የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የዮሐንስ ወንጌል ትርጓሜ / 13

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ማክሰኞ የካቲት 8/2008 ዓ.ም.
በኩነት ስሙ ቃል መባሉ

ወንጌላዊው ዮሐንስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በኩነት ስሙ ቃል ብሎ መጥራቱ ምሥጢረ ሥላሴን የሚያብራራ ነው /ዮሐ. 1፡1/። እያንዳንዱ የሥላሴ አካል በክበበ ሥላሴ ውስጥ የሚሠራው ባሕርያዊ ግብር አለ። ወልድ በክበበ ሥላሴ ምን ሆኖ ነው በዚያ ክበብ ውስጥ ያለው? ስንል ቃል ሆኖ ነው። ወልድ ቃል ተብሎ መገለጡ ሁለት ነገሮችን ያሳየናል። ወልድ ቃል ሆኖ ከኖረ አብ ምን ሆኖ ነው የኖረው? ብለን እንድንጠይቅ ይገፋፋናል። ወልድ ራሱ፡- ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤”  ብሏል /ዮሐ. 16፡28/። ቃል ከልብ ይወጣልና። በሌላ ስፍራም፡- “በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራልና”ይላል /ማቴ. 12፡34/። ስለዚህ የአብ ኩነት ልብ መሆን ነው። በክበበ ሥላሴ ውስጥ የመንፈስ ቅዱስ ኩነት ምንድነው? ስንል ሕይወት ወይም እስትንፋስ መሆን ነው። መንፈስ ቅዱስ በሕይወትነት የወጣው ከማን ነው? ስንል ከአብ ነው። ጠቢቡ፡- “አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፥ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና” ይላል /ምሳ. 4፡23/። ስለዚህ ሕይወት የሆነው መንፈስ ቅዱስ ልብ ከሆነው ከአብ ወጥቷል። በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ይሠርጻል ይላሉ። ይህ ኩነትን ያፈርሳል። በሕይወት ከዊን የሚታወቀው መንፈስ ቅዱስ፣ በልብ ከዊን ከሚታወቀው ከአብ ይሠርጻል። ይህንንም ራሱ ጌታችን፡- “ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤”ብሏል /ዮሐ. 15፡26/። ቅዱስ ጴጥሮስም፡- “ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን የተስፋ ቃል ከአብ ተቀብሎ ይህን እናንተ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው” ብሏል /የሐዋ. 2፡33/። መንፈስ ቅዱስም ከአብ የሚሠርጽ የእውነት መንፈስ ነው። መሥረጽ ማለት መውጣት ማለት ነው። በአንድ ተክል ላይ እንደሚወጣ ቡቃያ ማለት ነው።

የሥላሴን አንድነት የሚያመለክት አንድ ልብ፣ አንድ ቃልና አንድ እስትንፋስ መሆን ነው። ሦስት መለኮት ብሎ የሚያምን እያንዳንዱ አካል የራሱ ሆነ ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ እንዳለው የሚያስብ ነው። በዘዳ. 6፡4 ላይ፡- “እስራኤል ሆይ፥ ስማ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው” ይላል። አምላክ ማለት በዕብራይስጡ ኤል የሚለው ሲሆን በብዛት ኤሎሂም ይለዋል። እግዚአብሔር “ኤሎሂም ያህዌ” ነው። ኤሎሂምን አይተው ብዙ አማልክትን እንዳያስቡ “አንድ እግዚአብሔር ነው” የሚለው ማስጠንቀቂያ ሆኖ ተሰጣቸው። ሦስት አካላት አንድ አምላክ ብለን እናምናለን።

ቃል የወልድ የኩነት ስሙ ነው ብለናል። ይህን የኩነት ስም ወንጌላዊው መጠቀሙ በሥላሴ አካላት መካከል መቀዳደም እንደሌለ ያመለክታል። ልብ፣ ቃልና እስትንፋስ ያለመቀዳደም ይኖራሉ። ልብ የሚያስበው ቃላት በኅሊና ሲዋቀሩ ነው። ቃላት ካልተዋቀሩ አሳብ የለም። አሳብና ቃላት የሚኖሩት ደግሞ እስትንፋስ ሲኖር ነው። ስለዚህ ልብ፣ ቃልና እስትንፋስ ያለመቀዳደም ያለመለያየት ይኖራሉ። እንዲሁም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ያለመቀዳደም ያለመለያየት ይኖራሉ።

ወንጌላዊው ዮሐንስ የወልድን ዘላለማዊነት ለመግለጥ ቃል በማለት መጥቀሱ ይደንቃል። አብ ከዘላለም አባት ከሆነ፣ አባት መባሉም ከዘላለም ከሆነ ልጅ በሌለበት አባት መባል የለምና ወልድም ዘላለማዊ ነው። ልደቱ ከዘላለም የሆነው ልጅ አብን አባት አሰኝቶታል። ይህንን ነቢዩ ሚክያስ ሲገልጥ፡- “አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ፥በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል” ይላል /ሚክ. 5፡2/። አወጣጡ የሚለው ቃልን ወይም ወልድን የሚያመለክት ነው። ጌታችንም “ከአብ ወጥቼ” ብሏል /ዮሐ. 16፡28/። መውጣት ልደትን አመልካች ነው። የወልድን ዘላለማዊነት ኢሳይያስም ሲገልጥ፡- “ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል” ይላል /ኢሳ. 9፡6/። ለወልድ ከተሰጡ ስያሜዎች አንዱ “የዘላለም አባት” የሚል ነው። የዕብራውያን ፀሐፊም፡- “ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው”ይላል /ዕብ. 13፡8/። ትላንት ሲል ሰው ከመሆኑ በፊት ያለውን ሲያመለክት፣ ዛሬ የሚለው ደግሞ ሥጋዌን፣ ለዘላለም ሲል ፍጻሜ የለሽነትን ያመለክታል። ራሱ ጌታችንም፡- “አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ”  ብሏል /ዮሐ. 17፡5/። ዓለም ሳይፈጠር ከአብ ጋር የሚጋራው ክብር ነበረው።

ሰው በመሆኑ አየነው። እርሱ ግን ሁሉን የፈጠረ ነው /ዮሐ. 1፡3/። ይህ ቃል የተባለው ወልድ የባሕርዩ ክፍል እንጂ የተፈጠረ መሣሪያ አይደለም። አርዮስ ቃል የተባለውን አብ ሠራና በእርሱ ፍጥረትን አመረተበት አለ። የተናገረበትና ሁሉ የሆነበት ወልድ ግን የአብ ቃሉ ነው። የባሕርይ ልጁ ነው። አብ ቃልን አልፈጠረውም። ይህ ወልድ ክብር ይግባውና በብሉይ ኪዳንም እስራኤልን የመራ ለአፍታ ከሕዝቡ ያልተለየ ነው። እርሱን ዘላለማዊ ልጅ ማለት አብን ዘላለማዊ አባት ማለት ነው።

ክብር ለሥላሴ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ