የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የዮሐንስ ወንጌል ትርጓሜ / 4

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ሐሙስ ጥር 26/2008 ዓ.ም
የዮሐንስ ወንጌል መቼት/መችና የት/

ዮሐንስ ወንጌሉን የጻፈው ፍጥሞ በምትባል ሞቃታማና ዓለታማ ደሴት ላይ ታስሮ ነው /ራእ. 1፡9/። ዮሐንስ ሲታሰር የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን መሪ ነበር። ይህች የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን በጳውሎስ ተመሥርታ ጢሞቴዎስ አገልግሏታል። ዮሐንስም እስከ እስራቱ ድረስ በዚህች ቤተ ክርስቲያን አገልግሏል። የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ታላላቅ አባቶች ያገለገሏት ቤተ ክርስቲያን ናት። ይህች ቤተ ክርስቲያ በክፉ ዓለም ላይ መልካነቷን የጠበቀች በዘመናዊው ዓለም ውስጥ የላለሙን የመረጠች በጣኦት መንደር ሕያው ጌታን ያከበረች፣ በዝሙት መዲና ንጽሕናን ጌጥ ያደረገች ቤተ ክርስቲያን ናት። ከኤፌሶን መልእክት እንደምንረዳው ይህች ቤተ ክርስቲያን ስፍራዋን ያወቀች ነበረች። ስፍራዋም ከጌታችን ከኢየሱስ ቀኝ በሰማይ ነበረ /ኤፌ. 1፡21፤2፡6/። ይህችን ቤተ ክርስቲያን እየመራ ሳለ ዮሐንስ ወደ ግዞት ተወሰደ። ዛሬ ይህች ቤተ ክርስቲያን እንኳን ኅብረቷ ከተማዋም የለም። በአሸዋ የተቀበረች ከተማ ሆናለች። ምክንያቱም በራእይ  ዮሐንስ ላይ እንደ ተገለጠው የቀደመ ፍቅሯን ትታ ነበር /ራእ. 2፡4/

ዮሐንስም በመጨረሻ በራእዩ አገለገላት /ራእ. 2፡1-7/። ዮሐንስ ብዙ ራእዮችን ያየው በሞቃታማዋ ደሴት ላይ ኖ ነው። ደሴት የተፈጥሮ እስር ቤት ነው። የባሕር ፍርሃት ስላለ ማንም ሊንቀሳቀስ አይችልም። ደሴት መዝናኛ የሚሆነው ጀልባ እስካለ ድረስ ነው። ጀልባው የተወሰደበት ጎብኚ ወደ እስረኛነት ይቀየራል። ዮሐንስ የምድሩ ሲዘጋበት የሰማይ መስኮት ተከፈተለት። ደሴቱ ዝግ ቢሆንም ሰማይ ግን ክፍት ነው። ዙሪያውን ነገሥታት ቢያጥሩትም ወደ ሰማይ ግን ማጠር አይችሉም። በተዘጋ ሰማይ ዙሪያው ክፍት ከሚሆን በተከፈተ ሰማይ ዙሪያው ዝግ ቢሆን ይሻላል። ዮሐንስ ራእዩን የመቀበሉ ምክንያት እስረኛ መሆኑ ወይም ደሴት ላይ መኖሩ ሳይሆን በጌታ ቀን በመንፈስ መሆኑ ነው/ራእ. 1፡10/፡፡ የጌታ ቀን በብሉይ ኪዳን ሰንበት የሚል መጠሪያ ያላት ናት። ቀኑ ሊለያይ ቢችልም ጽንሰ አሳቡ ግን አይለያይም። ሰንበት በሥጋ አርፈን በመንፈስ እግዚአብሔርን የምናስስበት ነው። ከአይሁ ጋር ያለን ልዩነት እነርሱ ቀኑን ሲያከብሩ እኛ ግን የሰንበትን ጌታ እናከብርበታለን። ሰንበት የተፈጥሮ ሕግ እንጂ የኦሪት ሕግ አይደለም /ዘፍ. 2፡2/። ስንፈጠር እንድናርፍና እንድናመልከ ሆነን ተፈጥረናል።ሥጋዊ ድካማችን እንኳ ሰንበትን ይናፍቃል። ሰንበት የቤተሰብ ወይም የመዝናናት ቀን አይደለም። ሰንት የጌታ ቀን ነው በዚህ ቀን በሥጋ ስንሆን የያዝነው ራእይ ይጠፋናል። በመንፈስ ስንሆን ግን ዘመናትን የሚያይ ራእይ እንቀበላለን።

ዮሐንስ ወንጌሉንም የጻፈው በዚሁ በፍጥሞ ደሴት ላይ ሳለ ነው። ይህ በ90 ዓ.ም. ገደማ መሆኑ ነው። ዮሐንስ የመጨረሻው በሕይወት የቆየ ሐዋርያ ነው። የመጨረሻውንም የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ራእየ ዮሐንስን የጻፈልን ነው። የዮሐንስ ወንጌል የተጻፈው ከወንጌላት ሁሉ መጨረሻ ነው። ስለዚህ ስቱ ወንጌላት ያልዘገቡትን ዘገባዎች አስፍሯል። ይህ ዮሐንስ በሥጋ እንዳልሞተ ይታመናል /ዮሐ. 21፡23/። ካልሞተም ሞትን መቅመሱ የማይቀር ነው። ዘመነ ሐዋርያት ከ33-100 ዓ.ም ነው። ዮሐንስ በ96 ዓ.ም አገልግሎቱን ከፈጸመ የመጨረሻው ዋርያ ነው።

 ለእኛም ራእይን ያብዛልን።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ