የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጊዜዬ አልደረሰም

“ኢየሱስም፦ አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት” /ዮሐ. 2፥4 / ።
አንቺ ሴት የሚለው ቃል ፍቺው ምን እንደ ሆነ አይተናል፡፡ “ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?” የሚለው ዘይቤም ለብዙ ሰዎች በክርስቶስና በድንግል ማርያም መካከል ክፍተት እንዳለ ማስረጃ አድርገው ያቀርቡታል ፡፡ ይህንን የመሰለ ንግግር በመጽሐፍ ቅዱስ በብዛት እናገኛለን ፡-
ልጁ አቤሴሎም ባሳደደው ጊዜ በመንገድ ሳሚ የሚባል ሰው ትቢያ እየረጨ ዳዊትን ሰደበ ፡፡ በዚህ ጊዜ የሠራዊት አለቆች እንግደለው ብለው ሲነሡ፡- “ንጉሡም ፡- እናንተ የጽሩያ ልጆች፥ እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ?” አላቸው /2ሳሙ. 16፡10/ ፡፡ ከእናንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ? ማለቱ ነው ፡፡ ለምን እንዲህ አለ፡- አንደኛ፤ እግዚአብሔር ይህን ቆጥሮ የበደልኩትን በደል  ይቅር ቢለኝ ብሎ፡፡ ሁለተኛ፤ የገዛ ልጄ እንዲህ ካደረገኝ ከሌላ ምን እጠብቃለሁ? ብሎ፡፡ ሦስተኛ፤ እግዚአብሔር የግፍ ጽዋ ሲሞላ ቶሎ ይፈርድልኛል ብሎ ነው ፡፡ ስለዚህ ይህን ሰው እገድላለሁ የምትሉት ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? አላቸው ፡፡ መከራዬ እንዳያጥር የምታደርጉት ምን በድያችሁ ነው? ማለቱ ነው ፡፡

በሌላ ስፍራም እነዚህን ቁጡ የጦር አለቆች፡- “ዳዊትም፦ እናንተ የጽሩያ ልጆች፥ እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? ዛሬ ስለምን ጠላቶች ትሆኑብኛላችሁ?” በማለት ያንን ተሳዳቢ ሳሚን እንዳይበቀሉ ከልክሏል /2ሳሙ. 19፡22/፡፡ እግዚአብሔር ዋጋ ከፍሎ እንደ ገና የበደሉንን ዋጋ ማስከፈል ውለታውን መጣል ነውና ፡፡
በረሀብ ዘመን ኤልያስን ያስጠጋች ሴት አንድ ልጇ በሞተ ጊዜ ወደ ነቢዩ መጥታ፡- “እርስዋም ኤልያስን፦ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? ኃጢአቴንስ ታሳስብ ዘንድ፥ ልጄንስ ትገድል ዘንድ ወደ እኔ መጥተሃልን? አለችው” /1ነገሥ. 17፡18/፡፡ አነጋገሯ እኔ ጋ በቆየህበት ጊዜ ምን በደልሁህ? የሚል በውስጡ ንስሐ ያለበት ንግግር ነው ፡፡ ጌታችንም እናቱን “ከአንቺ ጋር ምን አለኝ” ሲል ጥልቅ ፍቅሩን የምናይበት ነው ፡፡ ሰርጎኞቹ ሳይለምኑ እርስዋ የእነርሱ ጉዳይ ተሰምቷት መጠየቋን እንዳከበረው የሚገልጥ ንግግር ነው ፡፡
ይህ ንግግር የሚነገረው አብረው ብዙ ጊዜ ባሳለፉና የጸና ወዳጅነት ባላቸው ወገኖች መካከል ነው ፡፡ በጣም የምንወዳቸው አንድን ነገር ሲያስፈቅዱን እንበሳጫለን ፡፡ የራሳችሁ አይደለም ወይ? ብለን ባለቤትነታቸውን ለማሳወቅ ቁጣ በሚመስል ንግግር እንናገራለን ፡፡ ይህ ንግግር ላለፉት በጎ ዘመናት ዋጋ የሚሰጥ ፣ አገልግሎትን የሚያከብር ንግግር ነው ፡፡ ጌታም እናቱን “ከአንቺ ጋር ምን አለኝ” ሲላት ምን ጠብ ምን ክርክር አለኝ? የለመንሽው መደረጉ የማይጠረጠር ነው ማለቱ ነው፡፡ ይህን ካለ በኋላ በእርጋታ፡- “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ”ማለቷ በአሳብ ስለተግባቡ ነው ፡፡ ጌታችን ለሚጠይቁት በርኅራኄ የሚመልስ ነው ብለን ካመንን ለእናቱ የሰጠው ምላሽ ከርኅራኄ ድምፅ የተለየ ነው ብለን ልናምን አንችልም ፡፡ እርሱ ለእስራኤል በተናገረበት አንቀጽ፡- “ለወይኔ ያላደረግሁለት፥ ከዚህ ሌላ አደርግለት ዘንድ የሚገባኝ ምንድር ነው?” ብሏል /ኢሳ. 5፡4/ ፡፡ እንዴት ልከልክላቸው ሳይሆን እንዴት ልስጣቸው የሚል ለምሕረት ሰፊ ልብ ያለው እግዚአብሔር ፣ የለመናችሁትን ላለመፈጸም ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? የሚል ነው ፡፡ ለእናቱ ለድንግል ማርያምም የሰጣት ምላሽ የእርሱን ልብ ያሳያል ፡፡ በዘመናት እግዚአብሔር ጸሎትን በርኅራኄ መልሷል ፡፡ ጸሎት የእርሱ የጸጋ መንገድ ነውና ፡፡ በጸሎት ውስጥ የእግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት ብቻ ሳይሆን ፍቅርም ይታያል ፡፡
ጊዜዬ አልደረሰም
 
ጊዜ ምንድነው? አባቶች፡- “ዓለም ከተፈጠረ ፣ ዘመን ከተቆጠረ” ይላሉ፡ ስለዚህ ጊዜ ዓለም ሲፈጠር የተፈጠረ ነው ፡፡ ፍጡር ከሆነም ጊዜ እግዚአብሔርን አይገዛውም ፡፡ ሁሉ ግን በጊዜ ሥር እንዲሆን ተወስኗል ፡፡ ጊዜ የእግዚአብሔር ሎሌ ነው ፡፡ ነቢዩ፡- “ሁሉም ባሪያዎችህ ናቸውና ቀኑ በትእዛዝህ ይኖራል” ይላል /መዝ. 118፡91/፡፡ ጊዜ እግዚአብሔርን ባይገዛውም ፣ እግዚአብሔር ከጊዜ ውጭ ቢሆንም ሥራን ግን የሚሠራው በጊዜው ነው ፡፡ ረጃጅም ቀጠሮዎችን የፈጸመው በጊዜ ውስጥ ነው ፡፡ 5500 ዘመን ረጅም ቀጠሮ ቢሆንም እግዚአብሔር ግን ከሰዓቱ ሳያጉድል ሳይጨምር በጊዜው ሰው ሆነ ፡፡ “ጊዜ ሲደርስ አምባ ይፈርስ” እንዲሉ ትልልቅ ግዛቶችና መንግሥታት ጊዜው ሲደርስ ይወድቃሉ ፡፡ ጊዜ ሲደርስ የፍቅር ብዛት አይታደጋቸውም ፡፡ ያለ ጊዜውም የጠላቻ ብዛት አይንዳቸውም ፡፡ “የቀን ጎዶሎን ሚዳቋም አትዘለውም” ይባላል ፡፡ ሰባራ ቀኖችን ብርታት አያልፋቸውም ፣ እግዚአብሔር ብቻ ያሳልፋል ፡፡ ስለ ጌታችን በተደጋጋሚ ከተነገሩት ነገሮች አንዱ፡- “ጊዜው ገና አልደረሰምና ማንም አልያዘውም” የሚል ነው /ዮሐ. 8፡20/፡፡ ብዙ ከሳሾች ፣ ብዙ የሚይዙ ወታደሮች ተልከዋል ፡፡ ያለ ጊዜው ግን ሊይዙት አልቻሉም ፡፡ የያዙትም መያዝ ስለቻሉ አይደለም ፡፡ ጊዜው ስለ ደረሰ ነው ፡፡ “የሰው ጀግና የለውም የጊዜ እንጂ” የሚባለው ለዚህ ነው ፡፡ ከጊዜ ውጭ ቀዳማዊ ልደቱን የተወለደው ጌታችን በጊዜ ውስጥ ደግሞ ደኃራዊ ልደቱን ከድንግል ተወልዷል ፡፡ በጊዜ መቀነት ውስጥ ገብቶ ዘመን ሲቆጠርለት በራሱ አስደናቂ ትሕትና ነው ፡፡
ጊዜ እግዚአብሔር የሰጠንን ድርሻ የምንፈጽምበት ለእያንዳንዳችን የተሰጠን በጎ ዕድል ነው ፡፡ ከተሰጠን ዘመን ውጭ ማገልገል ፣ ዘመንን ቆርሰንም ለሌላው መስጠት አይቻለንም ፡፡ ያለንበት ዘመን የእኛ ዘመን ነውና እንደ ባዕድ ተመልካች ፣ እንደ ሰነፍ ተቺ ከመሆን ልንሠራበት ይገባል፡፡
በትላንት አትቆጭ እርሱ አልፏልና
በነገም አትስጋ ያንተ አይደለምና
ዛሬን ግን ሥራበት ገንዘብህ ነውና
ከአሁን ሰዓት የተሻለ ምቹና የእኛ ጊዜ የለም ፡፡ ጊዜ መክሊት ነውና ልናተርፍበት ይገባል ፡፡ ሥራን የሚያሠራው የዘመን ርዝማኔ ሳይሆን የልብ ጥንካሬ ነው ፡፡ ማቱሳላ 969 ዓመት ኑሮ ይህን ሠራ አልተባለም ፡፡ ወጣቱ እስጢፋኖስ ግን ትልቅ ሥራ ሠርቷል ፡፡ ምቹ ጊዜ የለም ፡፡ እንዲመች የምናደርገው እኛው ነን ፡፡ በስንት ጊዜ አንዴ የሚመጡ ምቹ ጊዜዎች ግን አሉ፡፡ እነዚህን ጊዜዎች ፈጥኖ መጠቀም ከጸጸት ይጠብቃል ፡፡ ዕድሎችን አለመጠቀም ብዙ ጊዜ ይታያል ፡፡ ልጆቻችንን ለመቅረጽ የሕጻንነታቸው ጊዜ ምቹ ሰዓት ነው ፡፡ ወንጌል ለመስበክ ይህ ጊዜ ምቹ ነው ፡፡ መናገር በሚደመጡበት ዘመን ነውና መፍጠን ይገባል ፡፡ ጌታችን ፡- “ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል፤ ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች” ብሏል /ዮሐ. 9፡4/፡፡ ጌታችን ለእናቱ ጊዜዬ አልደረሰም አለ ፡፡
“ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ” /ገላ .4፡4/፡፡ ያ ዘመን 5500 ዘመን ሲፈጸም ነው ፡፡ ለምን እግዚአብሔር 5500 ዘመን ጠበቀ? አዳም በበደለ በዓመቱ ለምን አላዳነውም? ብንል አባቶች ምልዐተ ኃጢአት እስኪፈጸም ነው ይላሉ ፡፡ ክርስቶስ ምልዐተ ኃጢአት ከተፈጸመ በኋላ መጥቷልና አዲስ ኃጢአት ዛሬ የለም ፡፡ በሁሉም ኃጢአት ላይ እርሱ ድኅነት መስጠት ይችላል ፡፡ ዘመኑ በትክክልም ያ ዘመን ነበረ ፡፡
–    እርሱን መላው ዓለም ተባብሮ መስቀል ስለነበረበት የአይሁድ ካህናትና የሮማ ነገሥታት ፈርደውበታል ፡፡
–    መላው ዓለም በአንድ ንጉሥ የሚመራበት ፣ በአንድ ቋንቋ የሚናገርበት ዘመን ስለነበር ወንጌልን ለማዳረስ ምቹ ነበር ፡፡ ከቦታ ቦታ ለመዘዋወር ነጻ ፈቃድ ነበረ ፡፡ ዛሬ ወንጌል ለመስበክ የዝውውር ገደብ አለ ፡፡
–    መንገዶች ሁሉ ወደ ሮም ያቀናሉ እንደ ተባለ ወደ መላው ዓለም ለመሄድ መንገዶች በመልካም ሁኔታ ተሠርተው ነበር ፡፡ ይህም ወንጌሉን ለማፍጠን በጣም ምቹ ነበር ፡፡
     ስለዚህ ጌታችን የመጣው በትክክለኛው ሰዓት ነበረ ፡፡ እናቱን ግን ጊዜዬ አልደረሰም አላት ፡፡ ምን ማለቱ ነው?
–    እውነተኛ ችግረኞቹ ጌትነቴን አምነው ይለምኑ ብሎ ለሰርገኞቹ ጊዜ መስጠቱ ነው ፡፡
–    ጭላጩ ስለነበር ሙሉ በሙሉ ተንጠፍጥፎ ይለቅ ማለቱ ነው ፡፡ ሙሉ በሙሉ ካላለቀ በርዞ ሰጠ ይባላልና ፡፡
–    እውነተኛውን ወይን ለዓለም በመስቀል ላይ የምሰጥበት ጊዜዬ አልደረሰም ማለት ነው ፡፡
–    እመቤታችን ለዓለም በገለጠችውና ተአምራት ባደረገ ቁጥር ሞቱ እየተፋጠነ ይመጣል ፡፡ ስለዚህ ጌታችን በሰርግ ላይ ሞቱን ማሰቡ ልክ ነው ፡፡ እርሱ በጊዜው ነገርን ውብ አድርጎ ይሠራል /መክ. 3፡11/፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ