የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

“ሁሉ በእርሱ ሆነ”

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ዓርብ የካቲት 18/2008 ዓ.ም.
 ወንጌላዊው ዮሐንስ፡- “ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም” ይላል /ዮሐ. 1፡3/። ልብን የሚያሳርፍ ቃል ነው። ሁሉ በእኛ፣ ሁሉ በሰው የሚሆን እየመሰለን ለደከምን ትልቅ መልስ ነው። የሁሉም ነገር ጥያቄ መልስ ቢኖረውም አይነገረንም። ሁሉ በእርሱ እንደሚሆን ስናስብ ግን እግዚአብሔር ያውቃል ብለን ማረፍ ይሆንልናል። የእኛ ማወቅማ ያውከናል፣ ለምን? እንዴት? እያለ እንቅልፍ ያሳጣናል። የእግዚአብሔር እውቀት ግን መለኮታዊ ቻይነት አለው። ያወቅነውን ሳንሞላ አዲስ ለማወቅ፣ የደረስንበትን ጉዳይ ሳንፈታ ሌላ ለመስማት እንናፍቃለን። እርሱ ግን በእውቀቱ እንዲያሳርፈን መጸለይ ይገባናል። “ሁሉ” ተብሎ የሚጠቀስ ለእግዚአብሔር ብቻ ነው። ሁሉን ቻይነት፣ ሁሉን አዋቂነት፣ ሁሉን ፈጻሚነት የመለኮት ባሕርይ ነው። ሁሉን ችሎ ትዕግሥተኛ፣ ሁሉን አውቆ ጉድን ሸፋኝ፣ ሁሉን ፈጽሞ ትሑት አማኑኤል ብቻ ነው። ሁሉን ስላልቻልን እግዚአብሔር ይመስገን። ሁሉን ብንችል ኖሮ ዓለም ያለ ጊዜዋ ታልፍ ነበር። ሁሉን ብናውቅ ኖሮ ሁላችንም አንድ አንድ የሬድዮ ጣቢያ እናቋቁም ነበር። ሁሉን ብንፈጽም በትዕቢት እንፈነዳ ነበር። ሁሉን አለመቻልን ጸጋ አድርጎ የሰጠን እግዚአብሔር ይመስገን።
ሁሉ በርሱ ሆነ ለሁሉም ጥያቄዎቻችን መልስ ነው።
·       “ሁሉ በእርሱ ሆነ”  ሁሉ በእርሱ ከሆነ ራሱን ያስገኘ የለም።
·       ሁሉ በእርሱ ከሆነ የሁሉ ነገር ምስጋና ወራሽ እርሱ ነው።
·       ሁሉ በእርሱ ከሆነ የእርሱን ፈቃድና አቅም አምልጦ በእኛ ሕይወት ላይ የመጣ ምንም ነገር የለም።
·       ሁሉ በርሱ ከሆነ ዘላለማችን ያለው በእርሱ ውስጥ ነው።
 ሁሉ በእርሱ ሆነ የሚያጽናና፣ የሚያረጋጋ፣ መልስ ላጣንላቸው ጉዳዮች የተሟላ መልስን የሚሰጥ ነው። በእርግጥ እግዚአብሔር ጥያቄ ስናቀርብለት ለጥያቄአችን ዝርዝር መልስ አይሰጠንም። ለጥያቄአችን ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ሙሉ መልስ ነው። እርሱ ወደዚህ ዓለም የመጣው ለጊዜያዊና ለዘላለማዊ ጥያቄዎቻችን ዝርዝር መልስ ለመስጠት አይደለም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣው መልስ ለመሆን ነው። ዛሬም ብዙ ጥያቄዎች አሉ። ምዕራባውያን ብዙ ጥያቄዎች አሉባቸው፣ ምሥራቃውያን   ብዙ ጥያቄዎች አሉባቸው፣ አፍሪካውያን ብዙ ጥያቄዎች አሉባቸው። ይልቁንም አፍሪካ ብዙ ጥያቄ አለባት። የአፍሪካ ካርታውን ስንመለከተው ራሱ የጥያቄ ምልክት ነው። መልሱ ግን ምዕራባውያን አይደሉም። መልሱ ፈረንጆች አይደሉም። መልሱ የተሰቀለው ጌታ ክርስቶስ ነው።
“ሁሉ በእርሱ ሆነ”
     ሁሉ በእርሱ ከሆነ  ሁሉም የሚሆነው በእርሱ ነው። የሆነውን ካመንን የሚሆነው አያስፈራንም። ሁሉ በእርሱ ከሆነ ራሱን በዝግመት ያሳደገ ምንም ነገር የለም። እግዚአብሔር በተራ ፈጥሯል እንጂ በተራ ያደገ ፍጥረት የለም። እርሱ የእቅድ አምላክ ስለሆነ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ ሁሉን በእቅድ ፈጥሯል። ራሱን የፈጠረ ራሱን አሳድጎ አሁን ላለበት ማንነት ያበቃ ፍጥረት የለም። ሁሉ በእርሱ ሆነ። ይቺን ዓለም አዋቂ ነን፣ ጠበብት ነን የሚሉ ባል አልቦ አደረጓት። በአገራችን ባለአልቦ የሚባል ጌጥ ነበረ። ባለ አልቦ፣ ባል የለሽ፣ ባለቤት የለሽ፣ መሪ የለሽ፣ ፈጣሪ የለሽ መሆን ነው። ፈጣሪ ከሌለ፣ መሪ ከሌለ፣ በጎ መሥራት ምን ይሠራል? ክፉ መሥራት ለምን ያስፈራል? ሚዛን ያለው ሕይወት የምንኖረው ይህች ዓለም ባለቤት እንዳላት ስንቀበል ብቻ ነው። ሥራችን የሚዳኝ መሆኑን ስናምን ብቻ ነው በጎ ሥራ የምንሠራው።
“ሁሉ በእርሱ ሆነ”
     በእውነት ለብዙ ወገኖቻችን ይህ ቃል መልስ ነው። እግዚአብሔር የማያውቀው ነገር በሕይወቴ ላይ አልሆነም። የእርሱን አቅም አምልጦ፣ ፈንድቶ ወደ እኔ የመጣ ነገር የለም። እግዚአብሔር በሚያውቀው ነገር እኔ ዋስትና አለኝ። ነገሩ ቢታመም ይፈወሳል፣ ቢሞት ይነሣል፣ ቢጠፋ ይካሣል። የእግዚአብሔር እውቀት ዋስትናችን ነው።
ወታደር ለምንድነው አስፈቅዶ የሚወጣው? የአለቃው እውቀት የእርሱ ዋስትናው ስለሆነ ነው። በደረሰበት ቦታ ላይ እንዲህ ሆንኩኝ ቢል በታወቀ ቦታ ስለሚሄድ ኃይል ይደርስለታል። ልጆች ለወላጆቻቸው አስፈቅደው የሚሄዱት የወላጆቻቸው እውቀት ዋስትና ስለሚሆናቸው ነው። ያላስፈቀዱ ልጆች በጉዳታቸው ጊዜ ወላጆቻቸውን አይጠሩም። መንገደኛ ነው የሚረዳቸው። ወይም ጉዳታቸው ሳይድን ጉዳታቸው ሳይጠገን የፍቅር ረዳት ሳያገኝ ይቀራል። የእግዚአብሔር እውቀት ዋስትናችን ነው።
     ጉዳታችንን ሁሉ፣ ችግራችንን ሁሉ፣ ስብራታችንን ሁሉ፣ ጥያቄያችንን ሁሉ፣ ጉድለታችንን ሁሉ፣ ሰንሰለታማ ችግራችን ሁሉ እርሱ ያውቀዋል። አዎ ለነገሮች ሁሉ መሆንን እርሱ ሰጣቸው። ለነገሮች ሁሉ የሚታየውና የማይታየው ፍጥረት አስኋኙ እርሱ ቃል የተባለው እግዚአብሔር ወልድ ነው።
 ሆነ የሚለው ጊዜና ክስተትን ነው የሚያመለክተው። ሆነ የሚለው ጊዜን እንደገና ደግሞ አንድ ክስተትን ያመለክታል። እርሱ ቃል የተባለው ወልድ ያልሆነ ነው። ለእኛ መሆን፣ ለፍጥረት መሆን ግን መነሻ ነው። ስለዚህ የሁነት ባለቤት ነው ማለት ነው። የመሆን መነሻ እርሱ ነው። “ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም”/ዮሐ. 1፡3/።  ቅንጣት ፍጥረት እንኳ ራሱን ወደዚህ ዓለም አልጋበዘም። ይህ ዓለም ትልቅ ግብዣ ነው። ወደዚህ ትልቅ ግብዣ ሰማይን ና ብሎ የጠራው፣ ምድርን ነይ ብሎ የጠራው፣ ሰውን ና ብሎ የጠራው እርሱ ወልድ ነው። ስለዚህ ወደዚህ ዓለም የመጣችሁት በስህተት አይደለም። በወላጆቻችሁ እቅድም አይደለም። አምላካዊ ጥሪ ደርሷችሁ ነው። መፈጠር መጠራት የሚል ትርጉም አለው /ሮሜ. 8፡29/።
 ሁሉ ባንተ ነው።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ