የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ረቡዕ መጋቢት 7/2008 ዓ.ም.
“ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር” /ዮሐ. 1፡9/፡፡
ብርሃን የዚህች ዓለም ዕለታዊ ፍላጎት ነው፡፡ ዓይናችንም ሆነ ልቡናችን ብርሃን ይፈልጋሉ፡፡ የዓለም ሀብትም ለዚህ ብርሃን አስገኚ ኃይል ይባክናል፡፡ ብርሃን የተሟላ ኑሮ መግለጫ፣ የነገሥታት የአመራር ብቃት ማሳያም ሆኗል፡፡ በአገራችን እገሌ የምትባል ከተማ የሃያ አራት ሰዓት የመብራት ተጠቃሚ ሆነች ተብሎ ይጨፈራል፡፡ እንኳን ጨለማ ፈረቃ ብርሃንም አይለመድም፡፡ ብርሃንን ማየት ከሰብአዊ መብቶች አንዱ ነው፡፡ እስረኞች እንኳ ብርሃን አይከለከሉም፡፡ ከታሰሩበት አሥር ዓመት ይልቅ ጨለማ ውስጥ የታሰሩበትን ሦስት ቀን አይረሱም፡፡ ብርሃን አይጠገብም፣ ጨለማም አይለመድም፡፡ እያለ የምናጠፋው ብርሃን ሲሄድ ይናፍቀናል፡፡ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ይህች ዓለም የኃይልና የብርሃን ጥገኛ ሆናለች፡፡ ብርሃን ሕይወት ያለው ሁሉ በቃኝ የማይለው ፍላጎት ነው፡፡ እንኳን ሰው አትክልትም ያለብርሃን አይኖሩም፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ብዙ ብርሃናት አሉ፡፡ የዓይንና የልብ ብርሃን ብለን ለሁለት መክፈል እንችላለን፡፡
1- የመቅረዝ ብርሃን
ዘይቱ ሲሞላ፣ ክሩ ሲጸና የሚያበራ ነው፡፡ ዘይቱ ሲያልቅ ይሞላል፡፡ ክሩ መንደድ ሲያቆም ይቃናል፡፡ ይህ መንፈስ ቅዱስን ተሞልተው የሚያበሩ ክርስቲያኖች ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡ ክርስቲያኖችም ዘይቱ በውስጣቸው አለና ለማብራት ቀና ማለት ያስፈልጋቸዋል፡፡
2- የርችት ብርሃን
በአንድ ጊዜ ከፍታ፣ ብርሃንና ውበት ይታይበታል፡፡ ወዲያው ከፍታ በመሰወር፣ ብርሃን በመጨለም፣ ውበት በመጠውለግ ይጠፋል፡፡ ይህ ብርሃን የሚያስወጣው ዋጋ ከፍ ያለ ሲሆን ከበዓላት ኪሣራ አንዱ ነው፡፡ የዚህ ዓለም ፍቅር ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡ የዚህ ዓለም ፍቅር ሻሽ አያደርቅም፡፡ እዩኝ እዩኝ ይላል፣ መካካብ ይበዛዋል፡፡ ወረቱ ልብን ያጠፋል የኖረውን ወዳጅ ያስረሳል፡፡ ወዲያው ግን ከፍታው በመናናቅ፣ ብርሃኑ በርግማን፣ ውበቱ በጠብ ያከትማል፡፡
3- የጥዋፍ ብርሃን
መዓዛ አለው፣ እስካለ ድረስ ብቻ ያበራል፡፡ ነፋስ ካጠፋውና ካለቀ ግን መዓዛው ማቃጠል፣ ጭሱ መረበሽ ይጀምራል፡፡ ይህ የሰው መልካምነት ምሳሌ ነው /ማቴ. 12፡20/፡፡ የሰውም መልካምነት ፈተና እስከሚገጥመው ይቀጥላል፡፡ መልካምነቱ ሲፈተን ጭሱ መረበሽ ማስለቀስ ይጀምራል፡፡ ጭሱ የረበሸውም ፈጽሞ ሊያጠፋው እንጂ ሊያቀጣጥለው አይፈልግም፡፡ መልሶ ይበራል ተብሎ ተስፋ አይደረግም፡፡ ጌታችን ግን የሚጤስን የጥዋፍ ክር አያጠፋም፡፡ ዛሬ የምናያቸው ክፉ ሰዎች በክፉነት የጀመሩ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ስለ ክፉዎች ስንናገር ክፉዎችን ስላከፉ፣ ከጀርባ ስላሉት ክፉዎች መርሳት የለብንም፡፡ ስለዲዮቅልጥያኖስ ክፋት ስንናገር ዲዮቅልጥያኖስን ስላከፋው ስለ አባ አጋግዮስ ልንረሳ አይገባም፡፡ እንጀራችንን የበሉ ተረከዛቸውን ሲያነሡብን መታገሥ እንጂ ሰው በቃኝ ብለን ከመልካምነት መመነን አይገባንም፡፡
4- የአምፑል ብርሃን
ከጣራችን በታች የሚያበራ ብርሃን ነው፡፡ የራሳቸው ስለሆኑት ብቻ የሚያስቡና ከክልላቸው ወጥተው ደግ ለመሆን የማሰቡ ወገኖችን ይገልጣል፡፡ ቢያደርጉም የሚያደርጉትን ይቆጥራሉ፡፡
5- ሐሰተኛ ብርሃን
ቦግ ጭልም የሚሉ ሐሰተኞች የሚፈልጓቸው የሆቴል መብራቶች አሉ፡፡ አያሳይም ደግሞም አይጨልምም፡፡ የሚያጭበረብር ብርሃን ነው፡፡ ሐሰተኛ ትምህርትን ይመስላል፡፡ የእግዚአብሔርን ስም ይጠራል፣ መልሶ ይጨልማል፡፡ መጨረሻው ሥልጣንና ገንዘብ ሆኖ ይጠናቀቃል፡፡ ከጨለማ በላይ የሚያምታታ ብርሃን ለሰይጣን የበለጠ አሳቡን ይፈጽምለታል፡፡ ሰይጣን እንዳንኖር ሳይሆን ያለን እየመሰለን እንዳንኖር የማድረግ እቅድ አለው፡፡ ይህ ደግሞ የኑፋቄ ትምህርት ጠባይ ነው፡፡
6- የጨረቃ ብርሃን
ጨረቃ የራሷ ብርሃን የላትም፣ ግን ጨለማ አትባልም፡፡ ባዶ ሰሌዳዋን ወደ ፀሐይ ዘርግታለችና፡፡ የጨረቃ ብርሃን በጨለማው ዓለም የሚያበሩ የክርስቲያኖች ምሳሌ ናት፡፡ የራሳችን ብርሃን ባይኖረን አንወቀስም፣ ወደ ፀሐዩ ጌታ ባዶ የጽድቅ ሰሌዳችንን ካልዘረጋን ግን እንወቀሳለን፡፡
7- የፀሐይ ብርሃን
የፀሐይ ብርሃን የጌታችን ምሳሌ ነው፡፡ ሳይጎድልበት ለሁሉ የሚሰጥ፣ ሳይለይ ሁሉን የሚያፈቅር ነውና፡፡ “ነገር ግን ስሜን ለምትፈሩት ለእናንተ የጽድቅ ፀሐይ ትወጣላችኋለች፥ ፈውስም በክንፎችዋ ውስጥ ይሆናል እናንተም ትወጣላችሁ፥ እንደ ሰባም እምቦሳ ትፈነጫላችሁ” /ሚክ. 4፡2/፡፡ “እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና” /ማቴ. 5፡45/፡፡
እውነተኛው ብርሃን