የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የእመቤታችን ዘላለማዊ ድንግልና

 “ከዚህ በኋላ ከእናቱና ከወንድሞቹ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፥ በዚያም ጥቂት ቀን ኖሩ” /ዮሐ. 2፡12/፡፡
 የእመቤታችንን ዘላለማዊ ድንግልና ሲነሣ እንደ ማፍረሻ ከሚጠቀሱት አንዱ ወንድሞቹ የሚለው ቃል ነው ፡፡ ወንድሞች የተባሉት እነማን መሆናቸውን ባለፉት ትምህርቶች ለመጥቀስ ተሞክሯል ፡፡ በዚህ ክፍል ግን የእመቤታችንን ዘላለማዊ ድንግልና በሚመለከት ሌሎች ጥያቄዎችንና መልሶችን ለማቅረብ እንሞክራለን ፡፡
የእመቤታችን ዘላለማዊ ድንግልና የክርስቶስ ክብር መግለጫ ነው ፡፡ ይኸውም፡-
1-  ከአዳም ኃጢአት ጋር ያልተወለደ ንጹሕ መሆኑን ያሳያል ፡፡ ቤዛ ለመሆንም ንጹሕ መሆን መስፈርት ነው ፡፡
2-  በሰማይና በምድር አባቱ አንድ እግዚአብሔር አብ መሆኑን ያሳያል ፡፡
3-  አምላክነቱን ይገልጣል ፡፡ ድንግልናዊ ልደት መወለድ የሚችል እርሱ ብቻ ነውና ፡፡
4-  ቀዳማዊ አዳምን የተካ ዳግማዊ አዳም መሆኑን ያሳያል ፡፡ አዳም ከድንግል መሬት እንደ ተፈጠረ ጌታችንም ከድንግል ተወልዷልና ፡፡ አዳም የሠላሣ ዓመት ጎበዝ ሁኖ እንደ ተፈጠረ ጌታችንም በሠላሣ ዘመኑ አገልግሎት ጀምሯል ፡፡ አዳም በሠላሳ ዘመን ጉብዝና በልጅነት መዐርግ እንደ ተፈጠረ ፤ ጌታችንም በሠላሣ ዘመኑ ልጅነቱን አስመስክሯል ፡፡
5-  በዝግ መቃብር ከሞት የሚነሣው ፣ በዝግ ቤት ገብቶ ሰላም ለእናንተ ይሁን ለሚለው አምላካዊ ተግባሩ በዝግ ማኅጸን መወለዱ መነሻ ነው ፡፡
 የጌታችንን ድንግልናዊ ልደት አስቀድሞ የተነገረና በዘመናትም እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሰጠው ምልክት ነው ፡፡ አስቀድሞ የተነገረው በአንተና በሴቲቱ መካከል ተብሎ በዘፍ. 3፡15 ላይ ነው ፡፡ አዳም በወደቀ ቀን የተሰማ ድምፅ ነው ፡፡ ምልክት መሆኑንም በኢሳ. 4፡14 ተገልጧል ፡፡ ምልክት ያልተለመደና ከእግዚአብሔር የሆነን ነገር ለመቀበል ማስረጃ ነው ፡፡ ድንግልናዊ ልደት ከእግዚአብሔር የሆነ ለሰዋዊ አእምሮ መቀበል የሚከብድ ነው ፡፡ ለምሳሌ ኢሳ. 7፡14 “ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች” ይላል ፡፡ አይሁዳውያን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ይህ ጥቅስ የተነገረው ለሕዝቅያስ ነው የሚል ትርጉም ሰጥተውታል ፡፡ ይህ ምልክት ግን ለሕዝቅያስ እናት አይሠራም ፡፡ ምክንያቱም የሕዝቅያስ እናት በድንግልና አልወለደችምና ፡፡ ድንግል የሚለውንም ሴት ልጅ ብለው ተርጉመውታል ፡፡ ይህ ከጥንታዊ መጽሐፋቸው ጋር የሚጋጭና ከክርስቶስ ልደት 270 ዓመት ቀደም ብሎ ወደ ጽርዕ ከተተረጎመው ከሰባ ሊቃናት ትርጉም ጋር የሚጋጭ ነበር ፡፡ አይሁድ ስለ ክርስቶስ በድንግልና መወለድ ሲነገር የዚህን ጥቅስ አሳብ ለመቀየር ሙከራ አድርገዋል ፡፡ ከኤርምያስም ከመዝሙራትም ላይ መሢሑን የሚመለከቱ ጥቅሶችን አውጥተዋል ፡፡ ከ100 ዓ.ም እስከ 165 ዓ.ም የነበረው ሰማዕቱ ቅዱስ ጀስቲን ግን ለዚህ መልስ ሰጥቷቸዋል ፡፡ መጻሕፍቶቻችሁ ይህን አያመለክቱም በማለት መልሶላቸዋል፡፡
 ከአይሁድ ቀጥሎ የእመቤታችንን ዘላለማዊ ድንግልና ወይም የጌታችንን ድንግልናዊ ልደት የተቃወሙት ግኖስቲኮች ናቸው ፡፡ እነዚህ ግኖስቲኮች ክርስቶስ እውነተኛ ሥጋ አልነሣም የሚል አመለካከት ነበራቸው ፡፡ ከድንግልም አልተወለደም ፣ ውኃ በቱቦ እንደሚያልፍ አለፈባት ይላሉ ፡፡ ከግኖስቲኮች ቀጥሎ ይህን አሳብ በአቋም ያራመደው በ4ኛው ክፍለ ዘመን የነበረው ሄልቪድየስ ነው ፡፡  በዘመኑ የነበሩ አባቶች በቂ መልስ ሰጥተውታል፡፡ ቅዱስ ጀሮም በብርቱ ተቃውሞታል ፡፡
     የፕሮቴስታንት ተሐድሶ አራማጅ የሆኑት እነ ማርቲን ሉተር እነ ካልቪንም በዘላማዊ ድንግልና ላይ ጥያቄ አልነበራቸውም ፡፡ እንደውም ካልቪንም ሆነ ሉተር የሄልቪድየስን አሳብ ተቃውመዋል ፡፡ ሉተር “የበኩር ልጅዋንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም” የሚለውን የማቴዎስን ወንጌል እስክትወልድ ሲል ከወለደች በኋላ አውቋታል ማለት አይደለም አባባሉ እናንተ ከምታስቡት በተቃራኒው ፍጹም አላወቃትም ማለት ነው” ብሏል ፡፡  ካልቪንም ብዙ ረብሻ የፈጠረውን ይህን ትምህርት ወደ ቤተ ክርስቲያን ያስገባው ሄልቪዲየስ ነው ይላል ፡፡ በመቀጠልም የበዛ ለማወቅ ጉጉት ያለውና መለያየትን የሚናፍቅ ሰው ካልሆነ በዚህ ጉዳይ ግትር ተከራካሪ ሊኖር አይችልም ብሏል፡፡ ብዙ የፕሮቴስታንት ተርጓሚዎችም የዳዊት ትውልድ ክርስቶስ ላይ ስለሚያበቃ ማርያም ጌታን ከወለደች በኋላ ሌላ ልትወልድ አትችልም ይላሉ፡፡ የዓለሙን አዳኝ ስለወለደች ሌላ አልወለደችም የሚል ጠንካራ መከራከሪያ ያነሣሉ ፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ላይ የተነሡ የፕሮቴስታንት እምነት አራማጆች ግን ለልዩነት አሳብ ይጠቀሙታል ፡፡ አንድ ታሪክ ምሁር ፡- ታሪክን የማያነብቡ ሰዎች በታሪክ ውስጥ የተከሰቱትን ስህተቶች ለመድገም የተፈረደባቸው ሰዎች ናቸው” ይላል ፡፡ በዘመናችን አዲስ መገለጥ የሚመስሉ የቆዩ ኑፋቄዎች ናቸው፡፡ “ዓለም አዲስ የምትመስለው ታሪክን አንብቦ ለማያውቅ ሰው ነው “ የሚባለው እውነት ነው ፡፡
ታዲያ ዘላለማዊ ድንግልናን የሚቃወሙ እነዚህ ፕሮቴስታንት ከብዙ ውይይት በኋላ የሚያነሡት  አሳብ ከመዳናችን ጋር ምን የሚያገኛኘው ነገር አለ ? የሚል ነው ፡፡  ሉተርም እንዲህ ብሏል ሲባሉ እኛ የምናምነው መጽሐፍ ቅዱስን ነው የሚል አሳብ ያቀርባሉ ፡፡ ዘላለማዊ ድንግልናን መቀበል ለምን ተቸገሩ ?  እመቤታችን ሌሎች ልጆች ወልዳለች ብለው ጠንክረው ለምን ይከራከራሉ ? ቢባል መውለድ ክብር የሚቀንስ መስሎአቸው ሊሆን ይችላል ፡፡ አለመውለድን እንደ ርግማን የሚመለከቱ እነዚህ ሰዎች መውለድን እንደ ክብር ማሳነሻ መጠቀማቸው ተገቢ አይደለም ፡፡ እመቤታችን ከጌታ ሌላ መውለድ ያልተሰጣት ሁኖ እንጂ ክብረ ነክ አይደለም፡፡ ሙሴ ከተራራው በወረደ ጊዜ ብርሃን የተሣለበት በአምላክ ፊት ስለቆመ ነው ፡፡ በአምላክ ፊት መቆም ይህን ያህል ክብር ካለው አምላክን መውለድ ክብሩ ከፍ ያለ ነው ፡፡ አሁንም የአባቶችን ቃል እንደግማለን ፡- “በአምላክ ዙፋን ፍጡር አይቀመጥም” ማኅጸነ ማርያም የአምላክ ዙፋን ነው፡፡
ከዓለም አቀፍ ጉባዔዎች ከኒቅያ ጉባዔ መግለጫ የሚቀበሉት ፕሮቴስታንት “ስለ እኛ ስለ ሰዎች እኛንም ለማዳን ከሰማይ ወረደ ፤ በመንፈስ ቅዱስ ግብር ከቅድስት ድንግል ማርያም ፍጹም ሰው ሆነ ” የሚለውን በትክክል አስበውበታል ወይ ?
 ቅዱስ አግናጥዮስ ዘአንጾኪያ /50-110 ዓ.ም/ በአዋጅ ሊነገሩ የሚገባቸው ሦስት ምሥጢራት አሉ ፡፡ እነዚህ ግን ከዚህ ዓለም ገዥ የተሰወሩ ናቸው እነርሱም ፡-
1-  የማርያም ድንግልና
2-  በድንግልና መውለዷ
3-  የጌታ ሞት ነው ይላል ፡፡
   ዘላለማዊ ድንግልናን መቀበል አለመቻል አሁን እያደገ መጥቶ ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ ልትባል አይገባትም ወደሚል አስተሳሰብ ወደ ንስጥሮስ ክህደት ደርሷል ፡፡
ሄልቪድየስ ፡- “የበኩር ልጅዋንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም”  የሚለውን በመጥቀስ ተከራክሯል ፡፡
–    በኩር
–    እስከ
–    አላወቃትም
– ወንድሞች የሚለውን ቃል በመጥቀስ ዘላለማዊ ድንግል አይደለችም ይላል፡፡
በኩር ፡-
በኩር የሚለው ቃል ተከታይን ያመለክታል የሚል አሳብ ይዞ የተነሣውን ሄልቪድየስን ቅዱስ ጀሮም ይመልስለታል ፡- “ብቸኛ ልጅ በኩር ነው ፤ በኩር ሁሉ ግን ብቸኛ ልጅ ላይሆን ይችላል ፡፡ በኩር ማለት ከእርሱ ቀጥሎ ተወልዷል ማለት ሳይሆን ከእርሱ በፊት የተወለደ የለም ማለት ነው” ብሏል፡ ቅዱስ ጀሮም በመቀጠል ፡- እግዚአብሔር የግብጽ በኩር ሲመታ ተከታይ ያላቸውን እየለየ ነበር ወይ የመታው ? የሚል ጥያቄ ያቀርባል ፡፡ እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ፡- “በእስራኤል ልጆች ዘንድ ከሰውም ከእንስሳም ማሕፀንን የሚከፈት በኵር ሁሉ ለእኔ ቀድስልኝ የእኔ ነው” ብሏል /ዘጸ. 13፡2/፡፡ እነዚህ በኩሮች ተከታይ ላይኖራቸው ይችላል ፡፡ ጀሮም አሁን በኩር የሚለውን ቃል የክህነት መዐርግ ነው ይላል ፡፡ ለዚህም የሚጠቅሰው ከሙሴ በፊት የቤቱ በኩር እንደ ካህን ይታያል በማለት ነው ፡፡ ጌታችን ኢየሱስም ሊቀ ካህናት ነውና በኩር መባሉ ክህነቱንም ለመግለጥ ነው ይላል ጀሮም /ዕብ. 4፡14/ ፡፡
አንድ ፀሐፊ ፡- “አንድ አዲስ መጽሐፍ ስታነቡ ሦስት የቆዩ መጻሕፍትን ማንበብ አለባችሁ” ይላል ፡፡ አንድ አዲስ አሳብ ሲመጣ ከዚህ በፊት ተብሏል ወይ ? የቀደሙት አባቶች ለሐዋርያት ዘመን ቅርብ የነበሩት እንዴት ነው የተረዱት ? ማለት ያስፈልጋል ፡፡ በኩር የሚለውንም ቃል የቀደሙት አባቶች እንዴት እንደ ተረዱት ማጤን ያስፈልጋል ፡፡
እስክትወልድ ፡-
 እስከ የሚለውን ቃል በመጥቀስ ከወለደች በኋላ አውቋታል የሚል አሳብ ሔልቪዲየስ አቅርቧል ፡፡ ይህን አሳብ ዛሬም ያሉ ወገኖች ያነሣሉ ፡፡ እስከ የሚለው ቃል ግን ይህን ያመለክታል ወይ ? ለምሳሌ፡-
–    “የሳኦልም ልጅ ሜልኮል እስከ ሞተችበት ቀን ድረስ ልጅ አልወለደችም” ይላል /2ሳሙ. 6፡23/ ፡፡ ሜልኮል ከሞተች በኋላ ወልዳለች ማለት አይደለም ፡፡
–    “እግዚአብሔር ጌታዬን፦ ጠላቶችህን ለእግርህ መቀመጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው” ይላል /መዝ. 109፡1/ ፡፡ ለክርስቶስ የተነገረ ነው ፡፡ ጠላቶቹ ድል ከተነሡ በኋላ ከቀኙ ይነሣል ማለት ነው? አይደለም ፡፡ እስከ ዘላለም ማለት ነው ፡፡ እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም ማለትም እስከ ዘላለም አላወቃትም ማለት ነው ፡፡
–    “እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” /ማቴ. 28፡20/፡፡ ከዚያ በኋላ ይለየናል ማለት ነው ? አይደለም ፡፡
 ከወለደች በኋላ አውቋታል የሚል አስተሳሰብ መያዝ ከባድ ነው ፡፡ ብዙ ምልክቶችን ካየ በኋላ ዮሴፍ ይቀርባታል ማለት ተገቢ አይደለም ፡፡ ቅዱስ ዮሴፍ ትንቢቶችን በደንብ ያስተዋለ የኢሳይያስን ትንቢት ፍጻሜ በዓይኑ ያየ ነው ፡፡ አይሁድ ያለ ወንድ የፀነሰች ሴት ትወገር ይላሉና ሕይወቷን ከሞት ለመታደግ እንደ መጋረጃ ነበር ፡፡ አንዲት ሴት ስትዳር አደራ የሚሰጠው ከወላጆች ነው ፡፡ ድንግል ማርያምን በሚመለከት ግን ዮሴፍ የጠባቂነት አደራ የተቀበለው በቀጥታ ከእግዚአብሔር ነው ፡፡ “ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ” ተብሏል ፡፡ በተመሳሳይ መንገድም ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ ለዮሐንስ አደራ ሰጥቷታል ፡፡ ይህን አሳብ በደንብ የሚገልጠው ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ ነው ፡፡ ዮሐንስ አፈ ወርቅ አደራው ጋብቻ ለመፈጸም ሳይሆን ጠባቂ ለመሆን ነው ይላል ፡፡
“እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም” የሚለው ቃል ከወለደች በኋላ አውቋታል የሚል ትርጉም ለምን አመጣ ? እንደውም ከመውለዷ በፊት እጮኛ የሚለው ከወለደች በኋላ ግን በፍጹም አይልም ፡፡ ለዚህም የግብጽ ስደት ሲመጣና ከግብጽ ስደት በኋላ ለዮሴፍ የተነገረውን ማሰብ እንችላለን ፡-
–               “እነርሱም ከሄዱ በኋላ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ፡- ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፥ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ አለው” ይላል /ማቴ. 2፡13/ ፡፡ ሕጻኑንና ሚስትህን አላለም ፡፡ የድንግል ማርያም ግንኙነት ከልጇ ጋር ብቻ ነውና ፡፡ ይህ ጊዜ ጌታችን ከተወለደ ሁለት ዓመት የሞላው ጊዜ ነው ፡፡ እስከ ሁለት ዓመት ታዲያ እንዴት የእነ ሔልቪድየስ አሳብ አልተፈጸመም ፡፡ ለድንግል ማርያም ያልተሰጣት ስለሆነ ብቻ ነው ፡፡
–    “እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በሌሊት ያዘና ከጌታ ዘንድ…” /ማቴ. 2፡14/፡፡
–    “የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑን እናቱንም ይዘህ ወደ እስራኤል አገር ሂድ አለ” ይላል /ማቴ. 2፡20/፡፡ ይህ ጊዜ ደግሞ ጌታ የአምስት ዓመት ሕጻን የነበረበት ጊዜ ነው ፡፡ ከአምስት በኋላ ድንግል ማርያም ግንኙነቷ ከዮሴፍ ጋር ሳይሆን ከልጇ ጋር ብቻ ነው፡፡
 እነዚህ የቀደሙት አባቶች ስለ እመቤታችን ዘላለማዊ ድንግልና የሚጠቅሱት ሕዝ. 44፡1 ነው ፡፡ ቃሉ ፡- ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በስተ ውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አመጣኝ ተዘግቶም ነበር። እግዚአብሔርም፦ ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም፥ ሰውም አይገባበትም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል” ይላል ፡፡ ይህ ክፍል ስለ እመቤታችን ዘላለማዊ ድንግልና የተነገረ መሆኑን ቅዱስ አምብሮስ ፣ ቅዱስ አውግስጢኖስ ፣ ቅዱስ ጀሮም አበክረው ተናግረዋል ፡-
–               ቅዱስ አምብሮስ ፡- “ማርያም ካልሆነች ይህ በር ማነው? ድንግል በመሆኗ የተዘጋ አይደለምን? ክርስቶስ ወደ ዓለም የገባበት በር ማርያም ናት ፡፡ በድንግልና ሲወለድ መወለዱ የድንግልናዋን ማኅተም አላጠፋውም፡፡”
–            ቅዱስ አውግስጢኖስ ፡- ተዘግቶ የሚኖር የቤተ መቅደስ በር ምንድነው? ማርያም ለዘላለም ከነ ክብራ ትኖራለች ማለት ካልሆነ! ሰው አይገባበትም ማለትስ ምንድነው ? ዮሴፍ አያውቃትም ካልሆነ፡፡ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታል ማለትስ ምንድነው? ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳለች ከእርሷ የሚወለደው የመላእክት ጌታ ካልሆነ፡፡ ለዘላለም ተዘግቶ ይኖራል ማለትስ ምንድነው ? ማርያም ከመውለዷ በፊት በወለደች ጊዜ ከወለደችም በኋላ ድንግል ናት ማለት ካልሆነ ፡፡”
ሕዝቅኤል 44ን የሚተረጉሙ ሊቃውንት ስለ ብሉይ ኪዳኗ ቅድስተ ቅዱሳን ያነሣሉ ፡፡ በቅድስተ ቅዱሳን ከሊቀ ካህኑ በቀር ማንም አይገባም ፡፡ የመጀመሪያው ዘመን ክርስቲያኖች የድንግል ማርያምን ማኅጸን እንደ ቅድስተ ቅዱሳን ያስቡ ነበር ፡፡ ምሳሌ የሚሆነው የኪዳን ማደሪያ ውስጥ መግባት ከተከለከለ አማናዊ ቃለ እግዚአብሔር የሆነው ወልድ ያደረበት ማኅጸን ውስጥ ፍጡር ያድራል ማለት ተገቢ አይደለም ፡፡ እስከ ጋብቻ በድንግልና መቆየት የተሣነው ትውልድ ዘላለማዊ ድንግልናን መቀበል ቢከብደው የሚገርም አይደለም ፡፡ ለፍትወተ ሥጋ የተሰጠ ትውልድ ይህን መቀበል እንደሚቸግረው ብዙዎች ተናግረዋል ፡፡
 ሕዝቅኤል 44 ስለ እመቤታችን የሚናገር አይደለም የሚሉ ወገኖች የሚያነሡት ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም በክብር የገባበት በርን የሚያመለክት ነው ይላሉ ፡፡ ነገር ግን የመቅደሱ በርና የኢየሩሳሌም በር ልዩነት አለው ፡፡ ለዚህም ማያያዣ የሚያደርጉት የቱርክ ገዢዎች በ1560 ዓ.ም በምሥራቅ በኩል ያለውን የኢየሩሳሌም በር ዘግተውታል ፡፡ መሢሑ የሚገባበት በር ነው ተብሎ ስለሚታሰብ እንዳይገባ ለመከልከል ነው ፡፡ ይህ የኢየሩሳሌም ምሥራቃዊ በር ለ500 ዓመታት ያህል እንደ ተዘጋ ነው ፡፡ ከሕዝቅኤል ትንቢት ጋር ግን ግንኙነት የለውም ፡፡
ወንድሞች ፡-
 የጌታ ወንድሞች የተባሉት እነማን መሆናቸውን ባለፉት ጽሑፎች ደጋግመን ለማየት ሞክረናል ፡፡ የጌታ ወንድሞች የተባሉት የቅርብ የሥጋ ዘመዶች ናቸው ፡፡ በአይሁዳውያን ባሕል የቅርብ የሥጋ ዘመዶች ወንድም መባላቸው የተለመደ ነው ፡፡ አብርሃምና ሎጥ ወንድም ተብለዋል /ዘፍ. 13፡8/፡፡ አጎቱን ወንድም ብሎ ይጠራዋል ፡፡ ይህን የመሰለ ሩት .4፡3፤ 2ሳሙ. 20፡9 ተመልከቱ ፡፡ እመቤታችን ከጌታ ሌላ ልጅ አልወለደችም ፡፡
1-  እመቤታችን ከጌታችን ሌላ ሌሎች ልጆች ቢኖሯት ኑሮ በመስቀል ላይ ሳለ ለዮሐንስ አደራ አይሰጣትም ነበር ፡፡ አርጌንስ የተባለ ሊቅ ፡- “እነሆ ልጅሽ አላት እንጂ ይህ ሰው ልጅሽ ነው አላላትም ፡፡ ላንቺ እርሱ ኢየሱስ ነው ፡፡ እኔ ማለት ነው” የሚል ገለጻ ሰጥቷል ፡፡ ተጨማሪ ልጅ እየሰጣት አይደለም ፡፡ በዮሐንስ ልዩ ቅርበት ራሱን እየተካላት ነው ፡፡ ለምን ? ስንል ለድንግል ማርያም ሁለተኛ ልጅ እንዳይታሰብ ነው ፡፡
  2-  ወንድሞች የተባሉት በትክክል ወንድሞች ከሆኑ ታናናሽ ወንድሞች ናቸው ማለት ነው ፡፡ እነዚህ ታናናሽ ወንድሞች ጌታን በአደባባይ ገስጸዋል /ዮሐ. 7፡2/ ፡፡ በአይሁድ ባህል ታናናሾች ታላቅ ወንድማቸውን በአደባባይ አይገስጹም ፣ አይመክሩም ፡፡ ወንድሞች መባላቸው ታናናሾች አለመሆናቸውን የሚያሳይ ነው ፡፡ ስለዚህ የድንግል ማርያም ልጆች አይደሉም ፡፡ እነዚህ ወንድሞች የተባሉ አንድም ቦታ የእመቤታችን ወይም የዮሴፍ ልጆች ተብለው ተጠቅሰው አናነብም ፡፡ ከእመቤታችን ጋር ተገናኝተው ሲነገር አናነብም ፡፡
 እመቤታችን ድንግል ማርያምስ ምን ትላለች? መልአኩ ገብርኤል ባበሰራት ጊዜ ትፀንሻለሽ ሲላት “ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል? አለችው” /ሉቃ. 1፡34/፡፡ ፀንሰሻል ሳይሆን ወደፊት እንደምትፀንስ ነው የነገራት ፡፡ በድንግልና ለመኖር አሳቡ ባይኖራት ወንድ ሳላውቅ የሚል መልስ አትሰጥም ነበር ፡፡ በዚያ ላይ ታጭታለች ፡፡ ፅንስ እንዴት እንደሚፀነስ አይደለም የጠየቀችው ፡፡ የምትጠይቀውን ታውቃለች ፡፡ በድንግልና የመጽናት አሳቧን እየገለጠች ነው ፡፡ የእመቤታችንን ዘላለማዊ ድንግልና የቀደሙት ቅዱሳንና ሊቃውንት አባቶች ሁሉ የተቀበሉት ሲሆን ሄልቪድየስ ግን ከየት እንዳመጣው አይታወቅም ፡፡ በአምላክ ዙፋን ፍጡር አይቀመጥም ፡፡

ያጋሩ