የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የአርምሞ ትሩፋቶች

4   ቅርታ
የአርምሞ ሕይወት ይቅርታን ለመለማመድ ምቹ መንገድ ይሰጣል ። ብዙ ጊዜ ስናገር ይቀለኛል ብለን እናስባለን ። ስንናገር ግን የበለጠ እየተቀጣጠልን ውስጣችን በቂም እያመረቀዘ ይመጣል ። የምንናገርበት መንገድ ክርስቲያናዊ ከሆነ ፈውስ አለው ። በሁለት ዓይነት መንገድ ንግግሮች ይኖራሉ ። የመጀመሪያው በወቀሳ መንገድ ሲሆን ሁለተኛው ግን በክስ መንገድ ነው ። ወቀሳና ክስ ፍጹም የተለያዩ ነገሮች ናቸው ። የወንድማችንን አንድ ዓይነት በደል በመንፈስ ቅዱስ ዓይን ማየትና በሰይጣን ዓይን ማየት ነው ። ወቀሳ የመንፈስ ቅዱስ ነው ፥ ክስ ደግሞ የሰይጣን ነው። ወቀሳ ለሰውዬው ሲሆን ክስ ግን ለሌሎች ነው ። ወቀሳ በር ዘግቶ የሚደረግ ሲሆን ክስ ግን በአደባባይ ነው ። በወቀሳ መንገድ መነጋገር የተቋረጠውን ግንኙነት ይመልሳል ። ክስ ግን ተናጋሪውንም ተከሳሹንም ሰሚውንም ይጎዳል። ያሰብነውን እንናገራለን የሚለው ሁሉም ሰው የሚቀበለው የተለመደው መርሕ ነው ። የተናገርነውን እንደምናስብ ግን ብዙ ጊዜ አንረዳም ። በንዴት ሰዓት በክርክር ጊዜ በድንገት ከአንደበታችን የሚወጡ ከዚህ በፊት አስበናቸው የማናውቃቸው ንግግሮች አሉ ። አንድ ጊዜ ከአንደበታችን ስለወጡ እንደገና እናስባቸዋለን ። ለተናገርናቸው ነገሮች ታማኝ ለመሆን እንሞክራለን ። የተናገርነውን ማሰብ ማለት ይህ ነው ። አርምሞ ከዚህ ስህተት ይጠብቀናል ። ሌሎች በእኛ ላይ ያደረሱትን በደል የምንናገር ከሆነ እያደስነው እንመጣለን ። ከዚህ ሊገላግለን የሚችለው ነገር ምንድነው ? ስንል ፡-

1-  የሆነብን ሲሆን የነበረ እንጂ አዲስ አለመሆኑን ማሰብ
2-  የነገሮችን አስቂኝ ጎናቸውን ፈልጎ ተጨማሪ ደስታ ማድረግ ። አንድ ፈላስፋም ፡- “ኀዘንና መከራን የቀልድ መንገድ ማድረግ ያስፈልጋል። ካልሆነ ማበድ ይከተላልና” ብሏል ። ይኸው ሰው ፡- “የሕይወትን ግብ ማወቅ ፈተናን ለመቋቋም ብቻ ሳይሆን ከሚያዋዥቅ አቋምም ያድናል ። አሸናፊም ያደርጋል” ብሏል ።
3-  ክርስቶስ እንኳ በዚህ ምድር ላይ ብዙ መከራ ተቀብሏል ። ለትልቁና ለቅዱሱ ጌታ ያልተመለሰ ዓለም ለእኔ አይመለስም ብሎ ማሰብ ልበ ሰፊነትን ያጎናጽፋል ።
4-  በዝምታ ፥ መጽናናት በሞላበት አርምሞ ይቅርታን መለማመድ ይገባል ።
 ጻድቁ ኢዮብ ከመከራው በላይ መከራውን የሚተነትኑ ባልንጀሮቹ በብርቱ አቊስለውት ፥ በቊስል ላይ ጥዝጣዜ ሆነውበት ነበር ። የመከራው ማዕበል ካለፈ በኋላ እግዚአብሔር የኢዮብን ባንጀሮች ገሰጻቸው ። ኢዮብም እንዲጸልይላቸው ነገራቸው ። “ኢዮብም ስለ ወዳጆቹ በጸለየ ጊዜ እግዚአብሔርም ምርኮውን መለሰለት እግዚአብሔርም ቀድሞ በነበረው ፋንታ ሁለት እጥፍ አድርጎ ለኢዮብ ሰጠው”  /ኢዮብ .42፥10/ ። እግዚአብሔር ሁለቱንም ወገኖች ሲወቅስ እናያለን ። ኢዮብ አዝኖባችኋል ፥ የጸሎታችሁ መንገድ ተዘግቷል አላቸው ። ኢዮብም በመቀየሙ በረከቱ ተይዞበት ነበር ። የኢዮብ ወዳጆች መጥተው አብረውት መሥዋዕት ባሳረጉ ጊዜ ሁለቱም ተፈቱ። መሥዋዕታቸው ሰመረ ። የኢዮብም ምርኮ ተለቀቀ ። በይቅርታ ውስጥ አእምሮ ሰላም ፥ ልብ ደስታ ያገኛል ። ለመራመድ ጉልበት ፥ ለመጸለይም አቅም ይኖራል ። አህያ ጅብን ከያዘችው በጥርሷ ትገድለዋች ። ነገር ግን በፍርሃት ስለማትለቀው ተመርዛ ትሞታለች ። ሌሎችም በቂም ነክሶ መያዝ ሙት እንደ መንከስ ሁኖ ይገድላል ።
 ይቅርታን ከሚያዘገዩ ነገሮች አንዱ አንደበት ነው ። እግዚአብሔርን መፍራትና መጠበቅ ያለበት አርምሞ ግን ለይቅርታ ያሰናዳል ። የአርምሞ ሕይወት የነበራት እመቤታችን ድንግል ማርያምም የይቅርታ ሕይወት ነበራት። ልጅዋን በመስቀል ላይ በግፍ ሲሰቅሉት አልተቀየመችም ። ታላቅ ኀዘን ብታዝንም ውስጧ ግን በቀል አልነበረም ። ጌታችን የተሰቀለበት አንዱ ምክንያት ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ይላል የሚል ክስ ነበር ። እርስዋ ግን ገና ከጽንሰቱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ታውቅ ነበር ። በዚህች ሐሰተኛ ዓለም ግን አልተደነቀችም ። መልስ ለመስጠትም አልሞከረችም ። ልጇ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካከለ ብለው ሲገድሉት ሰብአ ሰገል ያቀረቡለትን ስግደትና እጅ መንሻ ብታውቅም አሁንም ቅር አልተሰኘችም ። ውስጧ ይቅርታ ያደርግ ነበር ።
 “እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር” ይላል /የሐዋ. 1፥14/ ። ይህ ጊዜ ጌታችን ካረገ በኋላ በመካከል ባለው አሥር ቀናት ውስጥ ነው ። እመቤታችን በጸሎት የምትተጋው “አላውቀውም” ብሎ ከካደው ከጴጥሮስ ጋር ትንሣኤውን ለማመን ከዘገየው ከቶማስ ጋር ነበር ። ስም ዝርዝራቸው ተጠቅሶአል /የሐዋ. 1፥13/። እናቶች ምንም የፍቅር ልብ ቢኖራቸውም ልጃቸውን የነካባቸውን መቀየም እንደ ትክክለኛነት ይመለከቱታል ። ልጃቸው ይቅር ቢል እንኳ እነርሱ ይቅር ለማለት ፈቃደኛ የማይሆኑበት ጊዜ ይበዛል ። እመቤታችን ግን እናት ብቻ ሳትሆን አማኒም ናትና የይቅርታ ልብ ነበራት ። ከነጴጥሮስና ከነ ቶማስ ጋር በጸሎት የሚያተጋ ይቅርታ ብቻ ነው ። ጊዜው የራቀ ነው እንዳንል አርባ ቀን ያህል የሚሆነው ነው ። መንፈሳውያን ሰዎች የይቅርታን ሕይወት አስቀድመው ስለሚይዙ በጉዳት ቀን ይቅር ለማለት አይታገሉም ። የይቅርታ ትግል እንዳይመጣ ፡-
1-  ሰዎችን እንደ ራሳችን መውደድ መልካም ነው ። ራሳችን ለቊጥር በሚያታክት መልኩ ያጠፋል ። ዘወትር አብረነው የምንኖረው ይቅር ስለምንለው ነው ። የይቅርታችን ምክንያቱም ራሳችንን ከጥፋታችን ለይተን ማየታችን ነው ። ሰዎችንም እንደ ራሳችን ስንወዳቸው ከጥፋታቸው ለይተን እናያቸዋለን ።
2-  መጠኑ ይነስ እንጂ የማናዝንበት ሰው ላይኖር ይችላል ። ስለዚህ ሰዎችን አስቀድመን ይቅር ማለት አለብን ። አሁን ያሉትን ገፍተን ብንሄድ የሚቀጥለውም ጉድለት ያለበት ነው ። የይቅርታን ሕይወት መለማመድ ግን ከትግል ያድናል ።
 ጸሎት ለይቅርታ ወሳኝ ነው ። ይልቁንም የተቀየምናቸውን ሰዎች በጸሎት ላይ ስማቸውን እየጠራን ይቅር ብያለሁ ማለት ንጹሕ ልብን ያጎናጽፋል ። ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም የምንማረው ይቅርታን ነው።
1-  አብረውን ኖረው ፥ አብረውን በልተው እንደ ጴጥሮስ የካዱን ቢኖሩ እኛም ይቅር ማለት አለብን ። ልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ፡-
 “ወዳጅ ለክፉ ቀን ይሆናል አትበለው
 ስትያዝ ይከዳል ሰው የጴጥሮስ ልጅ ነው” ብለዋል ።
  2-  ሞታችንን አምነው መነሣታችንን የተጠራጠሩ ቢኖሩ እኛም ይቅር ማለት አለብን ። ተስፋ የቆረጡብን ፥ አበቃ ብለው የማጠቃለያ ዜና ያነበቡብን እጅግ ያሳዝኑናል ። ግን እግዚአብሔር ለክብሩ ካስነሣን ለበቀል የሚሆን ጊዜ ሊኖረን አይገባም ። አንድ ትልቅ አባት ፡- “እግዚአብሔር ከዚያ ኑሮ አንሥቶ ለዚህ ክብር ካበቃኝ ሌሎችን ለመቀየም እኔ ማን ነኝ? ብለዋል ።
 እመቤታችን ድንግል ማርያም ልጅዋ በመስቀል ላይ ይቅር ያላቸውን ከእርሱ ጋር በመተባበር ይቅርታ ሰጠቻቸው ። ይቅርታ የእግዚአብሔር ጠባይ ነው። እግዚአብሔር በእኛ ውስጥም ሊያገኘው ከሚፈልገው ነገር አንዱ ይቅርታ ነው ።
ቅዱስ አውግስጢኖስ ፡- “በእስጢፋኖስ ጸሎት ቤተ ክርስቲያን የጠፋውን ጳውሎስን አገኘች” ብሏል ። የእስጢፋኖስ ጸሎት የይቅርታ ጸሎት ነበር ። እስጢፋኖስ ሲወገር ልብሱን ይጠብቅ የነበረው የቀድሞው ሳውል የአሁኑ ጳውሎስ ነው /የሐዋ. 7፥54-60/ ። ጸሎቱ ሁለት ዓይነት ተጽእኖ አሳድሯል ። የመጀመሪያው ጳውሎስ በዚያ የፍቅር ኃይል እንዲነካ አድርጓል ። ሁለተኛ ጳውሎስ የሚመለስበትን ጸጋ አምጥቷል ። ጳውሎስ ኋላ ላይ የተመካው የእስጢፋኖስ ቤተሰብን በማጥመቁ ነው ። በልጃቸው ገዳይ እጅ የተጠመቁት የእስጢፋኖስ ቤተሰቦች የይቅርታ ሕይወት ነበራቸው ። “ከእስር ቤቶች ሁሉ ዘግናኙ እስር ቤት በተዘጋ ልብ ውስጥ መኖር ነው።”
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ