የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ከእግዚአብሔር የተላከ

“ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ”
/ዮሐ. 1፡6/፡፡
 እግዚአብሔር የሚልክ አምላክ ነው /ኢሳ. 6፡8/፡፡ መልእክተኛም የተላከበትን ሳይጨምር ሳይቀንስ የሚያደርስ አድራሽ እንጂ ባለ ጉዳይ አይደለም፡፡ ባለ ጉዳዩ መልእክቱን እኔ ብሎ የላከው ነው፡፡ ብዙ ዓይነት መልእክተኞች አሉ፡-
1- ራሳቸውን የላኩ አሉ
 የእግዚአብሔር መድረክ ነጻ አደባባይ ሆኗል፡፡ ውስጣዊ ጭቆና ያለበት ሰው አደባባይን እንደ ተራበ ይኖራል፡፡ በሚያገኘው አጋጣሚ ሁሉ ራሱን መግለጥ ይፈልጋል፡፡ ነጻ ቦታ  ሲፈልግ የእግዚአብሔርን ቤት ያገኛል፡፡ ዛሬ የእግዚአብሔር ቤት ከእውነት ይልቅ ይሉኝታ የሚያዝበት ስለሆነ ደፋር ሲሰየምበት ማን ነህ? ተው አይባልም፡፡ እነዚህ ሰዎች ክፍት በር ሲያገኙ ቤተ ክርስቲያንን አግኝተው የገቡ፣ እኔ ከእገሌ በምን አንሳለሁ ብለው ቁመት ተለካክተው የተሰየሙ ናቸው፡፡ እነዚህ እኔነት የማይላቀቃቸው፣ ጥቅምን ብቻ ታሳቢ አድርገው የሚሮጡ ናቸው፡፡ ለቤተ ክርስቲያን መከፋፈልም ምክንያት ይሆናሉ፡፡ በእግዚአብሔር ቤት ያለ ቦታቸው የተቀመጡ፣ በጉልበት የተቀመጡ፣ በቦታቸው የተቀመጡ ሦስት ዓይነት ሰዎች ይታያሉ፡፡
 ራሱን የላከ ሰው የሚያምርበትን አያውቅም፡፡ ራሱን የቀባ ሰው የጌታ ቅባት ሲመጣ ያልፈዋል፡፡ ሁለት ቅባት የለምና፡፡ ያለ እርሻ እህል አይታጨድም፣ እሸት ይቀጠፍ ይሆናል፡፡ ያለ እርሻው የሚቀጥፍ ይታለፋል፣ ቢያጭድ ግን ይከሰሳል፡፡ በአብርሃም ቤት ይስሐቅና እስማኤል ይገለማመጣሉ /ዘፍ. 21፡9/፡፡ ይስሐቅ በጸጋ የተወለደ፣ የእግዚብሔር ቻይነት ብቻ የተገለጠበት፣ የቀጥታ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ እስማኤል ግን በጉልበትና በአቋራጭ የተወለደ ነው፡፡ በጸጋ የሚያገለግሉና በጉልበት የሚያገለግሉ ዛሬም መገለማመጥ ይኖራል፡፡ አሮንን ለክህነት፣ ባስልኤልን ለጠራቢነት የጠራው አንዱ እግዚአብሔር ነው /ዘጸ. 28፡1፤31፡1-5/፡፡ የተሰጠንን ብንሆን ክብር አለን፡፡ ጥሩ ሐኪም ጥሩ ሰባኪ መሆን አይችልም፡፡ ጥሩ ፖለቲከኛም ጥሩ ካህን መሆን አይችልም፡፡ ጸጋና መላክ የሚሉት ነገሮች ወሳኝ ናቸው፡፡ ጸጋው አለኝ? ደግሞስ ተልኬአለሁ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ያለ ቦታችን ስንገኝ የእኛ ቦታ ክፍት ይሆናል፡፡ ሰው ያለ ቦታው ትርፍ፣ በቦታው ዋና ነው፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ግን ከእግዚአብሔር የተላከ ነበር፡፡ ጌታ ሆይ ያማረንን ሳይሆን የሚያምርብንን ስጠን፡፡
የታወቅሁበት የተጠራሁበት በሚል እንደ አዲስ መጀመር ልንፈራ እንችላለን፡፡ ይልቁንም የምንንቀው ሰው የምንፈልገውን አገልግሎት ይዞ ስናይ እርሱ የያዘውን እኔ እንዴት ያቅተኛል? ልንል እንችላለን፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ግን የተጠራና የተላከ ስለ ነበር ቃሉ የዱላ ያህል ቢሆንም እስከ ሄኖን ሸለቆ ወርደው ይሰሙት ነበር፡፡ ከተላክን በዱላም እንማርካለን፡፡ በጸጋ ካልሆነ ግን እንደ ግብጽ አዋላጆች ሥራችን ማዋለድ ሳይሆን ማነቅ ይሆናል፡፡ አንድ አባት፡- “ስፍራዬን አሳውቀኝ” እያሉ ይጸልዩ ነበር፡፡ እርሻችንን ስናውቅ የማጨድ መብት ይኖረናል፡፡ ያለ ስፍራችን ከሆንን ከማስተማር መሳደብ ይቀናናል፡፡ የተላክንበትን ሕዝብ ስናገኝ እንረዳዋለን እንጂ አናደናብረውም፡፡ በሰው እርሻ ገብተንም ልጨድ አንልም፡፡
ዝንጀሮን በባህር በገደል ላይ ዓሣ
መስቀል ለዛር ፈረስ ከበሮን ላንካሳ
ጌታዬ ብይንህ ተወላገደሳ
 አንድ መሪጌታ ናቸው፡፡ በጣም መልካም ሰው ናቸው፡፡ ክፉ ቢታጣባቸው በደጉ ተከሰሱ፡፡ “አንድ ቀን እንኳ ተሳስተው ክፉ ተናግረው አያውቁም” ቢባሉ “ደጉ መች አልቆብኝ ነው ክፉ የምናገረው” አሉ ይባላል፡፡ እንዲሁም ከእግዚአብሔር የተላከ የሚናገረው ስለ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ስለ እግዚአብሔር መናገር ከጀመርን ጊዜ ተርፎን ስለ ሌላ መናገር አንችልም፡፡ በዘመነ ብሉይ እግዚአብሔር አብ ስለ ልጁ፣ በዘመነ ሐዲስ እግዚአብሔር ወልድ ስለ አባቱ፣ በዘመነ ቤተ ክርስቲያን መንፈስ ቅዱስ ስለ ወልድ ይናገራል፡፡ እግዚአብሔር የማያልቅ ርእስ፣ የማይሰለች የዘመናት ዜና ነው፡፡ ፍቅርን ታዳሽ የሚያደርገው ርእስ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ የማልቀው ደግነት እንጂ ክፋት ያልቃል፡፡ ጠብታ ውሃ መሬት ብትፈስ ትባክናለች፣ ውቅያኖስ ብትገባ ፍጹም ትሆናለች፣ ትበዛለች፡፡ ዘላለም ትሆናለች፡፡ ቀኑም እንደ ጠብታ ነው፣ ዘላለም ሲያዘው አስደሳች ይሆናል፡፡ ዘላለም ግን በቀን ሲታዘዝ መልካም አይደለም፡፡
2- ሰዎች የላኩአቸው አሉ
 ሰዎች እንደ ምኞታቸው ቀርጸዋቸው፣ ያልጨረሱትን ጦርነት እንዲፈጽሙላቸው የሚልኳቸው አሉ፡፡ እነዚህ መልእክተኞችም ጭካኔ የተሞሉና ለማንም ርኅራኄ የሌላቸው ናቸው፡፡ አገልግሎታቸው በቀል ይሁን ፍቅር አይታወቅም፡፡ ባለፉት ዘመናት በወንጌል መልእክተኛነት ስም አፍሪካን ያስወረሩ፣ ለቅኝ ገዢዎች መንገድ የከፈቱ አያሌ ናቸው፡፡ ዛሬም የአገር ፍቅርን፣ መልካም ባህልን፣ የቀና ሃይማኖትን ለመበረዝ የሚሮጡ መልእክተኞች አሉ፡፡
3- እግዚአብሔር የላካቸው አሉ
እነዚህ አገልጋዮች እግዚአብሔርን ብቻ ለማሳየት የሚተጉ፣ ርኅራኄን የተሞሉ፣ ለመንጋውና ለቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚተጉ ናቸው፡፡ ከእግዚአብሔር ተልከዋልና እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገራሉ፡፡ የተላከ ሰው አይጨምርም አይቀንስም፡፡ ለላኪው ክብር፣ ለተቀባዩ ፍቅር ይዞ የሚሄድ ነው፡፡ በእግዚአብሔር መላክ ክብር ነው፡፡ የሰማይ አምባሳደር መሆን ነው፡፡ የክርስቶስን ወንጌል የተሸከመ ክቡር ነው፡፡ የሚታየው ላኪውና መልእክቱ እንጂ ቅጥነቱና ውፍረቱ አይደለም፡፡
እግዚአብሔር አንድን ሰው፡- “ልጄ ልልክህ ነበረ፣ ግን ትልቅ ስለሆንህ ተውኩት” አለው ይባላል፡፡ ትሑት መሆንን ያድለን፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ