የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የመጥምቁ ዮሐንስ ምስክርነት

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ሰኞ ሚያዝያ 3/2008 ዓ.ም.
                                          
 
“ዮሐንስ ስለ እርሱ መሰከረ እንዲህም ብሎ ጮኸ። ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበረና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል፤ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነበረ” /ዮሐ. 1፡15/፡፡
ወንጌላዊው መጥምቁ ዮሐንስን ለሁለተኛ ጊዜ ያነሣዋል፡፡ በቁጥር 6 ላይ፡- “ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ” ብሎ ነበር፡፡ ወንጌላዊው ዮሐንስ መጥምቅን በማንሣት ክርስቶስ የከበረ መሆኑን ገልጦ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ራሱ መጥምቁ ዮሐንስ በአንደበቱ የተናገረውን በመጥቀስ የክርስቶስን ታላቅነት ይናገራል፡፡ ወንጌላዊው የክርስቶስን አምላክነት ለመግለጥ ለምን ተጨነቀ? ስንል መልእክቱ ለእስራኤልና ለአሕዛብ የተጻፈ በመሆኑ ክርስቶስን እንደ አንድ ሰው ብቻ ያዩትን አይሁድንና አሕዛብን ወደ መለኮታዊ ክብር ለማድረስ ነው፡፡ አይሁድ በትንቢት ያገለገሉትን አሁን በፍጻሜው እንዲሰግዱለት፤ አሕዛብ ሎጎስ ብለው ሲተርኩለት የነበረው በሥጋ የመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ለማስገንዘብ ይተጋል፡፡ መዳን የሚገኘው ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክ መሆኑን በማመን ነው፡፡ ይልቁንም የእግዚአብሔር መንግሥት የምትወረሰው በልጅነት ነው፡፡ ልጅነት ብቃትን ሳይሆን መወለድን ብቻ የሚጠይቅ መስፈርት ነው፡፡ ልጅነትን ለማግኘት ደግሞ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ማመን ያስፈልጋል፡፡ ልጆች የምንባለው በልጁ ነውና፡፡ “በወልድ ውሉድ፣ በክርስቶስ ክርስቲያን የተሰኛችሁ” የሚለው የሰላምታ ዘርፍ እጅግ ያማረና የጠለቀ ነው፡፡

ዮሐንስ መጥምቅ ስለ ክርስቶስ ምስክር ነበረ፡፡ ጌታችን ምስክር እንጂ ጠበቆች የሉትም፡፡ ምስክር ያየ የሰማ ነው፡፡ ጠበቃ ግን ስለ ገበያ የሚሟገት ነው፡፡ ምስክር አንገቱን ይሰጣል፡፡ ጠበቃ ሲረቱ ወደ ኋላ ይላል፡፡ ዮሐንስ መጥምቅ ግን ምስክር ነው፡፡ ምስክርና ሰማዕት በብዙ ቋንቋዎች ተመሳሳይ ትርጉም ያለው ነው፡፡ ዮሐንስ መሰከረ በመጨረሻም ሰማዕት ሆነ፡፡ ዮሐንስ የመሰከረው፡-
1-  በመጮኽ ነው፡፡
2-  የክርስቶስን ቀዳማዊነት በመናገር ነው፡፡
3-  ከከበሩት የከበረ መሆኑን በማወጅ ነው፡፡
4-  እርሱም በዮሐንስ እጅ የተጠመቀው ራሱ ክርስቶስ ነው፡፡
የጽድቅ ጩኸቶች ከተራ ጩኸቶች ይለያሉ፡፡ ጌታችን በመስቀል ላይ ጩኸት አሰምቷል፡፡ “በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ፦ ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ? ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህም። አምላኬ አምላኬ፥ ስለ ምን ተውኸኝ? ማለት ነው” /ማቴ. 27፡46/፡፡ “ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ። አባት ሆይ፥ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ አለ። ይህንም ብሎ ነፍሱን ሰጠ” /ሉቃ. 23፡46/፡፡ በመስቀሉ ዙሪያ ብዙ ጩኸቶች ነበሩ፡፡ “ይሰቀል” የሚል ጩኸትም ነበር፡፡ የጌታችን ጩኸት ግን ፍርድን ፍለጋ ወይም ሥቃይ የወለደው አይደለም፡፡ የኃጢአት ዋጋ መከፈሉን የሚገልጥና የነፍስ አድራሻ እግዚአብሔር መሆኑን የሚያውጅ ነው፡፡ ሰው እነዚህን ሁለት ነገሮች ማወቅ አለበት፡፡ ኃጢአቱ ያውከዋልና ስርየቱን፣ ከሞት በኋላ አይታየውምና የሰማይ መንገዱን መስማት አለበት፡፡ ጌታችን ለራሱ ሳይሆን ለእኛ ጮኸ፡፡ ዮሐንስ መጥምቅም በአዋጅ ድምፅ ጮኸ፡፡ መጮኽ ለምን አስፈለገው? አይሁድና ሕዝቡ ክርስቶስን አቃለው እርሱን ያከብሩት ነበር፡፡ ስለዚህ ዮሐንስ ለእኔ ያላችሁ ክብር ትክክለኛ የሚሆነው የክብር ራስ የሆነውን አምላክ ስታከብሩት ነው በማለት ጮኸ፡፡
 
“ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበረና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል፤ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነበረ” አለ /ዮሐ. 1፡15/፡፡ ዮሐንስ ጌታችንን በሥጋ ልደት ስድስት ወር ይበልጠዋል፡፡ ከኋላ የመጣ ከፊት የሚሆነው አንዳንዴ በክብር ሊሆን ይችላል፡፡ በዘመን ሊሆን ግን አይችልም፡፡ ዮሐንስ ግን በዘመንም በክብርም ይበልጠኛል እያለ ነው፡፡ ስለዚህ ክርስቶስ ከሥጋ ልደቱ በፊት ህልውና እንዳለው እየመሰከረ ነው፡፡ ወንጌላዊው ስለ ቃል መጀመሪያነት በመናገር ይጽፋል፡፡ አሁን ደግሞ መጥምቁ ዮሐንስን ምስክር ያደርጋል፡፡ ጌታችን በሥጋ ከዮሐንስ በኋላ ለምን መጣ? ስንል ዮሐንስ የንጉሥ መልእክተኛ ነውና ከፊት ፊት እየሄደ መንገዱን እንዲጠርግ፣ የሰውን ልብ ለመሢሁ እንዲያዘጋጅ ነው፡፡ በሥጋ ልደትም በአገልግሎትም ዮሐንስ ቢቀድምም ንጉሥ ሲመጣ ግን ስፍራውን ለቀቀ፡፡ በሰማዕትነትም አገልግሎቱን በቶሎ ፈጸመ፡፡ ከእርሱ በፊት የነበረው ከእርሱ በኋላ ሲመጣ ተደንቋል፡፡ ዘላለማዊ ጌታ በዘመን መጠን ውስጥ መግባቱ አስገርሞታል፡፡ የሚገርመው ደግሞ ለነማቱሳላ ሰፊ ዘመንን የሰጠ ጌታ በሠላሣ ሦስት ዓመቱ መሞቱ ነው፡፡ አንድ አባት፡- “ሰው የሚፈልገውን ካየ የሚጠብቀው ሞቱን ነው” ብለዋል፡፡ የእኛን መዳን ለማየት ጌታ ፈጥኖ ሞተ፡፡ ክርስቶስ የከበረው ሰው ክቡር ስላለው ሳይሆን በራሱ የከበረ ነው፡፡ የሰው ክብር፣ ክብርን አይጨምርለትም፡፡ ብናከብረው ግን እንከብራለን፡፡
 
“እግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፥ በምድርም መካከል መድኃኒትን አደረገ” ይላል /መዝ. 73፡12/፡፡ ሕዝብ በሌለበት ንጉሥ የለም፡፡ ሕዝብ በሌለበት ነግሠናል የሚሉትን ልንስቅባቸው እንችላለን፡፡ እግዚአብሔር ግን ዓለም ሳይፈጠር፣ ዘመን ሳይቆጠር ንጉሥ ነው፡፡ በራሱ የከበረ ነው፡፡ ያ ንጉሥ በምድር መካከል ማለት በቀራንዮ መድኃኒትን አደረገ፡፡ ነቢዩ በትንቢት የክርስቶስን ክብረትና አዳኝነት ተረከ፡፡ ዮሐንስ መጥምቅ ፍጻሜውን አወጀ፡፡
ምስጋና ለተገለጠው ብርሃን ለክርስቶስ ይሁን፡፡

ያጋሩ