የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጸጋና እውነት

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ማክሰኞ መጋቢት 27/2008 ዓ.ም.
 
“ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ”
/ዮሐ. 1፡14/፡፡
 እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በሕዝቡ መካከል መሆን ይፈልግ ነበር፡፡ እርሱ በሕዝቡ መካከል ካለ ለሁሉም በእኩል ይታያል ማለት ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን የተመረጠው የመገናኛው ድንኳን ነው፡፡ ራሱ እግዚአብሔር፡- “በመካከላቸውም አድር ዘንድ መቅደስ ይሥሩልኝ” ብሏል /ዘፀ. 25፡8/፡፡ መቅደሱም የመገናኛው ድንኳን ተብሏል፡፡ የእስራኤል ልጆች በድንኳኑ ዙሪያ ይሰፍራሉ፡፡ ሁሉም ከቤቱ ሲወጣ የሚያየው የማደሪያውን ድንኳን ነው፡፡ ስለዚህ ልቡን ያበረታል፡፡ ጠላቶቹን ሳይሆን የሚረዳውን አምላክ ያስባል፡፡ በምድረ በዳ ያለ ምክንያት የሚያኖረውን አምላክ አስቦ ቀኑን ለመዋል ድፍረት ያገኛል፡፡ የማደሪያው ድንኳን የጌታችንን ሰው መሆን ያብራራልናል፡፡ በማደሪያው ድንኳን ውስጥ ያሉት አገልግሎቶች በሙሉ ከመፍትሔ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ መሠዊያው የኃጢአት ስርየትን፣ የመታጠቢያው ሰሐን መንጻትን፣ መቅረዙ ብርሃንን፣ የገበታው ኅብስት ኅብረትን፣ እጣኑ ጸሎትን፣ ታቦቱ ኪዳንን ያመለክታሉ፡፡ የክርስቶስ የተቀደሰ ሥጋዌም የኃጢአት ስርየት፣ የልብ መታጠብ፣ ብርሃን፣ ከእግዚአብሔርና ከሰው ጋር ኅብረትን፣ አባ አባት የሚያሰኝ የልመና መንፈስን፣ ደግሞም አዲስ ኪዳንን ያገኘንበት ነው፡፡ አማኑኤል ማለት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የተባለበት ምሥጢር ነው፡፡

ስለዚህ ወንጌላዊው፡- “ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ” ያለው ለዚህ ነው፡፡ በእኛ አደረ የሚለው ባሕርያችንን ገንዘቡ እንዳደረገ ያሳየናል፡፡ ዛሬ ወደ ሰማይ ቀና ብንል ከሦስቱ አካላት እንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ የእኛን ሥጋ ለብሶ ይታየናል፡፡ እግዚአብሔር በመካከላችን እንዳለ ይሰማናል፡፡ ስለዚህ የጠላት ብዛት፣ የምድረ በዳ ስጋት፣ የቀኑ ፍርሃት ድል ይነሣል፡፡ በዚያ በብሉይ ኪዳን መቅደስ የእግዚአብሔር ክብር አልፎ አልፎ ይገለጥ ነበር፡፡ ሰውና እግዚአብሔር በተገናኙበት በዚህ የተቀደሰ ሥጋዌ ግን የመለኮቱ ሙላት ተገልጦ ይኖራል፡፡ “በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና” /ቆላ. 2፡9/፡፡ ጌታችንም ራሱን በቤተ መቅደስ መስሏል /ዮሐ. 2፡19-21/፡፡ ሰውና እግዚአብሔርን ያገናኘ ብቻ ሳይሆን ሰውና ሰውን ያገናኘ ነው፡፡ ሰውና መላእክት ማለት ምድራውያንና ሰማያውያን አብረው የዘመሩት በጌታችን መወለድ ነው፡፡ በቤተ መቅደሱ የነበረው አይሁድና አሕዛብን የሚለይ ትልቅ ግንብ ፈርሶ በቤተ ክርስቲያን አንድ የሆኑት በጌታችን መወለድ ነው፡፡ ትልቅ የኑሮ ደረጃ የነበራቸው ሰብአ ሰገልና ዝቅተኞቹ እረኞች በአንድነት የሰገዱት በጌታ መወለድ ነው፡፡ የጌታችን ሰው መሆን የተገናኘንበት ትልቅ ድልድይ ነው፡፡
አንድ ሕዝብን ብቻ የወከለው የኦሪት ግድግዳ የፈረሰው፣ ሰውና እግዚአብሔርን የለየው የኃጢአት ግንብ የተናደው፣ ሕዝብና አሕዛብን የለየው የአዋጅ ግድግዳ የፈረሰው፣ ወደ እግዚአብሔር የሚወስደውን መንገድ የዘጋው መጋረጃው የተቀደደው በጌታችን ሰው መሆን ነው፡፡ በእርግጥም እርሱ መገናኛ ነው፡፡ ሐዋርያው፡- “አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” ይላል /1ጢሞ. 2፡5/፡፡ አንድ መካከለኛ ስለሆነ በክርስቶስ ካልተገናኘን በሌላ መገናኘት አንችልም፤ ብንገናኝም መገናኘታችን ለመፍረስ ነው፡፡ እርሱ የተወለደው ከሕዝብና ከአሕዛብ ነው፡፡ በጌታችን የዘር ሐረግ ውስጥ ከአረማውያን የሆኑ ወገኖች አሉ፡፡ ከእስራኤል ብቻ አልተወለደም፡፡ መላውን ዓለም ባማከለ ልደት ተወልዷል፡፡
“ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ” /ዮሐ. 1፡14/፡፡ ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ቢወለድም ያ ልደት ግን የሁላችን ክብርና ደስታ ነው፡፡ የሰውን ዘር በወከለችው በድንግል ማርያም እግዚአብሔር በእኛ አደረ፡፡ ዘመድ ምንም ቢጣላ ዝምድናው አይፈርስም፡፡ የተመሠረተው በፈቃድ ላይ ሳይሆን በደምና በሥጋ ቋጠሮ ላይ ነውና፡፡ እግዚአብሔርም ዘመዳችን ሆነ፡፡ ላንለያይ በእኛ አደረ፡፡ “የዘመድ ቄስ እየፈታ ያለቅስ” እንደ ተባለው የዘመድ ካህን ሆኖ ይቅር እያለን ቃተተልን፣ እየፈታን አለቀሰልን፡፡ እንባውን እያፈሰሰ “አልዓዛር ወደ ውጭ ና” አለ /ዮሐ. 11፡38-43/፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ሲኖር አንድ ቀን መለኮታዊ ኃይሉን ራሱን ለመርዳት አልተጠቀመበትም፡፡ እኛን ለመርዳት ግን አጋንንትን ገሰጸ፣ የደዌያትን ጉልበት ሰበረ፣ ማዕበልን ቀዘፈ፣ ውኃውን ወደ ወይን ለወጠ፣…፡፡ እርሱ ግን ሲራብ ድንጋዩን ዳቦ አላደረገም፣ ሲገረፍ የገራፊዎቹን ክንድ አላደረቀም፣ የሕይወት ራስ ሳለ እንዲገድሉት ፈቀደ፡፡
ያዕቆብ ያየው መሰላል አንድ ጫፉ ምድር አንድ ጫፉ ሰማይ የነካው ሥጋዌን ያመለክታል፡፡ ራሱ ጌታችንም፡- “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ አለው” በማለት ለናትናኤል ተናግሯል /ዮሐ. 1፡52፤ ዘፍ. 28፡12/፡፡ አንድ ጫፉ ምድር መንካቱ ጸጋን ተመልቶ ያለውን፣ አንድ ጫፉ ሰማይን መንካቱ እውነት ተመልቶ በእኛ አደረ ያለውን ይገልጣል፡፡ የጌታችን ሰው መሆን ጸጋና እውነትን ለማስፈን ነው፡፡ ጸጋ ሰው በቸርነቱ የሚድንበት ምሥጢር ነው፡፡ እውነት ደግሞ ፍትሕ የሚሟላበት ነው፡፡ በመስቀል ላይ ጸጋና እውነት ተከናወነ፡፡ ጸጋው መዳናችን እውነት ክርስቶስ ለእኛ መከራ መቀበሉ ነው፡፡ እግዚአብሔር የራሱን የፍትሕ ጠባይ አርክቶ የራሱን ፍቅር የገለጠው በዚህ ሥጋዌ ነው፡፡ ጸጋና እውነት አይለያዩም፡፡ ጸጋ እውነትን ያከብራል፡፡ እውነትም ጸጋን ያመጣል፡፡ የክርስቶስ መስቀል በራሱ የሚዛን ቅርጽ አለው፡፡ ያ ሚዛንም ነቢዩ ዳዊት “ምሕረትና እውነት” እያለ ሲዘምር የኖረው ወንጌላዊው ጸጋና እውነት በማለት የገለጠው ነው /መዝ. 100፡1/፡፡
ነቢዩ፡- “ምሕረትና እውነት ተገናኙ ጽድቅና ሰላም ተስማሙ። እውነት ከምድር በቀለች፥ ጽድቅም ከሰማይ ተመለከተች” ያለው ለዚህ ነው /መዝ. 84፡10-11/፡፡ እነዚህ ሁለት ነገሮች አልገናኝ ብለው ለዘመናት ኖረዋል፡፡ እግዚአብሔር ግን ፍቅሩ ፍርዱን የማያጓድልበት፣ ፍርዱም ፍቅሩን የማያስቀርበት ነውና ይኸው በምሥጢረ ሥጋዌ ገለጠው፡፡ እናት ልጇን በጣም መውደዷ ፍርድን ያሳጣታል፡፡ በዓለም ላይ ፍቅር ፍርድን፣ ፍርድም ፍቅርን እያሳጣ ኖሯል፡፡ በክርስቶስ ግን ምሕረትና እውነት ተገናኙ፡፡ ነቢዩ ቤተ ልሔም በመንፈስ ተገኝቶ የዘመረው ዝማሬ የልደት አምኃ/እጅ መንሻ/ ነው፡፡
ምስጋና ለእግዚአብሔር
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ