የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ክብሩን ማየት

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ሐሙስ መጋቢት 29/2008 ዓ.ም.
                      ክብሩን ማየት  
 
“አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን”
/ዮሐ. 1፡14/፡፡
ሃይማኖታዊ አንቀጾች ምሥጢር የሚባሉት የቻልነውን ተገንዝበን በእምነት የምንቀበላቸው ስለሆኑ ነው፡፡ ደግሞም የመጽሐፍ፣ የጉባዔያት ገደብ ስላላቸው አልፈን በራሳችን የማንተነትናቸው ስለሆኑ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ የምንደነቅባቸውና በመንፈሳዊ ተመስጦ የምንጠፋባቸው ስለሆኑ ነው፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆንም ምሥጢር ነውና በእምነት የምንቀበለው፣ መጻሕፍትና ጉባዔያትን አልፈን መላምት የማንሰጥበት ከሁሉ በላይ የመደነቅ ዝማሬ የምናቀርብበት ነው፡፡ የሰው ልጅ የመዳን ልመና ቢያቀርብም ከዚያ አልፎ እግዚአብሔርን ሰው ሁነህ አድነኝ አይልም፡፡ ሰው ለመሆን ፈቃዱ የራሱ የእግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህ ነው ጌታችን በተወለደ ቀን ቅዱሳን መላእክት፡- “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ” በማለት የዘመሩት /ሉቃ. 2፡14/፡፡ ፈቃዱ የራሱ የእግዚአብሔር ነውና ክብር ይገባዋል አሉ፡፡ የመወለዱም ትርፍ ሰላምና በጎ ፈቃድ ማለት ነጻነት ነው፡፡ እነዚህ መላእክት የነጻነትን ትርጉም አስቀምጠዋል፡፡ ነጻነት ማለት በጎ ፈቃድ ትክክለኛውን ነገር የማድረግ መብት ነው፡፡ ሰው መሆን ግን የራሱ የመለኮት ፈቃድ ነው፡፡

እኛ ጨረቃ ላይ እግሮቻቸው ስለቆሙ አዋቂዎች ይደንቀናል፡፡ የሚደንቀው ጨረቃን መርገጥ ሳይሆን የእግዚአብሔር ልጅ የእኛን ምድር በሥጋ መርገጡ ነው፡፡ በመለኮት ምልአቱ ያልተለያትን ዓለም በሥጋዌው ደግሞ ተመላለሰባት፡፡ የዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ ልጅ ዓለማየሁ ቴዎድሮስ በልጅነቱ ተሰድዶ እንግሊዝ አገር መሞቱ ያሳዝናል፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉ እያለው እንደሌለው ሆኖ በዚህች ምድር ላይ መንከራተቱ ይደንቃል፡፡ ምሥጢረ ሥጋዌ የማይጨረስ ትንታኔ ነው፡፡ ምሥጢር ነውና የምንችለውን አውቀን የማንችለውን አምነን እናርፋለን፡፡ ምሥጢር ድብቅ ማለት ሳይሆን በምናውቀው ጥቂት ነገር ውስጥ የማናውቀው ብዙ ነገር እንዳለ የምንገነዘብበት ነው፡፡
“ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ” ካለ በኋላ ቃል ሥጋ በመሆኑ የባሕርይ ክብሩን ያጣ እንዳይመስለን “አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን” ይላል፡፡ አየን የሚለውን ቃል ወንጌላዊው ብዙ ጊዜ ያነሣዋል፡፡ ያየ ትልቅ ምስክር ነው፡፡ በመልእክቱ ላይም፡- “ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን” ይላል /1ዮሐ. 1፡1/፡፡ ዮሐንስ ያየው ዘመን የሚቆጠርለትን የክርስቶስን ሥጋዌ ብቻ ሳይሆን ዘመን የማይቆጠርለትን ቅድምናውንም ነው፡፡ “ከመጀመሪያ የነበረውን” ይላልና፡፡ በቅድምና የነበረውና በዓይኑ ያየው አንዱ ክርስቶስ እንደሆነ ይገልጣል፡፡ ቀዳማዊው ደኃራዊ መሆኑ ይደንቃል፡፡ ዘመን የማይቆጠርለት ዘመን የሚቆጠርለት መሆኑ ይገርማል፡፡ ክርስቶስ በሥጋ በነበረበት ዘመን ብንኖር እንመኝ ይሆናል፡፡ ክርስቶስ ግን ያኔም አሁንም የሚታየው በእምነት ነው፡፡ በሥጋዊ ዓይናቸው ያዩት አይሁድ ሰቅለውታል፣ በእምነት ያዩት ደቀ መዛሙርት ሰግደውለታል፡፡ ዮሐንስ በርግጥም አይቷል፡፡ ዮሐንስ፣ ያዕቆብና ጴጥሮስ የምሥጢር ደቀ መዛሙርት የሚባሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ደቀ መዛሙርት ብዙ ነገር አይተዋል፡፡ ስላዩም ያዕቆብ ከሐዋርያት የመጀመሪያው ሰማዕት ሆኗል /የሐዋ. 12፡1/፡፡ ጴጥሮስም በ67 ዓ.ም የቁልቁሊት ተሰቅሎ በሮም አደባባይ ሰማዕት ሆኗል፡፡ ዮሐንስም በደሴተ ፍጥሞ ተግዞ በ96 ዓ.ም. በሰማዕትነት አገልግሎቱን ፈጽሟል፡፡ ማየት ጽኑ ያደርጋል፡፡ እነዚህ ደቀ መዛሙርት በቀረቡት ቁጥር የጌታችን መለኮትነት ይታያቸው ነበር፡፡ በቀረቡ ቁጥር የሚያናንቅ የዓለም መንፈስ ነው፡፡
ሙሴ ይህን ክብር ለማየት ናፍቋል፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር አምስት መቶ ጊዜ ያህል ቃል በቃል ሲነጋገር አሁን ፊቱን ለማየት ናፈቀ፡፡ “እባክህ ክብርህን አሳየኝ አለ” /ዘፀ. 33፡18/፡፡ ሙሴ በእግዚአብሔር ፊት ቆይቶ ሲመጣ ፊቱ እንደ ፀሐይ አበራ፡፡ እስራኤል ፊቱን ማየት አልቻሉምና ፊቱን በመጋረጃ ከልሎ አናገራቸው /ዘፀ. 34፡29-35/፡፡ ሙሴ ብርሃን ተስሎበት ሳለ እስራኤል የእርሱን ፊት ማየት እንዳልቻሉ ዘንግቶ ራሱን እግዚአብሔር ልይህ አለ፡፡ እግዚአብሔር ፍጡር በክብሩ አይቶት አይድንምና መልሱን አዘገየበት፡፡ ዘመኑ ሲደርስ መለኮት በሥጋ መጋረጃ ተሰውሮ መጣ፡፡ ሙሴ ክብሩን ማየት ለምኖ ነበር ሳያይ ሞተ፡፡ በደብረ ታቦር ግን ከሞት ተነሥቶ የጌታን ፊት አየ፡፡ እግዚአብሔር ከሞት ቀስቅሶም ጸሎትን ይመልሳል፡፡ ብዙ ነቢያት ይህን ሥጋዌ ለማየት ናፍቃዋል፡፡ ራሱ ጌታችን፡- “እውነት እላችኋለሁ፥ ብዙዎች ነቢያትና ጻድቃን የምታዩትን ሊያዩ ተመኝተው አላዩም፥ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ተመኝተው አልሰሙም” ብሏል /ማቴ. 13፡17/፡፡
ይህንን ክብር ሙሴ ከመቃብር ተነሥቶ ሲያይ ወንጌላዊውም ከጴጥሮስና ከዮሐንስ ጋር ሆኖ በደብረ ታቦር ላይ አይቷል /ማቴ. 17፡1-8/፡፡ ወንጌላዊው ኢየሱስ ክርስቶስ የአብ አንድ ልጅ መሆኑን ልጅነቱም የክብር መተካከል እንደሆነ ይመሰክራል፡፡
እኛም አይተንሃል፡፡ እናመሰግንሃለን፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ