የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሕግና ጸጋ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ዓርብ ሚያዝያ 7/2008 ዓ.ም.
                                          
 
“ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ” 
/ዮሐ. 1፡16/፡፡
 ሕግና ጸጋ ተናባቢ የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው፡፡ ብሉይ ኪዳን እኛ በዚህ ስያሜ ብንራውም አይዳውያን ግን ቶራህ ወይም ሕግ ይሉታል፡፡ በጌታችንም አገላለጥ ብሉይ ኪዳን ሕግና ነቢያትይባላል /ማቴ. 11፡13፤ ሉቃ. 24፡44/፡፡ የሕግን ትክክለኛ ፍቺ አለማወቅ ከእግዚአብሔር ንግሥት ሊያጎድል ይችላል። አይሁድ ወደ ክርስቶስ በሚመራው ሕግ ክርስቶስን የተቃወሙት የሕጉን ትክክለኛ ትርጉም ባለመረዳትና ሕጉን ያለ ክርስቶስ በመተርጎም ነው። ለሄሮድስ ክርስቶስ የት እንደሚወለድ ትንቢት ጠቅሰው የነገሩት የአይሁድ ካህናት ናቸው /ማቴ. 2፡4/፡፡ በትንቢት ያመኑትን ክርስቶስ ግን በፍጻሜ ሲመጣ ሰቀሉት፡፡ አይሁዳውያን በጣም ሕግን አፍቃሪ ናቸው፡፡ ዛሬ እንኳ ከአገሩ ሕዝብ ዘጠና ከመቶ ሕግ አዋቂ ነው፡፡ በነፍስ ወከፍ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ አንድ ጠበቃ አለ፡፡ የሰው ልጅ ሕግን እንደ መውደዱ ሕግን መጠበቅ አልቻለም፡፡ በዓለም ላይ ያለው የፓርላማ ሥርዓት ሕግን ሲያረቅቅ የሚውል ነው፡፡ በየዕለቱ ሕግ ይረቅቃል፡፡ ሕጉ ግን እስረኞችንና ወንጀለኞችን አበዛ እንጂ ጻድቃንን አላበዛም፡፡

አይሁድም በጣም ያፈቀሩትና ተመክተውበት ክርስቶስን የገፉበት ያ ሕግ የሚከሳቸውና የሚኰንናቸው ነበር፡፡ የሰው ልጅ ሕግን በጣም የሚወደው በራሱ የማድረግ አቅም ያለው ስለሚመስለውና የእኔ የሚለውን በጎነት ስለሚፈልግ ነው፡፡ ሰው ግን ያለ ክርስቶስ እርዳታ ሕግን መፈጸም በፍጹም አይችልም /ዮሐ. 15፡5/፡፡ ሕጉ በጸጋው የተተካበት ሕግን ለመሻርና መረኖችን በዓለም ላይ ለማብዛት ሳይሆን ጸጋው የመታዘዝ አቅም እንዲሰጥ ነው፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “ኃጢአት አይገዛችሁምና፤ ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደላችሁምና” ይላል /ሮሜ. 6፡14/፡፡ ኃጢአት አይገዛችሁም የሚል ዋስትና ሕጉ መስጠት አልቻለም፡፡ ሕጉ ትእዛዝ እንጂ ኃይል አልነበረውም፡፡ ከሕግ በታች መሆን ማለት ሁለት ፍቺ አለው፡፡ በሕግ አገዛዝ ሥር መሆንና በሕግ ተጠያቂነት ሥር መሆን ነው፡፡ በዚህ ክፍል ላይ ከሕግ በታች አይደላችሁም ማለት በማይረዳው በሕግ ሥር ሳይሆን ለቅድስና በሚረዳው ከጸጋው አገዛዝ ሥር ናችሁ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ኃጢአት አይገዛችሁም ይላል፡፡ ሕጉ ሊፈጸም ያልቻለው ሕጉ በራሱ ኃይል አልባ በመሆኑ ነው፡፡ ማለት ያዝዛል እንጂ ያዘዘንን እንድንፈጽም ኃይል አይሰጠንም፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ሥጋም ደካማ ነው፡፡ ሕጉን የሠራውና ሥጋን የፈጠረው አንዱ እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህ ለሠራው ሕግና ለፈጠረው ሥጋ ራራ፡፡ ሕጉንና ሥጋን የሚታደግ ማለት ኃይል በመስጠት ሕጉ በሥጋችን እንዲፈጸም የሚያደርግ ኪዳን አዘጋጀ፤ እርሱም ጸጋ ይባላል፡፡ /ሮሜ. 8፡3-4/፡፡ አባቶቻችን ይህን በሃይማኖተ አበው በግልጽ አስቀምጠዋል፡-

“ሕግ የተሰጣቸውም ቢሆኑ እነርሱ ሕግን መፈጸም ስለተሳናቸው ሕጉም እነርሱን ማዳን ስለተሳነው እግዚአብሔር ሁለቱንም ወገኖች ለማዳን ተቀዳሚ ተከታይየሌለው ልጁን ወደ ዓለም ላከ፤ እርሱም መጥቶ ሕግን መፈጸም የተሳናቸው ሕጉንእንደፈጸሙ እንዲሆንላቸው ግዙፍ አምላክ የፈለጉ ሁሉም ረቂቁን አምላክ በግዙፍ መልክ ዐይተው ደስ እንዲላቸውና አሳባቸው እንዲፈጸምላቸው በሥጋ ተገለጠ፡፡ ስሙን እንዲቀድሱ ክብሩንእንዲወርሱ አደረገ፡፡ በዚህ ምክንያት ቀድሞ ነቢያትን ቃል በቃል ያነጋገራቸው ፊቱን ለማየት ግን የማይቻላቸው መሆኑን የገለጠላቸው አምላክ ሰው ሆኖ ሥጋ ለብሶ በተገለጠ ጊዜ ሐዋርያቱ መልኩን አይተው ትምህርቱን ከቃሉ ሰምተው፤ አምላክነቱን በሥራው ተረድተው ሃይማኖትን በማየት በመስማት አረጋገጡ ሃይማኖትን ሰምተው ከአስተማሩ ከነቢያት ይልቅ ሕያው ባሕርይ ራሱን የገለጠላቸው ሐዋርያት /የሐዋ.ሥራ1÷3/ እግዚአብሔርን ከቶ ያየው የለም በአባቱ ዕሪና ያለ አንድ ልጁ ነገረን እንጂ /ዮሐ.1÷18/ ዓለም ሳይፈጠር የነበረውን በዓይናችን አየነው፤ ሲያስተምርም በጆሮአችን ሰማነው በእጃችንም ዳሠሥነው /1ዮሐ. 1÷1/ ብለው መሰከሩ” /ሃይማኖተ አበው መቅድም ተመልከቱ /፡

ሐዋርያው ጳውሎስ አሁንም አፍም ሁሉ ይዘጋ ዘንድ ዓለምም ሁሉ ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች ይሆን ዘንድ ሕግ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንዲናገር እናውቃለን” ብሏል /ሮሜ. 3፡19/፡፡ እግዚአብሔር እጅን በአፍ ላይ ማስጫን ወይም ዝም ማሰኘት ለምን ፈለገ ስንል ሰው እችላለሁ ባይ ነው፡፡ ደካማነቱን ካላመነ ደግሞ ክርስቶስ ያስፈልገኛል ብሎ ስለማያምን ነው፡፡ እግዚአብሔርም ሕግን ሰጥቶ አቅሙን ያሳየዋል፡፡ ያን ጊዜ በቸርነትህ ይላል፡፡ ሕግ አፍ ያለው ከሕግ በታች ላሉት ነው፡፡ ማለት ለተከሳሾችና ለፍርደኞች ነው፡፡ አሁን ዝም ብለን ብናዳምጥ ሕግ ያለ አይመስልም፡፡ አንድ ሌባ ግን ነጥቆ ቢሮጥ ተሰራቂው ይጮኻል፣ ፖሊስ ይሮጣል፣ ዐቃቤ ሕግ ፋይል ይከፍታል፡፡ ሕጉ አፍ ያለው ወንጀል ባለበት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ሕጉ ስለ ሰረቅን ይቀጣናል እንጂ ስላልሰረቅን አይሸልመንም፡፡ ባሕርይው መቅጣት እንጂ መሸለም አይደለም፡፡ ለዚህ ነው በሕግ ሥራ መጽደቅ ያልተቻለው /ሮሜ. 3፡20/፡፡ ጸጋ ግን ሕይወት ሰጥቶ ያሠራል፣ ዳግመኛም ሽልማትን ያሰጣል፡፡ ያማ ባይሆን ኖሮ በሕጉ ዘመን የነበሩ ደጋግ አባቶች ገነት ተቆልፎባቸው እስከ ክርስቶስ መምጣት በሲኦል ባልቆዩ ነበር፡፡ የገነትን በር የከፈተው የሰው መልካምነት ሳይሆን የክርስቶስ ደም ነው፡፡ ወንበዴውን ቀዳሚ አድርጎ ያስገባው በደሙ የተገኘው ጸጋ ነው፡፡ ጸጋ ነጻ ስጦታ ነው፡ ነጻ ሁሉ ነጻ አይደለም፡፡ እኛ ነጻ እንድናገኝ የከፈለ ወገን ስላለ ነው፡፡ የጸጋም ክፍያ ክቡር ደሙ ነው፡፡
 ሕጉ ያለ ጸጋው ፍጻሜ የሌለው ጅማሬ ነውጸጋው ያለ ሕጉ ጅማሬ የሌለው ፍጻሜ ነው። ሕግ ወደ ጸጋው ሚያደርስ መሰላል ወይም ድልድይ ነው። ሕጉ ያለ ጸጋ አስፈሪ ነውጸጋው ያለ ሕጉ መነሻ የሌለው ነው፡፡ ሕጉ የሰውን የኃጢአት ልክ ያሳየ ነውጸጋው ግን የእግዚአብሔርን የፍቅሩን ልክ የገለጠ ነው። ሕጉ ውሃ ሽቅብ እንደማይፈስ ሰውም ለእግዚአብሔር ማድረግ እንደ ተሳነው ያሳየ ነውጸጋው ግን ውሃ ቁልቁል ያለከልካይ እንደሚፈስ የእግዚአብሔር ቸርነት ተገለጠበት ነው። የሕግና የጸጋን ትክክለኛ ትርጉም መረዳት ከክርስቶስ ጋር እድንኖር ያደርገናል። አይሁዳውያን ሕጉ ተስፋ ሳለ እንደ ፍጻሜ ስለ ተቀበሉት ክርስቶስን እንዲገፉ አደረጋቸው። የሕጉንና የጸጋን ትርጉም ወንጌላዊ ሲያሳያቸው ሕጉ በሙሴ  ጸጋው ግን በኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ሕጉ በመልእክተኛ የተከናወነ ነው፣ ጸጋው ግን በራሱ በእግዚአብሔር ከተከናወነ ጸጋው ይበልጣል፡፡ ሕጉ አንድ ሕዝብን ማለት እስራኤልን አድራሻ ያደረገ ነው፡፡ ጸጋው ግን መላውን ዓለም አድራሻ ያደረገ ሰፊ ኪዳን ነው፡፡ ሕጉ በእንስሳት ደም የጸና ነው፣ ጸጋው ግን በክርስቶስ ደም የጸና ነው፡፡ ሕጉ ምድራዊ ተስፋን የሚያወርስ ነው፣ ጸጋው ግን የዘላለም ሕይወትን የሚያጎናጽፍ ነው፡፡ ሕጉ በጊዜያዊነት ሲሰጥ ጸጋው ግን በዘላለማዊነት ተሰጥቶአል፡፡  ሕጉ በድንጋይ ጽላት ላይ ሲጻፍ ጸጋው ግን በልባችን ላይ ተጽፎአል፡፡ ሕጉ ሲያስገድድ ጸጋው ግን ያስፈቅዳል፡፡ ሕጉ ሲያዝ ጸጋው ግን ኃይል ይሰጣል፡፡ ሕጉ ሲከስስ ጸጋው ግን ይሸፍናል፡፡ ሕጉ ወደ ክርስቶስ ሲያመለክት ጸጋው ግን ፍጻሜውን ያበስራል፡፡ ሕጉ ብዙ ካህናትን ሲሾም ጸጋው ግን አንዱን ሊቀ ካህን ያሳያል፡፡ ሕጉ ብዙ መሥዋዕቶችን ሲያቀርብ ጸጋው ግን በአንዱ መሥዋዕት ድኅነትን ይሰጣል፡፡ ሕጉ ኃጢአትን ሲያዳፍን ጸጋው ግን ኃጢአትን ያጠፋል፡፡ ሕጉ ቁጣን ሲያበርድ ጸጋው ግን ቁጣን ያጠፋል፡፡ ሕጉ ሲኰንን ጸጋው ግን ያጸድቃል፡፡
ከሕግ ወደ ጸጋ ሲጓዙ ንጋት ነው፤ ከጸጋ ወደ ሕግ ሲጓዙ ግን ምሽት ነው፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ