የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የምልክቶች መጀመሪያ

“ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ” /ዮሐ. 2፡11/፡፡
ወንጌላዊው ዮሐንስ ጌታችን ያደረጋቸውን ተአምራቶች ምልክት በማለት ይጠቅሳቸዋል /ዮሐ. 2፡11፤ 4፡54፤ 20፡30/፡፡ ምልክትነታቸውም ወደ እውነተኛውና ወደ ዘላለማዊው ነገር የሚመሩ መሆናቸው ነው ፡፡ ምልክቱ የበለጠ እንዳለ ልብን መቀስቀሻ ፣ የእምነትን ጥማት መጨመሪያ ነው እንጂ በራሱ ፍጻሜ አይደለም ፡፡ የእስራኤል ልጆች ቀይ ባሕርን መሻገራቸው ትልቅ ተአምር ነው ፡፡ በራሱ ግን ፍጻሜ አይደለም ፡፡ ፍጻሜው እግዚአብሔር በሚሰጣቸው ምድር ላይ እንደ ቃሉ መኖራቸው ነው ፡፡ ክርስቲያኖች የምልክት ጥገኞች እንዳይሆኑ መጠንቀቅ ያስፈልጋቸዋል ፡፡ ምልክቶች ለአሕዛብ ልብን ማነቃቂያ እንጂ ለክርስቲያኖች አይደሉም ፡፡ ለምሳሌ ፡- የልሳን ጸጋ ቢኖር ይህ ለአሕዛብ ምልክት ነው ፡፡ ምክንያቱም ከዚህ በፊት የአሕዛብን ቋንቋ ተናግሮ የማያውቅ ሰው ዛሬ ቢናገር አሕዛብ እግዚአብሔር ቢፈልገን ነው በቋንቋችን ያናገረን እንዲሉ የሚያደርግ ነው ፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ፡- “እንግዲያስ በልሳኖች መናገር ለማያምኑ ምልክት ነው እንጂ ለሚያምኑ አይደለም፥ ትንቢት ግን ለሚያምኑ እንጂ ለማያምኑ አይደለም” ይላል /1ቆሮ. 14፡22/፡፡ ትንቢት ያለው ዓይንን እየጨፈኑ ወደፊት እንዲህ ይሆናል ማለት አይደለም ፡፡ ትንቢት አሁን ያለውን ትውልድ ሰማንያ ከመቶ ተደራሽ ሲያደርግ የሚመጣውን ትውልድ ግን ሃያ ከመቶ ሊገልጥ ይችላል ፡፡ ስለዚህ ትንቢት ስብከት ነው ፡፡ ለዚህም የነቢያትን መጻሕፍት ማንበብ ተገቢ ነው ፡፡ ትንቢት ሁሉን እንደሚመለከት ሁሉን እንደሚያስተምርና እንደሚመክር ሐዋርያው ተናግሯል /1ቆሮ. 14፡25/ ፡፡ ልሳን ወይም በሌላ ቋንቋ መናገር ግን ለቋንቋው ባለቤቶች ምልክት ነው ፡፡ ልባቸውን እንዲከፍቱ የሚያደርግ ተአምር ነው ፡፡
ክርስቲያኖች ከሞቀው የቃለ እግዚአብሔር ማዕድ ላይ እየተነሡ ተአምራት ፍለጋ ይባዝናሉ ፡፡ አንዳንዶች ቅድስናቸውን ሌሎችም ገንዘባቸውንና ተስፋቸውን ሲከስሩ ይታያሉ ፡፡ በቀላሉ ሊያስወግዱት በሚችሉት ነገር ተአምራት ይፈልጋሉ ፡፡ የተሸከሙት ሥጋ ታማሚ መሆኑን ብሎም የሚሞት መሆኑን ረስተው ክርስቲያን አይታመምም ፡፡ በሽታ ሁሉ ከሰይጣን ነው ይላሉ፡፡ ከሰይጣን የሆኑ በሽታዎች አሉ ፡፡ በሽታ ሁሉ ግን ከሰይጣን አይደለም ፡፡
1-  የተጋድሎ ደዌ ፡- ጻድቁ ኢዮብ የገጠመው ደዌ የተጋድሎ ደዌ ነበር፡፡ ሰይጣን እግዚአብሔር የሚመለከው ስለሚሰጠው ጥቅማ ጥቅም መሆኑን በመናገሩና የኢዮብም እምነት ምንጩ ጥቅም መሆኑን ስላወራ ፤ እግዚአብሔር ስለ ራሱ የሚመለክ ፣ ኢዮብም ስለ ፍቅር የሚያምን መሆኑ እንዲገለጥ እግዚአብሔር በኢዮብ ተወራርዶበት እንዲታመም ፈቅዷል፡፡ ይህ የኢዮብ ደዌ ዛሬ አልፏል ፡፡ በዘመናት የሚነሡ አማንያንን ግን ሲያጽናና ይኖራል፡፡ስለዚህ የተጋድሎ ደዌ አለ ፡፡
2-  የመጠሪያ ደዌ ፡- ነቢዩ ኤልሳዕ በሚሞትበት በሽታ ታመመ ይላል /2ነገሥ. 13፡14/፡፡ አንዳንድ ደዌ መጠሪያ ነው ፡፡ እግዚአብሔር ለምን ዝም ብሎ አይወስድም ? ብንል ለቤተሰብና ለታማሚው የዝግጅት ጊዜ ለመስጠት ነው ፡፡ የከደነውን ሳይከፍት ፣ የከፈተውንም ሳይከድን እንዳይሞት የዝግጅት ጊዜ ይሰጣል ፡፡ ያስታመሙ ሰዎችም ልባቸው ስለሚዘጋጅ ኀዘናቸው ይቀንሳል ፡፡ ይቅር ለመባባል ፣ ኑዛዜ ለመስጠት እነዚህ ደዌዎች ያግዛሉ ፡፡ በሥጋም በነፍስም ለመስተካከል ፣ ሟችንም ቋሚንም ለመጥቀም የሚመጡ ደዌዎች አሉ ፡፡
3-  የመጠበቂያ ደዌ ፡- ሐዋርያው ጳውሎስ ገጥሞት የነበረው ደዌ እንዲነሣለት ቢጸልይም የጌታ ፈቃድ ግን አልነበረም ፡፡ በልብሱ ቅዳጅ ስንቱን የፈወሰ ሐዋርያ የራሱ ደዌ ግን መላልሶ ቢጸልይም መራቅ አልቻለም ፡፡ እግዚአብሔር ጸጋ ላበዛለት ሐዋርያ ደዌን የፈቀደው ከትዕቢት ሊጠብቀው ነው ፡፡ ምክንያም ትዕቢት ከኃላፊነት ያፈናቅላል ፡፡ መልአክን ሰይጣን ፣ ሰውን ኃጢአተኛ ያደረገ ፤ መጋረጃ ገላጩን ሳጥናኤል ሲኦል ፣ ገነት ጠባቂውን አዳም ምድረ ፍዳ የሰደደ ትዕቢት ነው ፡፡ ሐዋርያው ስለ ትምክሕት በተናገረበት አንቀጽ ፡- “ስለዚህም በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ፥ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ፤ ይኸውም እንዳልታበይ ነው። ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንሁ። እርሱም፦ ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ”ብሏል /2ቆሮ. 12፡7-9/ ፡፡
አባቶች ደዌያትን ለአራት ከፍለው ያስተምራሉ ፡-
1-   ደዌ ዘኃጢአት  እንደ መፃጕዕ /ዮሐ. 5፡2-9/ ፡፡
2-   ደዌ ዘመቅሠፍት  እንደ ሄሮድስ /የሐዋ. 12፡20-23/፡፡
3-   ደዌ ዘዕሤት  እንደ ኢዮብ /ኢዮ. 2፡7/ ፡፡
4-   ደዌ ዘንጽሕ  እንደ ጢሞቴዎስ /1ጢሞ. 5፡23/ 
ተአምራትን የሚፈልጉ ክርስቲያኖች ሁሉንም በሽታ ከሰይጣን ማለታቸው ብቻ ሳይሆን መድኃኒት መጠቀምንም እንደ ኃጢአትና እንደ አለማመን ይወስዱታል ፡፡ ለሐኪም የሚያክምበትን ጭንቅላትና ጥበብ የሰጠ ማነው እግዚአብሔር አይደለም ወይ ? መድኃኒቱስ እግዚአብሔር ከፈጠረው ዕጽዋት የተቀመመ አይደለም ወይ ? ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አለመሆኑን ከብሉይና ከሐዲስ መጥቀስ ያስፈልገናል ፡፡ ለታመመው ንጉሥ ለሕዝቅያስ፡- ኢሳይስም፥ የበለስ ጥፍጥፍ አምጡልኝ አለ አምጥተውም በእባጩ ላይ አደረጉለት፥ እርሱም ተፈወሰ” ይላል /2ነገሥ. 20፡7/፡፡ ኢሳይያስ ትልቅ ነቢይ ነው ፡፡ የብሉይ ኪዳን ወንጌላዊ ነው ፡፡ በጸሎት መፈወስ ይችላል ፡፡ ከእግዚአብሔር የመጣለት ድምፅ ግን መድኃኒት እንዲጠቀም ነበር ፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ብዙዎችን በጸጋው የፈወሰ ነው ፡፡ የመንፈስ ልጁ የሚሆን የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ጢሞቴዎስ ግን ታማሚ ነበርና ፡- “ስለ ሆድህና ስለ በሽታህ ብዛት ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣ እንጂ፥ ወደ ፊት ውኃ ብቻ አትጠጣ” ብሎ መክሮታል /1ጢሞ. 5፡23/፡፡ ታዲያ ጳውሎስ እምነት የለውምን ? ጢሞቴዎስስ የማያምን ነውን ? የዛሬ ክርስቲያኖች የደረሱበት እውቀት ላይ ሳይደርሱ ቀርተው ነውን ?
 ተአምራት አሳዳጅነት ለስህተት ትምህርትና ለሰይጣን አሳልፎ ይሰጣል፡፡ ተአምራት ቀጥተኛ የእግዚአብሔር መሥሪያ መንገድ አይደለም፡፡ በርኩስ መንፈስም ተአምራት ይደረጋል ፡፡ ሙሴ በፈርዖን ፊት ተአምራት ሲያደርግ የፈርዖን ጠንቋችም ተመሳሳይ ተአምራት አድርገዋል ፡፡ ሐዋርያው በመጨረሻ ዘመን ያሉትን ክርስቲያኖች ሲያስጠነቅቅ ፡- “ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደ ተቃወሙት፥ እንዲሁ እነዚህ ደግሞ አእምሮአቸው የጠፋባቸው ስለ እምነትም የተጣሉ ሰዎች ሆነው፥ እውነትን ይቃወማሉ” ይላል /2ጢሞ 3፡8/፡፡ ብዙ ሞኞችን ደግሞም የዋህ እህቶችን መጠበቅ ይገባናል ፡፡ ለዚህ ነው ወንጌላዊው ተአምራቱን በጥንቃቄ ቋንቋ ምልክት የሚለው ፡፡ ምልክትነቱም በክርስቶስ እንድናምን ነው ፡፡ ተአምራት ለሚያምኑም ለማያምኑም ይደረጋል ፡፡ የዘላለም ሕይወት ግን እምነት ይጠይቃል ፡፡
 ተአምራት ሱሰኛ ያደርጋል ፡፡ የጨው ውኃ እንደ ጠጡ እየተደረገ ሌላ ያስናፍቃል ፡፡ ተአምራት ማድረግ ለቤተ ክርስቲያን የተሰጠ ጸጋ ነው ፡፡ ይህ ማለት ፡-
1-  ከቤተ ክርስቲያን ጸጋዎች አንዱ እንጂ ጠቅላይ ጸጋ አይደለም ፡፡
2-  የተሰጠው ለቤተ ክርስቲያን ጥቅም እንጂ ለግለሰብ መግነኛ አይደለም፡፡
3-  ተአምራቱ የሚደረገው እግዚአብሔር ለበሽተኛውና ለችግረኛው ያለውን ፍቅር ለመግለጥ እንጂ የአገልጋዩን ብቃት ለማሳየት አይደለም ፡፡
4-  ተአምራት አልፎ አልፎ ሊደረግ የሚችል እንጂ መደበኛ የእግዚአብሔር አስተርእዮ አይደለም ፡፡ እግዚአብሔር ሁልጊዜ የሚያገኘን በቃሉ ፣ በምሥጢራትና በአገልጋዮች በአባቶች እረኝነት ወይም ጉብኝት ነው፡፡
5-  እግዚአብሔርን ስለ ተአምራት የሚከተል የበለጠ ካሳየው ሰይጣንንም ይከተላል ፡፡
6-  የተአምራት አገልግሎት በቤተ ክርስቲያን የመገለጥ ጸጋ መመርመር አለበት ፡፡
7-  ጌታችን ተአምራት ናፋቂዎችን ወቅሷል ፡- ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፥ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። ትቶአቸውም ሄደ” /ማቴ. 16፡4/ ፡፡
 ይልቁንም በመጨረሻ ዘመን በክርስቶስ ስም ብዙ ተአምራት አድራጊዎች ይፈልቃሉና ከሐሰተኛ መምህራን መጠንቀቅ ይገባል ፡፡ በእነዚህ ተአምራት አድራጊዎች ምክንያት ፡-
1-  ማኅበራዊ ሰላም ሊናጋ ይችላል ፡፡ ብዘዎች ትዳራቸው ፈርሷል ፡፡ ወዳጆቻቸውን ተጠራጥረዋል ፡፡
2-  ሰዎች ፈሪና ሰይጣንን ከአቅሙ በላይ ኃይለኛ ሊያደርጉት ይችላሉ ፡፡
3-  የሚኖሩትም ራሳቸው ለራሳቸው በሚያደርጉት ጥበቃ ይመስላቸዋል ፡፡ በዚህም እምነትን ያጣሉ ፡፡
 የጌታችን መወለድ እግዚአብሔር የሰጠው ትልቅ ምልክት ነው ፡፡ ይህንን ለመረዳት ቀጥሎ ያሉትን ጥቅሶች መመልከት መልካም ነው ፡፡ ጥቅሶቹ ሁሉ ያሉት በልደቱ ዙሪያ ነው ፡-
1-  “ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች” /ኢሳ. 7፡14/፡፡
2-  “ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ” /ሉቃ. 2፡12/ ፡፡
3-  “ስምዖንም ባረካቸው እናቱን ማርያምንም። እነሆ፥ የብዙዎች ልብ አሳብ ይገለጥ ዘንድ፥ ይህ በእስራኤል ላሉት ለብዙዎቹ ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሾሞአል፥ በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል አላት” /ሉቃ. 2፡34-35/ ፡፡
 እግዚአብሔር የተአምራት አምላክ ነው ፡፡ በብዙ ተአምራትም እዚህ አድርሶናል ፡፡ ዛሬም የተአምራት እጁ አልደከመችም ፡፡ መሽቶ መንጋቱ ፣ ክረምትና በጋው መፈራረቁ ፣ ከሞተ የእህል ዘር ፍሬ መገኘቱ ይህም ተአምራት ነው ፡፡ በሕመማችን ይፈውሰናል ፣ በችግራችን ይረዳናል ፡፡ ምሕረት ግን ለሮጠ ወይም ለቀደመ ሳይሆን ከሚምር ከእግዚአብሔር ነውና በትዕግሥት መጠበቅ ይገባናል ፡፡ የቱንም ያህል ተአምራት ቢደረግልን ከመዳናችን የሚበልጥ አይደለም ፡፡ የመስቀል ላይ ፍቅሩ ዘላለም የምናመሰግንበት ርእስ ነው ፡፡ ዓለምን በጦር ስላስገበረና በአጭሩ ስለተቀጨው ስለታላቁ እስክንድር እንኳ እስከ ዛሬ ይተረካል ፡፡ በፍቅሩ ዓለምን ስላስገበረውና በዙፋኑ ስለ ገነነው ስለ ክርስቶስ እጅግ ሊተረክ ይገባዋል ፡፡ ተአምራት ምልክት ነው ፡፡ መዳረሻ እንጂ መድረሻ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ሥጋችንን ፈውሶ ነፍሳችንን የመተው ዓላማ የለውም ፡፡ ጤነኛ ነፍስ ታማሚ ሥጋን መሸከም ትችላለች ፡፡ ጤነኛ ሥጋ ግን ታማሚ ነፍስን መሸከም አትችልም ፡፡

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።