የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ረቡዕ ጥር 25/2008 ዓ.ም
የዮሐንስ ወንጌል ተደራስያን
ዮሐንስ ወንጌሉን የጻፈው በሥጋ የተገለጠው ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ መሆኑን ለመግለጥ ነው። ከሦስቱ ወንጌላት ልዩ የሚያደርገው የሚጀምረው ከጌታ ጽንሰት፣ የትውልድ ሐረግ፣ ጥምቀት ሳይሆን ከዘላለማዊ ልደቱ በመሆኑ ነው። ቤተ ልሔም ለክርስቶስ ልዩ የመገለጥ ስፍራ እንጂ የህልውናው መነሻ አይደለችም። እርሱ ከዘላለም ከአብ ጋር የነበረ መሆኑን በመግለጥ ይጀምራል። የዮሐንስ ወንጌል ተደራስያን በክርስቶስ አምላክነት ማመን የሚገባቸው ወገኖች ሁሉ ናቸው። ማቴዎስ ለአይሁድ፣ ማርቆስ ለሮማውያን፣ ሉቃስ ለቴዎፍሎስ ሲጽፍ ዮሐንስ ግን ለአይሁድና ለአሕዛብ የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት እንዲያምኑ ጽፏል። ኢየሱስ ክርስቶስ በታሪክ ውስጥ የነበረ አንድ ሰው አድርጎ ማመን ለብዙዎች አይቸግራቸውም። ስለ ግፍ ሞቱና ስለ ደግነቱም ሊቀበሉ ይችላሉ። ይህንን የታሪክ መዝገብም አልካደውም። ለመዳን ግን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ መሆኑን ማመን ያስፈልጋል። በመስቀል ላይ የዋለው ሰው ብቻ ከሆነ ሞቱ ሰማዕትነት እንጂ ቤዛነት ሊሆን አይችልም። ደግሞም በፍጡር ዓለም ሊድን አይችልም። በመስቀል ላይ የሞተው መለኮት ብቻ ነው እንዳንል መለኮት በባሕርዩ አይሞትም። እርሱ ግን ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ነው። እርሱ እግዚአብሔር ባይሆን ኖሮ በሞቱ የእግዚአብሔር ፍቅር ተገለጠ ሊባል አይችልም።
ዮሐንስ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት ለመግለጥ የተጠቀመው አይሁዳውያንና አረማውያን በሚያውቁት ቃል ነው። “በመጀመሪያው ቃል ነበረ” በማለት ይጀምራል /ዮሐ. 1፡1/። ይህ ቃል የተባለው በግሪኩ ሎጎስ የሚባለው ነው። ሎጎስ ለብዙ መቶ ዓመታት የለማ ቃል ነው። ሎጎስ በጥንት አረማውያንና አይሁዳውያን ሥነ ጽሑፍ የታወቀ ነው። አንድ ኦርቶዶክሳዊ ሊቅም፡- “ከክርስቶስ ልደት በፊት በ500 ዓመት የነበረው ሒራክሊቱስ የተባለው ፈላስፋ “ሎጎስ እግዚአብሔርን በመግለጥ ዓለምን የሚገዛና የሚያሳውቅ የበላይ ምክንያት በማለት ጽፎ ነበር፡፡ ከእርሱም በኋላ በይበልጥ ለሌሎች ያስተዋወቁት ስቶይክስ የተባሉ ከ335-263 ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበሩ ፈላስፎች ናቸው፡፡ እነዚህ ፈላስፎች በአቴንስ ትምህርት ቤት አቋቁመው ስለ ሎጎስ ያስተምሩ ነበር፡፡ የዚህ ጽንሰ ሐሳብ ትርጉም ግሪክኛ በሚናገሩ አይሁዳውያን ዘንድ ይበልጥ እየተስፋፋ መሄዱ ጥበብ (Wisdom) ከሚለው ጋር የትርጉም ዝምድናን አገኘ፡፡ በእስክንድሪያ ከ30 ዓመተ ዓለም እስከ 50 ዓ.ም የነበረው ፋይሎ የተባለ አይሁዳዊ ፈላስፋ ግሪክኛ መጽሐፍ ቅዱስን በማዛመድ ሎጎስ የሚታየውንና የማይታየውን ዓለም አንድ ያደረገ መለኮታዊ ኃይል ነው በማለት ይገልጻል፡፡ የፋይሎን መጻሕፍት ያነበቡ ግሪክኛ ተናጋሪ አይሁድም እግዚአብሔር ራሱን ለዓለም ይገልጥ የነበረው በቃል አማካይነት ነው፡፡ ያህዌ ለአብርሃም፣ ለአጋር፣ ለይስሐቅ፣ ለያዕቆብ፣ ለሙሴ በቊጥቋጦ ራሱን የገለጠላቸው በቃል አማካይነት ነው… በማለት ይተርካሉ፡፡ ስለዚህ ወንጌላዊው ዮሐንስ በግሪክኛ ወንጌሉን ሲጽፍ አይሁዳውያንና አረማውያን በለመዱት “ሎጎስ” የሚለውን ቃል በመጥቀስ፡– “ለአባቶችና ለነቢያት ሥጋን ከመልበሱ በፊት የተገለጠው የያህዌ ቃል ዛሬ በሥጋ የተገለጠው ክርስቶስ እንጂ ሌላ አይደለም በማለት በመጀመሪያው ምዕራፍና ቊጥር ይገልጻል” ብለዋል።
ይህ ቃል ወይም ሎጎስ ለፍጥረት የበላይ ምክንያት፣ ዘላለማዊ ጥበብ፣ እግዚአብሔርን የገለጠ ብርሃን፣ አባቶችን የመራ፣ የአብ መልእክተኛ ነው። ዮሐንስም፡- “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል” ይላል /ዮሐ. 20፡31/። ስሙ ይቀደስ፡፡