የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ቃል ሥጋ ሆነ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ሐሙስ መጋቢት 22/2008 ዓ.ም.
“ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ”
/ዮሐ. 1፡14/፡፡
 ወንጌላዊው ስለ ቃል ቀዳማዊ ልደት በመናገር የጀመረው የቃልን ደኃራዊ ልደት ለመናገር ነው፡፡ በክፍሉ ስለ ሥላሴ ይናገራል፡፡ ቃል ብሎ ሲናገር ልብና እስትንፋስ የሌለው ቃል የለምና አብና መንፈስ ቅዱስንም ያሳስባል፡፡ ስለ ቃል ዘላለማዊነት ከተናገረ በኋላ የቃልን ከድንግል መወለድ ይገልጣል፡፡ ግቡም ክብር ስጡት የሚል ነው፡፡ ቃል ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እኩል ነው፡፡ ከከበሩት ከእነ ዮሐንስ መጥምቅ ግን በላይ ነው፡፡ የወልድ የኩነት ስሙ ቃል ነው ብለናል፡፡ ኩነት ወይም መሆን ለራስ በቅቶ፣ ለሌላው ተርፎ፣ ከሌላው መቀበል ነው፡፡ ወልድም በአብ መሠረትነት ለራሱ ቃል ሆኖ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ነው፡፡ በኩነት ቃልን ሲሰጥ በነሢዕ ደግሞ ከአብ ልብነትን ከመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስን ይወስዳል፡፡ ኩነት ወይም መሆን፡-
 
1-  መሠረት አለው
2-  ለራስ መብቃት ይገባዋል
3-  ለሌላው መስጠት አለበት
4-  ከሌላው መቀበል ይገባዋል፡፡ እኛም ብዙ የመሆን መመሪያዎች አሉን፡፡
ለምሳሌ፡- “እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ”/ማቴ. 5፡48/ “አባታችሁ ርኅሩኅ እንደ ሆነ ርኅሩኆች ሁኑ” /ሉቃ. 6፡36/፡፡ መሆንና ማስመሰል ልዩነት አላቸው፡፡ ሰዎች ሩኅሩኅ ለመምሰል ይችላሉ፡፡ መሆን ግን እውነት ነው፡፡ አንድ በጎ ነገር በማስመሰል ሲሠራ ድራማ ነው፣ በመሆን ሲሠራ እውነት ነው፡፡ መሆን ሲያቅተን ለመሆን እነዚህን አራት መመሪያዎች ማጤን አለብን፡፡ መሠረታችን እግዚአብሔር መሆን አለበት፡፡ እግዚአብሔር ላይ ያልተመሠረተ ማንነት ይናዳልና፡፡ ዳግመኛ ለራሳችን ልንገነዘበውና ልናጣጥመው ይገባል፡፡ ያላጣጣምነው ነገር ሊያጸጽተን ይችላል ወይም ደስታ የለሽ ያደርገናል፡፡ ከዚያም ለሌሎች ልንሰጠው ይገባል፡፡ ሕይወት መብቃት ብቻ ሳይሆን መትረፍም ነውና፡ ከሌሎችም የምንቀበለው ብዙ ይሆናል፡፡ ምርት የተትረፈረፈ ነውና፡፡

እርሱ በቃል ከዊን ሲኖር ሳለ አሁን ደግሞ በሥጋ ከዊን መጣ፡፡ የቃል ከዊንነቱ መምሰል የሌለበት እውነት እንደሆነ የሥጋ ከዊንነቱም መምሰል የሌለበት እውነት ነው፡፡ ለዚህ ነው ወንጌላዊው፡- “ቃልም ሥጋ ሆነ” ያለው፡፡ በእርግጥም ሰው ሆኗል፡፡ ዘላለማዊ ልደት ያለው እርሱ የደኃራዊ ልደት ባለቤት ሆኗል፡፡ መሆን ራስን ማጣት አይደለም፡፡ ራስን ሆኖ ሌላ ርስትን መውረስ ነው፡፡ አንድን ሰው እዚህ ጋ ሁን እዚህ ጋ ተቀመጥ ስንለው ማንነትህን እንደ ያዝህ ያንን ስፍራና ወንበር ውረስ ማለት ነው፡፡ ቃል ሥጋ ሆነ ሲባልም ማንነቱንና ክብሩን እንደ ያዘ የሥጋን ርስት ገንዘብ አደረገ ማለት ነው፡፡ “ቃልም ሥጋ ሆነ” ስለሚል አቡሊናርዮስ የተባለ መናፍቅ ነፍስን አልነሣም፡፡ የገዛ መለኮቱ ነፍስ ሆነው ብሎ አስተምሯል፡፡ ሥጋና ነፍስ ግን አንዱን ሰው ለመግለጥ የሚነገሩ ናቸው፡፡ ሥጋ ስላለ ነፍስ የለም ማለት አይደለም ነፍስ ስላለም ሥጋ የለም ማለት አይደለም፡፡ ይህ የመጽሐፍ ዘይቤ ነው፡፡ ቀጥሎ ያሉትን ጥቅሶች እንመልከት፡-
“አባቶችህ ሰባ ነፍስ ሆነው ወደ ግብፅ ወረዱ” ይላል /ዘዳ. 10፡22/ ይህ ማለት ሥጋቸው ከነዓን ቀረ ማለት ነው? ዳዊትም፡- “ሥጋ ሁሉ ጸሎትን ወደምትሰማ ወደ አንተ ይመጣል” ይላል /መዝ. 64፡2/፡፡ ይህ ማለት ነፍስ የሌለው ሥጋ ይጸልያል ማለት ነው? ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ ይላል /የሐዋ. 2፡17/፡፡ ይህ ማለት የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ነፍስን አይመለከታትም ማለት ነው፡፡ ይልቁንም ይህ ቃል የተነገረው በበዓለ ሃምሳ በአዲስ ቋንቋ በተናገሩ ጊዜ ነው፡፡ ቋንቋ ከሥጋ ይልቅ የነፍስ ነው፡፡ ነፍስና ሥጋ ግን በአንድ አካል ተዋህደዋልና በተዋህዶ ስማቸው “ሰው” ይባላሉ፡፡ በሌላ ጊዜም ነፍስ ወይም ሥጋ እየተባሉ ይጠራሉ፡፡
አቡሊናርዮስ ክርስቶስ ሥጋን እንጂ ነፍስን አልነሣም ሲል ሊቃውንቱ የሰጡት ምላሽ፡- “ያልተዋሐዳትን ነፍስ ሊቤዣት አይችልም” የሚል ነው፡፡ ዳግመኛም፡- “የኃጢአት መነሻ የሆነችውን ነፍስን ትቶ መዳንን እንዴት ሊፈጽም ይችላል?” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የሰው ልጅ በኃጢአት በወደቀ ጊዜ የወደቀው ሥጋው ብቻ ሳይሆን ነፍሱም ናት፡፡ መዋጀት የሚያስፈልገው የሰው ሥጋውም ነፍሱም ነውና ጌታችን ፍጹም ሰው ሆነ፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” ብሏል /1ጢሞ. 2፡5/፡፡ ሰው ከሆነ ሥጋ ብቻውን ሰው አይባልም፡፡ ሥጋና ነፍስ የተዋሐዱት እርሱ ሰው ይባላል፡፡ ጌታችንም በወንጌላት ራሱን ለ62 ጊዜ ያህል “የሰው ልጅ” እያለ ጠርቷል፡፡ የእንስሳት መሥዋዕት የኃጢአት ዋጋ መክፈል ያልቻለው በግዙፍነቱ ለሥጋ ካሣ መሆን ሲችል ረቂቅ ነፍስን ለመካስ ግን ሕያውነት ስላልነበረው ነው፡፡ ጌታችን ግን ሥጋንና ነፍስን በመንሣት ፍጹም ሰው ሆነ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እመቤታችን ድንግል ማርያምን “የኢየሱስ እናት” እያለ ይጠራታል፡፡ ከእርስዋ ሥጋንና ነፍስን ካልወሰደ እንዴት እናቱ ይላታል? ከእናቶች የሚወለዱ ልጆች ሥጋ ብቻ የነሡ ናቸው?
ጌታችን ሥጋንና ነፍስን እንደ ነሣ የነፍስ ጠባያቱ ያስረዳሉ፡፡ አቡሊናርዮስ ነፍስን አልነሣም፣ የገዛ መለኮቱ ነፍስ ሆነው ብሏል፡፡ ነገር ግን ጌታችን የነፍስ ጠባያት ታይተውበታል፡፡ አዝኗል፣ አልቅሷል፣ ተክዟል፣ እስከ ሞት ድረስ ተጨንቋል፡፡ የነፍስ ጠባያት ናቸው፡፡ መለኮት በባሕርይው አይጨነቅም፡፡ ጌታ ግን፡- “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች” ብሏል /ማቴ. 26፡38/፡፡ ራሱ ባለቤቱ ነፍሴ እንጂ መለኮቴ አላለም፡፡ ዳግመኛም እጅግ አዘነች በማለት የነፍስን ጠባይ የሆነውን ማዘንን ገልጧል፡፡ በመስቀል ላይም፡- “አባት ሆይ፥ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ አለ። ይህንም ብሎ ነፍሱን ሰጠ” ይላል /ሉቃ. 23፡46/፡፡ ነፍሱን ሰጠ የሚለው ቃል በይበልጥ ያብራራልናል፡፡ ጌታችን ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ካልነሣ ሰው ሆነ ማለት አይቻልም፡፡ ሰው ማለት ነፍስና ሥጋ ያሉት ነውና፡፡ እርሱ ከፊል ሰውን ሳይሆን ፍጹም ሰውነትን ገንዘብ አድርጓል፡፡ የዕብራውያን ፀሐፊ፡- “የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም” ያለው ለዚህ ነው /ዕብ. 2፡16/፡፡ ነፍስና ሥጋን ካልነሣ የአብርሃም ዘር ሊሆን እንዴት ይችላል?
“ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ”
/ዮሐ. 1፡14/፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ