የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የዮሐንስ ወንጌል ትርጓሜ / 1

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ሰኞ ጥር 23/2008 ዓ.ም

    መቅድም

 ከአራቱ ወንጌላት የዮሐንስ ወንጌል በበጋ ይመሰላል። በጋ ደረቅ ነው፣ የዮሐንስ ወንጌልም ደረቅ እውነት ነው። በጋ የመኸር ወቅት ነው፣ የዮሐንስ ወንጌልም ስለዘላለም ሕይወት የሚናገር ነው። በጋ የደረቡትን ያስወልቃል፣ የዮሐንስ ወንጌልም የራስን አስተሳሰብ ያስጥላል። በጋ ለአዝመራ መዘጋጃ ነው፣ የዮሐንስ ወንጌልም የምስክርነት ኃይል ነው። በጋ የሠርግ ጊዜ ነው፣ የዮሐንስ ወንጌልም ለበጉ ሠርግ የሚያዘጋጅ ነው። በጋ ጭጋግ የለውም፣ የዮሐንስ ወንጌልም ግልጽ ትምህርት ነው። በጋ ዘሩን ሊጎዱ የሚችሉ ነፍሳትን የሚገድል ነው፣ የዮሐንስ ወንጌልም የስህተት ትምህርቶችን፣ ጤናማውን ቃል የሚጎዱትን ድል የሚነሣ ነው።

የዮሐንስ ወንጌል ከአራቱ እንስሶች ወይም ከኪሩቤል በገጸ ንስር ይመሰላል /ራእ. 4፡7/። ንስር በከፍታ ሆኖ ጥልቀትን ያያል፣ ዮሐንስም ቅድመ ዓለም የነበረውን የወልድን አኗኗር ይገልጣል /ዮሐ. 1፡1/።

     ሕጻናት መልእክተ ዮሐንስን ንባብ እንዲማሩበት መመረጡ በጣም አስደናቂ ነው። የቀደሙት አባቶች እስከ ዛሬ የዮሐንስ ወንጌልን በየዕለቱ ከማንበብ ባሻገር ይጸልዩታል።  የዮሐንስ ወንጌል በራሱ ምሥጢራትን ለማክበር ዙፋን ሆኖ ያገለግላል። ይህን ስናይ የዮሐንስ ወንጌል በአገራችን ከፍ ያለ ክብር እንዳለው እንረዳለን።

የዮሐንስ ወንጌል ከሌሎቹ ወንጌላት ለየት የሚያደርገው የጌታችንን ትምህርት በስፋት በመያዙ ነው። ምሳሌዎችንንና ተአምራትን ብዙ አይጽፍም። የጌታችንን ትምህርት በቀጥታ ያስተላልፋል። ሌሎቹ ወንጌላት የጌታችንን የሥጋ ልደት ሲዘግቡ ዮሐንስ ግን ከአብ የተወለደበትን የማይመረመር ልደት በመግለጽ ይጀምራል። የዮሐንስ ወንጌል ስለ እውነትና ሕይወት በግልጽነት ይናገራል።

ጌታችን በአይሁድ በተያዘ ጊዜ ሌሎቹ ወንጌላውያን ክስተቱን እንጂ ትምህርቱን ብዙ አልዘገቡም። ዮሐንስ ግን ከምዕ. 13 ጀምሮ እስከ መጨረሻው የዘገበው ከሐሙስ ማታ እስከ ዕርገት ያለውን ነው። ይህን ለመተረክ ጽናት ያስፈልጋል። ጌታን የሚያህል ወዳጅ በሚያዝበት ምሽት ትምህርቱን ማስቀረት ትልቅ ብርታት ነው። ዮሐንስ እስከ መስቀል ድረስ ተጉዟል። እመቤታችንን ወደ ቤቱ ይዞ ሲመለስም አይሁድና ሮማውያን፣ መላው ዓለም ማለት ይቻላል ተባብሮ የሰቀለውን የኢየሱስን እናት ይዞ በመግባት የሚመጣውን ጫና አልፈራም። ዮሐንስ ወንጌልን እርስዎስ እንዴት ተረድተውታል?
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ