የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የገዛ ወገኖቹ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ሐሙስ መጋቢት 15/2008 ዓ.ም.
 
“በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም። የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም” /ዮሐ. 1፡10-11/፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም መጣ ሲል ከዓለሙ ተለይቶ በአፍአ ነበረ ማለት አይደለም፡፡ በልዩ መገለጥ ሥጋ ለብሶ ታየ ማለት ነው፡፡ ወንጌላዊው፡- “በዓለም ነበረ” ያለው ለዚህ ነው፡፡ እርሱ በዓለም የነበረ ብቻ ሳይሆን ለዓለሙ መገኘት ምክንያት የሆነ ፈጣሪ መሆኑን ይገልጣል፡፡ ዓለም የተከናወነው በእርሱ ነው፡፡ ዓለሙ ግን ከራሱ በሚያንሱ ጣዖታት እያመነ ፈጣሪነቱን አላወቀም፡፡ አሁን ደግሞ ሥጋ ለብሶ ሊያድን ቢመጣ ዓለሙ በራሱ ስለ ታመነ ሊቀበለው አልፈቀደም፡፡ ጣዖታት ፈጣሪነቱን፣ የራስ ትምክሕት አዳኝነቱን እንደ ጋረዱ ያሳያል፡፡ እርሱ የመጣው ወደ ባዕዳን ሳይሆን ወደ ወገኖቹ ነው፡፡ በመልኩና በምሳሌው ወደ ፈጠራቸው፣ በጸጋ ልጅነትና ገዢነት ወዳከበራቸው ወደ ሰው ልጆች ነው፡፡ ወንጌላዊው መላውን የሰው ልጅ የእርሱ የሆኑትና ወገኖቹ በማለት ይገልጣል፡፡ ጥንትም በፍጥረት ወገኖቹ ነበርን፡፡ ያንን ልጅነትና ክብር በኃጢአት ስላጣነው ጌታችን ዳግመኛ ሊመልስልን መጣ፡፡ ይህን ልጅነት የምናገኘውም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ነው፡፡

እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም መጣ ሲባል ከዓለሙ ተለይቶ የነበረ ስለሆነ አይደለም ብለናል፡፡ ከዓለሙ በመግቦት በረድኤት ያልተለየው አምላክ አሁን ደግሞ ሥጋ ለብሶ መጣ፡፡ ይህ ታላቅ አስተርእዮ ወይም መገለጥ ነው፡፡ ከዓለሙ ያልተለየ ብቻ ሳይሆን የዓለሙ አስገኚም ነው፡፡ የመጣው ወደ ፈጠረው ዓለም ነው፡፡ ንጉሥ ወደ ግዛቱ ሲገባ ታላቅ አቀባበል ይደረግለታል፣ እርሱ ግን ማደሪያ አጥቶ በበረት ወደቀ፡፡ በፈጠረው ዓለም እንደ ባዕድ ታየ፡፡ በገዛ ንብረታቸው ተመልካች ሆነው ለሚያዩ፣ ተወርሰው ለሚያለቅሱ፣ ሌሎች እየጠገቡ እነርሱ ግን ለሚራቡ ሰዎች መጽናናት በሚሆንበት መልክ መጣ፡፡ የመጣውም እንስሳትንና አእዋፋትን አድራሻ አድርጎ ሳይሆን ሰውን አድራሻ አድርጎ ነው፡፡ ይህም ለሰው ልጅ ትልቅ ክብር ነው፡፡ ጌታችን የእኔ ናቸው ደግሞም ወገኖቼ ናቸው ይቀበሉኛል ብሎ ሲመጣ ሰው ግን አለመቀበሉ ያሳዝናል፡፡ ያመነንን ጌታ አለማመን፣ የወደደንን ጌታ አለመውደድ፣ ለምስጋና የሚጠብቀንን ጌታ ይሰቀል ማለት በእውነት የማይገባ ተግባር ነው፡፡
ወንጌላዊው፡- “የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም” ይላል፡፡ የሰው ልጆች ሁላችን አንደኛ የእርሱ ነን፡፡ ሁለተኛ ወገኖቹ ነን፡፡ ሰው የእግዚአብሔር ነው፡፡ ሰው የራሱ አይደለም፡፡ ሰው የወላጆቹም አይደለም፡፡ ሰው ራሱን ሳይገነዘበው፣ ወላጆቹም ሳያዩት በእግዚአብሔር የታየ ፍጡር ነው፡፡ እኛ በእኛ ላይ፣ ሰዎችም በእኛ ላይ ካላቸው እቅድ በላይ እግዚአብሔር በእኛ ላይ ያለው እቅድ ይበልጣል፡፡ ወደዚህ ዓለም የመጣነው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፡፡ እኛ የእግዚአብሔር ነን፡፡ ሰው ግን ይህንንም አላወቀም፡፡ “የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን” ይላል /1ቆሮ. 3፡16/፡፡ የምናውቀው እኛ የእኛ እንደሆንን እንጂ የእግዚአብሔር እንደሆንን አይደለም፡፡ ወንጌላዊው፡- “የእርሱ ወደ ሆነው”  ማለቱ ለዚህ ነው፡፡ ሰዎችም የእግዚአብሔር ናቸው፡፡ ስለዚህ የእኔ ሰዎች ልንል አንችልም፡፡ ሰዎችን የእኔ የማንላቸው ብዙ ምክንያቶች አሉን፡-
1-  ዋጋቸውን አንችለውም፡፡ ሰው የተገዛበት ዋጋ አምላካዊ ደም ነው፡፡
2-  ራሳቸውን ያጡታል፡፡ እንኳን ለእኛ ሊሆኑ ለራሳቸውም መገኘት የሚያቅታቸው ጊዜ ብዙ ነው፡፡
3-  የእግዚአብሔር ከሆኑ ይበቃናል፡፡ የእግዚአብሔር ከሆኑ የእኛ ወገኖች ናቸው፡፡ ሰውን ከርሞ የምናገኘው እግዚአብሔር ጋ ሲሆን ብቻ ነው፡፡
ሰው የእግዚአብሔር መሆኑን መረዳት ከብዙ ውዝግብና ትዝብት ያድነናል፡፡ የራሳችንን ኅሊናም ከመጉዳት ይጠብቃል፡፡ እኛ የእግዚአብሔር ነን፣ እግዚአብሔርም የእኛ ነው፡፡ “ውዴ የእኔ ነው፥ እኔም የእርሱ ነኝ” /መኃ. 2፡16/፡፡ የእኔ ብለነው የማያሳፍረን፣ የእርሱ ሆነንም የማይጎዳን ውዳችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ጌታችን በመፍጠርና በማዳን ዋጋ ሰውን ስለገዛው የእኔ ቢለው ተገቢ ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ ነጻ ፈቃዱን ያከብርለታል፡፡ ባልፈጠርነውና ባልገዛነው ሰው መራኮት ግን ተገቢ አይደለም፡፡ ወንጌላዊው “የገዛ ወገኖቹ” በማለት በቅርበት ቃል ይናገራል፡፡ የግሪክ ፈላስፎችም፡- “እኛ ደግሞ ዘመዶቹ ነንና” ብለዋል /የሐዋ. 17፡28/፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ የእነዚህን ባለቅኔዎች አሳብ በመጥቀስ ጣዖታውያን የሆኑትን ይገስጻል፡፡ ዘመዶቹ ከሆንን እኛ እርሱን፣ እርሱ እኛን ይመስላል፡፡ ጣኦታት ግን ሕይወት የላቸውምና እኛን ሊመስሉ አይችሉም፣ ሕያው ሰው ግዑዝ ጣዖታትን ሊያመልክ አይገባውም የሚል መከራከሪያ አሳብ ያነሣል፡፡ ከተሣሣቱ ላይቀር ጣዖታት ሰውን ቢያመልኩ ይሻላል፡፡ ሰው ግን ወርዶ ጣዖትን ማምለኩ ክብሩን አለማወቁ ነው፡፡ በእውነት ክርስቶስ ሰው ሳይሆን እኛ የእርሱ ነን፣ ደግሞም ወገኖቹ ነን ከተባለ ሰው ከሆነ በኋላማ እንዴት ያለ ቅርበትን እንዳገኘን ልናስብና ልንደነቅ ይገባናል፡፡ የእኔ የምንለው፣ የእኔ የሚለን ሰው ባይኖረን ችግር የለውም፡፡ ከጠቢቡ ጋር እንዲህ እንላለን፡-
“ውዴ የእኔ ነው፥ እኔም የእርሱ ነኝ”/መኃ. 2፡16/፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ