“ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ ይህ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክር መጣ።ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ፥ እርሱ ብርሃን አልነበረም” /ዮሐ. 1፡6-8/፡፡
ወንጌላዊው ዮሐንስ ስለ ወልድ ቀዳማዊና ዘላለማዊ ልደት፣ ስለማይመረመረው ምሥጢር እየተናገረ ወዲያው ወደ መጥምቁ ዮሐንስ ትርካ የገባው ለምንድነው? ስንል ዮሐንስ መጥምቅ በጣም የተከበረ ስለነበረ ክርስቶስ ከከበሩት የከበረ መሆኑን ለመግለጥ ነው፡፡ የወልድን ቀዳማዊነትና ዘላለማዊነት ለመተረክ ሞከረና አቅቶት በምድር ያለ ምስክር መጥራት ፈለገ፡፡ እናቶች፡- “እግዜርን እግዜር ያመስግነው” ይላሉ፡፡ እኔ አመስግኜ አልዘልቀውም ማለታቸው ነው፡፡ የልኩን ያህል ማመስገን አይቻልም ማለታቸው ነው፡፡ አመስጋኞች ሁሉ እያመሰገኑ ያሉት የአቅማቸውን ያህል እንጂ የልኩን ያህል አይደለም፡፡ “ሥራው ሥራውን፣ ባሕርዩ ባሕርዩን ያመስግነው” በማለት አባቶች አርፈዋል፡፡ እግዚአብሔር በራሱ ብቻ ይታወቃል፡፡ ታላቅ መገለጥን ያየው ነቢዩ ሙሴ እንኳ፡- “ምሥጢሩ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው የተገለጠው ግን የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ እናደርግ ዘንድ ለእኛ ለዘላለምም ለልጆቻችን ነው” ብሏል /ዘዳ. 29፡29/፡፡ እግዚአብሔር በራሱ ብቻ የታወቀ ነው፣ ትንሹ መገለጥ ግን ለእኛ ነው በማለት ነቢዩ ሙሴ እግዚአብሔር ከአእምሮ በላይ መሆኑን ይናገራል፡፡
ወንጌላዊው ዮሐንስም አቅቶት ወደ ምድር ይመለሳል፡፡ ከማይጨርሰው ጀመረ፣ ከማይዘልቀው አሐዱ አለ፡፡ ይህ ወንጌላዊ መጥምቁ ዮሐንስን የብርሃን ምስክር ነው ይለዋል፡፡ ብርሃን እግዚአብሔር ከሚጠራባቸው የጠባዩ ስያሜዎች አንዱ ነው፡፡ ብርሃን መነሻ ነው እግዚአብሔርም የነገር ሁሉ መነሻ ነው፡፡ ያለ እርሱም አንዳች ማድረግ አንችልም፡፡ ያለ እግዚአብሔር ማቀድ ክንድ የሌለው እጅ፣ ባሕር የሌለው ዓሣ መሆን ነው፡፡ እግዚአብሔር ብርሃን ነው ስንል የሕይወት እውነት ነው፡፡ እውነትነቱ ግን ድካማችንን መንገሩ ሳይሆን ዕረፍትን አዘጋጅቶ መጥራቱ ነው፡፡ መድኃኒቱን የሚያስቀድም እውነት ነው፡፡ ይህ ብርሃን ሸፋኝ ብርሃን ነው፡፡ እውነቱ ይውጣ የሚል ድምፅ እውነትን በገፋች ዓለም ላይ ይሰማል፡፡ እውነት ከምድር ስትጠራ ይጋለጥ የሚል ትርጉም አላት፣ ከሰማይ ግን ትርጉሟ ይዳን የሚል ነው፡፡ እውነትን ከምድርና ከሰማይ ስናያት ትርጉሟ ይለያያል፡፡ ዮሐንስ የዚህ ብርሃን ምስክር ነው፡፡ ዮሐንስ ከጌታችን ጋር በሥጋ ዘመድ ነው፡፡ ዮሐንስ ግን በሥጋ የተሰወረውን የክርስቶስን መለኮታዊነት አይቷል፡፡ መዛመድና መተዋወቅ ለዚህ ዓለም ሰዎች የመናናቅ ምክንያት ነው፡፡ ዮሐንስ ግን ሰማያዊ መልእክተኛ ነበርና ጌታችንን አከበረ፡፡ ምስክር ማለት በግእዙ ሰማዕት ማለት ነው፡፡ ምስክርነትና መሥዋዕትነት የአንድ ሣንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ ዮሐንስም ምስክርነቱን በሰማዕትነት ፈጽሟል፡፡
“ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ፥ እርሱ ብርሃን አልነበረም” ይላል፡፡ በርግጥ ክርስቲያኖች ሁሉ ብርሃን ተብለዋል /ማቴ. 5፡14/፡፡ ታዲያ ዮሐንስ ብርሃን አልነበረም ማለት ምን ማለት ነው? ትልቁ ብርሃን ፀሐዩ ክርስቶስ ነው፡፡ ዮሐንስ ግን የጨረቃ ብርሃን ነበረ፡፡ ጨረቃ ከፀሐይ ባገኘችው ብርሃን ለዓለም እንደምታበራ ዮሐንስም በክርስቶስ ያበራል፡፡ ክርስቶስ ግን በራሱ የሚያበራ ብርሃን ነው፡፡ ወንጌላዊው እንዲህ ማለት ያስፈለገው ለምንድነው? ስንል ብዙዎች ዮሐንስን የሚመጣው መሢህ ነው በማለት ያምኑት ነበረ፡፡ ዮሐንስ ግን ወደ እውነቱ የሚያደርስ ምልክት እንጂ ራሱ ፍጻሜ አልነበረም፡፡ አይ የሰው ልጅ! “እኔ ነኝ” ሲል ክርስቶስን ካደው፡፡ ዮሐንስ “አይደለሁም” ሲል መሢህ ነህ አለው፡፡ ዮሐንስ በእጁ ተአምራት ሲያደርግ አይታይም፡፡ ትልቅ ተአምራት ግን ሰዎችን ለንስሐ ማብቃት ነው፡፡ የሌሎች ተአምራት ሁሉ ግብ ንስሐ ነው፡፡ መጥምቁ ዮሐንስን ለምንድነው? እንደ መሢህ ያዩት ስንል አንዱ ከሰው ተለይቶ በበረሃ ይኖር ስለነበር ነው፡፡ ዮሐንስ በረኸኛ ስለነበር በጣም ያከብሩት ነበር፡፡ ዓለም የናቃትን ታከብራለች፡፡ ምን ቢኖረው ነው እያለች ታስሳለች፡፡ ክርስቶስን ግን በሰው መካከል እየተመላለሰ መጣ፡፡ ሠርግ ቤት የሚጠራ ልቅሶ ቤት የሚደርስ ሆነ፡፡ አምላካቸው ገናና ከሰው የራቀ እንዲሆን የሚፈልጉ ትሕትናውን መቀበል አቃታቸው፡፡
እኛስ እናምንሃለን እናመሰግንሃለን፡፡