የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የተዋህዶ ምሥጢር

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ማክሰኞ መጋቢት 27/2008 ዓ.ም.
“ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ” /ዮሐ. 1፡14/፡፡
ከተዋህዶ በፊት ሁለት የማይገናኙ አካላት ከተዋህዶ በኋላ የማይለያዩ ሆነዋል። ከተዋህዶ በፊት ሁለት አካላት ነበሩ። በተዋህዶ ግን አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነዋል። ተዋህዶ ያለመለወጥ ነው። መለኮትና ትስብእት በመጠባበቅ አንድ ሆነዋል። ተዋህዶ ማለት ሁለት ማንነቶች ማንነታቸውን ሳይከስሩ አንድ መሆናቸው ነው። ተዋህዶ ለሥጋዌ ብቻ ሳይሆን ለምሥጢረ ሥላሴም ይነገራል። በምሥጢረ ሥላሴ ሦስቱ አካላት በመለኮት ይዋሐዳሉ ወይም አንድ ይሆናሉ። በምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት አካላት ሳይዋሐዱ መለኮትም ሳይከፈል ዘላለም ሥላሴ ዘላለም አሐዱ አምላክ ሆነው ይኖራሉ። የአካላት ሦስት መሆን መለኮትን አይከፍልም። የመለኮት አንድ መሆንም አካላትን አይጠቀልልም። በሥጢረ ሥጋዌ ግን የባሕርይ ብቻ ሳይሆን የአካልም አንድነት አለ። ተዋህዶ ለሥጋዌ ሲነገር አካልም ባሕርይ አንድ መሆናቸውን ያስረዳል። ተዋህዶ በምድር ላይም ለነፍስና ሥጋ፣ ለትዳር፣ ለቤተ ክርስቲያን ይነገራል። ምሥጢረ ሥጋዌን የሚያብራራልን ግን የነፍስና የሥጋ ተዋህዶ ነው፡፡

ነፍስ ከሥጋ ጋር በተዋህዶ ትኖራለች። ነፍስ ረቂቅነቷን ሳትለቅ ከግዙፍ ሥጋ ጋር ተዳለች። ሥጋም ግዝፈቱን ሳይለቅ ከረቂቅ ነፍስ ጋር ተዋህዷል፡፡ ነፍስ የሥጋን መከራ ለራስዋ አድርጋ ትናገራለች፡፡ ደግሞም ይናገሩላታል፡፡ ለምሳሌ እገሌ ነፍስ ገደለ ይባላል፡፡ ነፍስ በባሕርይዋ የማትሞት ስትሆን ከሥጋ ጋር ተዋህዳለችና የሥጋ ሞት ለእርስዋ ይነገራል፡፡ በተዋህዶ ነፍስ የሥጋን፣ ሥጋም የነፍስን ርስት ገንዘብ ያደርጋልና፡፡ ሥጋና ነፍስ ፍጹም የማይገናኝ ማንነት ቢኖራቸውም በተዋህዶ ግን ተስማምተው አንድ ሆነው ይኖራሉ፡፡ ሁለት የተለያየ ማንነቶች በአንድ ሰው ውስጥ ቢኖሩእኔ እንጂ እኛ የሚል ድምፅ አያሰሙም።ተዋህዶ እኛ የሚል ድምፅን ይሽራልና፡፡
እንዲሁም መለኮትና ሰውነት እንደ ነፍስና ሥጋ ተዋህደዋል። ነፍስና ሥጋ በአካልም በባሕርይም እንደ ተዋሐዱ መለኮትና ሰውነትም እንዲሁ ተዋህደዋል፡፡ ነፍስ የራስዋ ያልሆነውን የሥጋ ሕማምና ሞት እንደሚነገርላት እንዲሁም መለኮትና ሰውነት በፍጹም ተዋህደዋልና የሥጋ መከራና ሞት ለመለኮት ይነገራል፡፡ ሥጋ የነፍስን ክብር የራስዋ ነፍስም የሥጋን ድካም የራስዋ አድርጋ ትናገራለች፡፡ መለኮት የሰውነትን ውርደት የራሱ፣ ሥጋም የመለኮትን ክብር የራሱ አድርጎ ይናገራል፡፡ በተዋህዶ አንዱ የአንዱን ርስት ገንዘብ ያደርጋልና፡፡ ነፍስና ሥጋ ሁለት አካላትና ባሕርያት እንደነበሩ በሞት ቀን እንረዳለን፡፡ ሥጋም ወደ አፈር፣ ነፍስም ወደ እግዚአብሔር ይሄዳሉ፡፡በዚህ ዓለም ላይ ግን አንዱ ያለ አንዱ አይገለጽም፡፡ እንዲሁም መለኮትና ሰውነት ከተዋህዶ በፊት በየራሳቸው ቢሆኑም ከተዋህዶ በኋላ ግን ላይለያዩ አንድ ሆነዋል፡፡ አማኑኤል ማለት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሆነው በረድኤት በተአምራት ሳይሆን በተዋህዶ ነው፡፡ ዘላለም አማኑኤል ነውና ተዋህዶም ዘላለማዊ ነው፡፡ ነፍስና ሥጋ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ናቸውና እኔ እንጂ እኛ አይሉም፡፡ መለኮትና ሰውነትም በተዋህዶ አንድ ነዋልና እኔ እንጂ እኛ የሚል ድምፅ አሰማም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እኔ እያለ ተናገረ እንጂ እኛ እያለ አልተናገረም፡፡
 ከተዋህዶ በኋላ ሁለትነትና ፈረቃ የለም። ይህን ያደረገው ሥጋ ነው ይህን ያደረገው መለኮት ነው አይባልም።አንዱ ክርስቶስ ይህን አደረገ፡፡ ሥጋና ነፍስ የተዋህዶ ስማቸው “ሰው” የሚል ነው፡፡ እንዲሁም የመለኮትና የሰውነት የተዋህዶ ስም ኢየሱስ የሚል ነው፡፡ ሰው መባልን ሥጋ ብቻውን አይጠራበትም፡፡ ነፍስ ስትለየው በድን ይባላል፡፡ ነፍስም ብቻዋን አትጠራበትም፡፡ ነፍስ ያለ ሥጋ በዚህ ዓለም መገለጥና መጠራት አትችልምና፡፡ እንዲሁም ኢየሱስ የሚለውን ስም ከተዋህዶ በፊት መለኮትም ሥጋም ለብቻ አልተጠሩበትም፡፡ ከተዋህዶ በኋላ ግን ኢየሱስ ስመ ተዋህዶ የተጸውዖ መጠሪያ ሆኖአል፡፡ ኢየሱስ ማለትም አዳኝ ማለት ነውና፡፡ መዳን የተከፈለው በተዋህዶ ነው፡፡ መለኮት በሥጋ ሞቶ፣ ሥጋም በመለኮት መድኃኒት ሆኖ መዳን ሆኗል፡፡
 ቃል ሥጋ ሆነ የሚለውን ቃል በመያዝ መለኮት ወደ ሰውነት ተለውጧል። ክብሩንም አጥቷል የሚል አሳብ የያዙ ወገኖች ነበሩ። ሆነ የሚለውን ቃል የተረዱት የሎጥ ሚስት የጨው ሐውልት እንደሆነየቃና ዘገሊላ ውኃም ተለውጦ ወይን ጠጅ እንደሆነ መለኮትም ከሥጋ ጋር በተዋሐደ ጊዜ የባሕርይ ክብሩን አጥቷል የሚል አሳብ ይዘው ተነሥተዋል። በተቃራኒም አውጣኪ የተባለው በአምስተኛው ክፍለ ዘመን የተነሣው መናፍቅ መለኮትና ሥጋ በተዋሐዱ ጊዜ መለኮት ሥጋን መጠጠውወደ ራሱ አፈለሰውከዚያ በኋላ ያደረገው ሁሉ ለእኛ እንዲመስለን ለአርአያ ለትሕትና ነውብሏል። እነዚህን ሁለት አስተሳሰቦች የሚመክተው ተዋህዶየሚለው ቃል ነው። ተዋህዶ የራስን ማንነት ሳያጡ የሌላውንም ማንነት ሳያሳጡ አንድ መሆን ነው። የአውጣኪ አሳብ ነገረ ድኅነትን ይነካል፡፡ ክርስቶስ ያደረገው ሁሉ እውነትነት ከሌለው ቤዛችን ሊሆንና ሊያድነን አይችልም፡፡ ያደረገው ሁሉ ከተውኔትነት አያልፍም ማለት ነው፡፡ እውነት በሌለበት ደግሞ መዳን ሊፈጸም አይችልም፡፡
ወንጌላዊው “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ” ያለው እጅግ ጠቃሚና በዘመናት ለተነሡ ክርክሮች መልስ የሰጠ ነው። ሆነእና አደረየሚሉት ቃላት ትልቅ መመከቻ ናቸው። ሆነን በመያዝ ተለወጠ ለሚአደረየሚለው ቃል ይረታቸዋል። ከተለወጠ አደረ ሊባል አይችልምና። አደረየሚለውን ቃል በመያዝ አልተዋደም ለሚሉደግሞ ሆነ” የሚለው ቃል ይረታቸዋል
 
ተዋህዶ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚገልጥ ነው፡፡ ተዋህዶ እንደ አገባቡ ምሥጢረ ሥላሴንና ሥጋዌን የሚያብራራ ነው፡፡ ተዋህዶ የጉባዔ ስም ነው፡፡ ንስጥሮስን ያወገዘው የኤፌሶን ጉባዔ /431 ዓ.ም./ የሚታወቅበት ስም ነው፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ተዋህዶ ስመ ሃይማኖት ሆኗል፡፡ በአጭር ቃል ተዋህዶ ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ ማለት ነው፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ