች ድንግል ማርያምም ፅንሷ አሳሳቢ እንደሆነ ይታያል ። አሳሳቢነቱ ይህን ምሥጢር በማያውቀው በዮሴፍ ዘንድና በአይሁድ ዘንድ ነው። ምንም እንኳ ጠባቂዋ ዮሴፍ ጉዳዩ ግራ ስለ ገባው በስውር ሊተዋት ቢያስብም አሁንም በትዕግሥት ትጠብቅ ነበር ። የምሥጢር ማኅደር ነበረች። ለሰዎች ሊያስረዱት ከምክንያት በላይ የሆነ ነገር ሲገጥም ፥ አጠገብ ያለ ሰው ራሱን ገሸሽ ማድረግ ሲጀምር ምን ያህል ጭንቀት እንዳለው በውስጡ የሚያልፉ ያውቁታል ። በፀነሰችው ጌታ የአይሁድ ውግረት ፥ የዮሴፍ መሸሽ እየመጣ ይመስላል ። ይህን ሰይፍ ግን በትዕግሥት ተቀበለችው ።
እግዚአብሔር ያደረገልን ትልቅ ተአምር እንዴት እንደሆነ በሰዎች ቢታወቅ ምን አልባት ጠላት ሊያበዛ ይችላል ። ጠላትን በማጣት ብቻ አይደለም ፥ በተአምራትም እናመርታለን ። ይረዱናል የምንላቸው ያውም ደግሞ ጻድቅ የሆኑት ሊሸሹን ቢሰናዱ ሁሉም ነገር ጭልም ሊልብን ይችላል። ማሰብ ግን ያለብን እግዚአብሔር የተናገረንን ነው ። እመቤታችን ድንግል ማርያም በመልአኩ በኩል የተነገራትን አሰበች ። ያ ብቻ አይደለም ተአምራዊውን ፅንስ ተሸክማለች ። ወልድን ለመሸከም ያጸናት አሁንም ጽናት ሲሆናት እናያለን ። ዝርዝሩን ለመናገር አስቸጋሪ የሆኑ ተአምራቶችን በልብ ይዞ ማመስገን ትዕግሥት ይጠይቃል ። ለእኛ መልስ የሆነን ዝርዝር ሌሎች ቢሰሙት ጥያቄ ይሆንባቸዋል ። የድንግል ማርያም ድንግልናዊ ጽንስም በእውቀት ሳይሆን በእምነት የተቀበልነው ነው ። ዛሬም እንኳ ይህን መቀበል የሚቸገሩ አሉ ። ድንግል ማርያም ግን ይህ ሰይፍ በትዕግሥት ተቀበለች ። የአርምሞ ሕይወቷም ሰዎች እንዲረዱላት ከመድከም ጠብቋታል ። እግዚአብሔር ለሁሉም ራሱን የሚገልጥበት መንገድ ፥ የሚያነጋግርበት ቋንቋ እንዳለው ታምናለች ። ይህ ትዕግሥት ሲኖረን እወቁኝ ከሚል ጭንቀት ፥ ተረዱኝ ከሚል ልፍለፋ ፥ ሰው ላጣ ነው ከሚል መዋተት እንድናለን ። ትዕግሥት በሌሎች አለማወቅና ስህተት ተስፋ አለመቊረጥ ነው ። አርምሞ የትዕግሥት እናት ናት ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ