የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አንድ ልጁ እርሱ ተረከው

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ሰኞ ሚያዝያ 10 2008 ዓ.ም
 
 
“መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው” /ዮሐ. 1፡18/፡፡
እግዚአብሔር የማይታይ አምላክ ነው፡፡ የሚታየውንና የማይታየውን ዓለም ግን ፈጥሮ ይገዛል፡፡ የሚታየው ዓለም መሠረት የማይታየው እግዚአብሔር ነው፡፡ የሚታዩ ግዙፍ ሕንጻዎች መሠረት የማይታየው የሰው ኅሊና ነው፡፡ የማይታየው ለሚታየው መሠረት ነው፡፡ የሚታየውና የማይታየው ዓለምም በእግዚአብሔር ተደራጅቷል፡፡ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፡፡ እግዚአብሔር መንፈስ ነው ስንል የማይታይ፣ የማይወሰን ማለታችን ነው፡፡ መንፈስ የሚለው ቃል ለሰው ለመላእክትና ለእግዚአብሔር ይነገራል፡፡ ለሰው ሲነገር ከሥጋ ቀጥሎ ስላለው አንድ ክፍል እየተናገረ ነው፡፡ ለመላእክት ሲናገር ስለ አንድ ክፍል ሳይሆን ስለ ተፈጥሮአቸው እየተናገረ ነው፡፡ ለእግዚአብሔር ሲናገር ግን ረቂቅና ምሉዕ በኩለሄ /በሁሉ የሞላ/ መሆኑን እየገለጠ ነው፡፡

ነፍስ ረቂቅ ናት፣ ከነፍስ መላእክት ይረቅቃሉ፤ ከመላእክት ረቂቅነት እግዚአብሔር ይረቅቃል፡፡ እግዚአብሔር በእምነት የሚገኘው እምነት የማይታየውን የምናይበት መሣሪያ ስለሆነ ነው /ዕብ. 11፡1/፡፡ እምነት ረቂቁን የምናይበት መነጽር፣ ከእውቀታችን በላይ የሆነውን የምንቀበልበት አስረጂ ነው፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ሩቅ ከዋክብትን የምናይበት፣ ረቂቅ በሽታዎችን የምንመለከትበት የርቀትና የረቂቅነት መሣሪያ አለ፡፡ በዚህም ሁሉ ቅርብ፣ ሁሉ የሚታይ አለመሆኑን እንረዳለን፡፡ እግዚአብሔር ረቂቅ ነው፡፡ ከዓይናችን የዘለቀ ነው፡፡ እግዚአብሔር ከአእምሮአችንም የሰፋ ነው፡፡ እግዚአብሔር መንፈስ ነው ስንል አይታይም፣ አይወሰንም ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር አይታይም፤ ነገር ግን፡-
    የሚታዩትንና የማይታዩትን ፍጥረታት አስገኝቷል፡፡
    የሚታዩትንና የማይታዩትን ጠላቶች ይመልሳል፡፡
    የሚታይና የሚሰማ ፍርድን ይሰጣል፡፡
እግዚአብሔር በባሕርይውና በክብሩ አይታይም፡፡ በፈቀደ ጊዜ በሰው መጠን ራሱን ይገልጻል፡፡ ኃያል ነውና አንዳንዴ እንደ ጎበዝ ተገልጦአል፣ ዘመን ጠገብ ነውና አንዳንዴ በሽማግሌ አምሳል ታይቷል፡፡ እምነት ያስፈለገንም ከዓይናችን የራቀውን እግዚአብሔር ለማየትና ለማድነቅ ነው፡፡ ዓይን የሚያየው በዓለመ ግዘፍ ያለውን ነው፡፡ በዓለመ መንፈስ ያለውን ለማየት መንፈሳዊ ዓይን ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር የማይታየው፡-
ፍጡር አይቶት በሕይወት መኖር ስለማይችል ነው፡፡ በቀትር የፀሐይ ክበብን ማየት እንደማይቻል እንዲሁም ከፀሐይ ይልቅ የሚያበራውን አምላክ ማየት አይቻልም፡፡ በሰማይ የሚያድሩ ቅዱሳን የዝማሬአቸው አዝማች፡- “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ” የሚል ነው፡፡ እግዚአብሔርን በልዩ ባሕርዩ አይተውት “ቅዱስ አንተ ልዩ” ብለው ይሰግዳሉ፡፡ ሲነሡ በሌላ ውበቱ ያዩታል አሁንም “ቅዱስ አንተ ልዩ” እያሉ ይሰግዳሉ፡፡ አሁንም ሲነሡ በሌላ ክብር ያዩታል፡፡ እንዲህ ሳይለምዱት ዘላለም ይጠባል፡፡ እግዚአብሔር አይታይም፡፡ እግዚአብሔር አይጠገብም፡፡ መላእክትም የሚያመልኩት በማየት ሳይሆን በማመን ነው፡፡ ፍጡር አይቶት አይድንም፡፡ መላእክት ሰውን ከሚወዱበት ነገር አንዱ የሚወዱት ጌታቸው ምሳሌ ስለሆነ ነው፡፡ ሰውን እያዩ ሲደነቁ ሰው ወደቀ፡፡ እግዚአብሔር ሰው እንደሚሆን ተስፋ በሰጠ ጊዜ አሁንም ያንን በማየት ሳይሆን በማመን የሚያመልኩትን ጌታ ለማየት ናፈቁ፡፡ ለዚህ ነው ጌታችን ሲወለድ የሰው ልጅ ተኝቶ እነርሱ የዘመሩት፡፡ የጌታችን ሰው መሆን የአበው ተስፋ፣ የነቢያት ትንቢት፣ የመላእክት ናፍቆት፣ በሲኦል ያሉት ነፍሶችም ጩኸት ነበር /1ጴጥ. 1፡12/፡፡ የአንድ ሕጻን መወለድ አንድ ቤተሰብን ያስደስታል፡፡ በቤተ ልሔም እንደ ሕጻን የተወለደው ግን በመለኮቱ የዘላለም አባት ነውና ሰማይና ምድርን አስደስቷል፡፡
 ሙሴ ይህ አምላክ ለማየት ጠይቋል፡፡ የተሰጠው ምላሽ ግን “ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም” የሚል ነው /ዘጸ. 33፡20/፡፡ እግዚአብሔር በመለኮታዊ ክብሩ ቢገለጥ እንደ ሰም እንቀልጣለን፡፡ ፀሐይ ቢቀርቧት እንደምታቀልጥ እግዚአብሔርም በግርማው መደፈር የለበትም፡፡ እግዚአብሔርን በክብሩ በሆነው ልክ ብናይ እንደ ነፋስ እንበናለን፡፡ እንኳን እግዚአብሔር በፊቱ የሚቆሙ መላእክት ሲመጡ እንኳ ቅዱሳን ወድቀው እንደ በድን ሆነዋል /ዳን. 10./፡፡ መልእክቱን የሰሙት ተቀስቅሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር ማለት ያወቅነውና ያላወቅነው ነው፡፡ በመታወቁና ባለመታወቁ የሚያስደስት አምላክ ነው፡፡ በዚህ ዓለም ያወቁት ሲያስደስት ያላወቁት ያበሳጫል፡፡ እግዚአብሔርን ስናውቀውም ሳናውቀውም በደስታ እናመልከዋለን፡፡ አንተ ራስህን ታውቃለህ ብለን እናርፋለን፡፡
ሐዋርያው፡- ብቻውን አምላክ ለሚሆን ለማይጠፋው ለማይታየውም ለዘመናት ንጉሥ ምስጋናና ክብር እስከ ዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን” ይላል /1ጢሞ. 1፡17/፡፡ ብቻነት ወይም አቻ የለሽነት፣ አለመታጣት ወይም ነዋሪነት፣ አለመታየት ወይም ወሰን የለሽነት፣ ዘላለማዊ ንጉሥነት ጠባዩ ነው፡፡ ዳግመኛም ሐዋርያው፡- “እርሱ ብቻ የማይሞት ነው፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤ አንድ ሰው እንኳ አላየውም ሊያይም አይቻለውም፤ ለእርሱ ክብርና የዘላለም ኃይል ይሁን፤ አሜን” ብሏል /1ጢሞ. 6፡16/፡፡ እግዚአብሔር ራሱን ያውቃል እንጂ እኛ በሙሉነት ልናውቀውና ልናሳውቀው አንችልም፡፡ ከኅሊናችን በላይ ነው፡፡ ቅዱስ ጎርጎርዮስ፡- “እርሱን መመርመር ከቻልንና ካወቅንስ ረቂቅ የሚሆን የእርሱን ገናንነት ባጎደልን ነበር፤ ነገር ግን ከቻልን የሥጋዊውን ምሥጢር እናውቅ ዘንድ እንመርምር፤ ይህም ከልብ የኅሊና መገኘት ነው፤ እንደምን ነው? ወይም የፍጡራንን ተፈጥሮ እናውቅ ዘንድ እንመርምር፤ ከአንደበት የቃል መገኘትስ ምን ይመስላል? በእኛ ባሕርይ ያሉ እሊህን ማወቅ ካልተቻለን ኅሊናት የማይመረምሩት ያልተፈጠረ የፈጣሪን ምሥጢር እንደምን እናውቃለን? ኢሳ 45፡15፡፡ ሮሜ. 11፡33-35፡፡ ይህን ምሥጢር ያውቅ ዘንድ ለሰው ቢገባው ኖሮስ አንድነቱን ሦስትነቱን የተናገረ ወንጌላዊው ዮሐንስ እግዚአብሔርንስ ፈጽሞ ያየው የለም ባላለም ነበር፤ ማንም ፈጽሞ የማያየውን በማን እንመስለዋለን? ከአብ ተወለደውን ልደትስ ዛሬ እናውቅ ዘንድ እንደምን እንመረምራለን ? ኢሳ 40፡18-25፡፡ ዮሐ. 1፡18፡፡ ግብረ ሐዋ. 17፡29 ብሏል /ሃይማኖተ አበው ገጽ 41 ምዕ 13፡16-17/፡፡ የቅዱስ ጎርጎርዮስም ገለጻ በጣም ሰፊ ነው፡፡ በአጭሩ፡-
1-  እግዚአብሔርን በሙሉነት ካወቅነው እግዚአብሔር መሆኑ ይቀራል፡፡
2-  እንኳን እግዚአብሔርን ተፈጥሮንም በሙሉነት ማወቅ አይቻለንም፡፡
3-  በግዙፉ ጭንቅላት ረቂቅ አሳብ፣ በግዙፉ ምላስም ረቂቅ ቃል መኖሩ ድንቅ ነው፡፡
4-  ረቂቅ ልደት የተወለደው ወልድ ግዙፍ ልደት ቢወለድ፣ ግዙፍ ልደት ያለን እኛ በእምነት ረቂቅ ልደት ብንወለድ አሜን ብለን በመቀበል እንጂ መዘርዘር በመቻላችን አይደለም፡፡ በግዙፉ ምላስ ያለውን ረቂቅ የቃል ልደት በማሰብ እናርፋለን፡፡
5-  እገሌ ይህን ይመስላል ለማለት ማየት ያስፈልጋል፣ እግዚአብሔርንም አላየነውምና ክብሩን መመሰል አንችልም፡፡
ርቱዐ ሃይማኖትም፡- “ሰው ሆይ፣ ፍጥረታት ለማይመስሉት በምን ታመሳስለዋለህ? የማይታሰበውንስ እንዴት አድርገህ ልታስበው ትቃጣለህ? በፍጡራን ሊያስተካክሉት የሚገባ አይደለም፤ በምንም በማናቸውም ስለ ግርማው በመብረቅ፣ ከፍተኛ ስለሆነው ብርሃኑ በፀሐይ፣ ስለ ልዕልናው በሰማይ፣ ስለ ስፋቱ በምድር፣ ስለ ጥልቀቱ በባሕር፣  ስለማቃጠሉ በእሳት፣ ስለ ርቀቱና ስለፍጥነቱ በነፋስ ወይም በማናቸውም ቢሆን የእውነት አምላክን መለኮትነት ሊያስረዳ ይችላል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ይህ ለፍጥረት ያልተሰጠውና፣ በምንም በማናቸውም ሁኔታውን ለመረዳት አይቻልም፤ ስለዚህም ሁኔታውን ለመመርመር አይቻልም” በማለት ይገልጠዋል፡፡ ለመመሰል ማሰብ ያስፈልጋል። እግዚአብሔር ደግሞ ከአሳብም ይረቃል። ይህን ያህላል ይህን ይመስላል ለማለት እግዚአብሔር ከመለኪያ ውጭ ነው። ከፍታዎችን ይረግጣል፣ ከፍታዎች አይደርሱበትም። የጥልቀቶችን መሠረት በመዳፉ ይዟል፣ እውቀቱም አይመረመርም። አንዳንዴ ምሳሌ የምንመስለው እግዚአብሔርን ስለሚመጥነው ሳይሆን የእኛን ደካማ ተፈጥሮ ስለሚያግዘው ነው።
የክርስቶስን ሰው መሆን ሊቃውንቱ ሲያደንቁ የኖሩት ሥጋዌን ከቤተ ልሔም ተነሥተው ሳይሆን ከአርያም ተነሥተው ስላዩት ነው፡፡ አንዳንድ ወገኖች ሥጋዌን ከቤተ ልሔም ተነሥተው ስለሚያዩት የክርስቶስን አምላካዊ ክብር መረዳት ይቸግራቸዋል፡፡ ቢረዱም ይሳሳባቸዋል፡፡ ሥጋዌ ግን ከአርያም ተነሥተን ስናየው እጅግ ያስደንቀናል፡፡ ሰማይ ምድር የማይችሉት አምላክ በድንግል ማኅጸን መወሰኑ፣ የፍጥረታት መጋቢ ከእናቱ የድንግልናዊ ወተት መለመኑ ይደንቃል።
ወንጌላዊውም፡- “መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው” ይላል /ዮሐ. 1፡18/፡፡ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ ለምን ሰው ሆነ? አብና መንፈስ ቅዱስ ለምን ሰው አልሆኑም? ስንል የስምና የግብር ተፋልሶ እንዳይኖር ነው፡፡ የአብ ስሙ አባት፣ ግብሩም ወላዲ ነው፡፡ የወልድም ስሙ ልጅ ግብሩም ተወላዲ ነው፡፡ አብ ሰው ቢሆን በምድር ወልድ ወይም ልጅ ይሆን ነበር፡፡ ወልድ ወይም ልጁ ግን ሰው በመሆኑ በሥላሴ መንግሥት የስምና የግብር ተፋልሶ አልተገኘም፡፡ በሰማይም ልጅ በምድር ልጅ ይባላል። የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ ሆኗልና። እግዚአብሔር የማይታይ ከሆነ ያላዩት እርሱን በሙሉነት መግለጥ አይችሉም፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ሊገለጥ የሚችለው በራሱ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በሥጋ መገለጥ የመጣው ልጁ የማይታየውን ባሕርይ ገለጠልን፡፡ እርሱ አንድ ልጅ ነው፡፡ እርሱ በአባቱ እቅፍ ያለ ነው፡፡ እርሱ ብቻ አባቱን መግለጥ የሚችል ነው፡፡
አንድ ልጅ፡- “አንድ ልጁ እርሱ ተረከው” ይላል። በመለኮታዊ ልደቱም በሥጋ ልደቱም ቀዳሚና ተከታይ የሌለበት አንድ ልጅ ነው። ለአባቱ አንድ ለእናቱም አንድ ልጅ ነው። ልደቱም እንደምን እንደሆነ መናገር አንችልም። የእርሱ ልጅነት ግን፡-
1-  ከዘላለም ነው /ሚክ. 5፡2/፡- ቀዳማዊ ልደቱ በዚህ ጊዜና ሰዓት ተብሎ አይጠቀስም። ከጊዜ መስፈሪያ ውጭ ነው።
2-  የባሕርይ ነው /ዕብ. 1፡3/፡- አብን በመልክ መስሎ በክብር ተካክሎ የተወለደው ልደት ነው። የእርሱ ልጅነት እኩያነት ነው።
3-  የማይለይ ነው /ዮሐ. 1፡1/፡- ልደቱ ተከፍሎ ያለበት ምድራዊ ልደት ሳይሆን መለየት የሌለበት ልደት ነው። ቃል ከልብ እንደሚወለደው ያለ ልደት ነው። ረቂቅና መለየት የሌለበት ነው።
4-  አንድ ልጅ ነው /ዮሐ. 1፡18/፡- ይህን በመሰለ የክብር መበላለጥ፣ የዘመን መቀዳደም በሌለበት የተወለደ ወልድ ብቻ ነው።
5- ልደቱ በሥላሴ ውሳጣዊ ግብር የተፈጸመ ነው። ሥላሴ ውሳጣዊ ግብራቸው ሦስት ሲሆን አፍአዊ ግብራቸው ግን አንድ ነው። ውሳጣዊ ግብር አብን ወላዲና አሥራጺ፣ ወልድን ተወላዲ መንፈስ ቅዱስን ሠራጺ የሚያሰኝ ነው። አፍአዊ ግብር ግን የእኛ አምላክና አባት የሚሆንበት ነው። ይህ ግብር አንድ ነው። ለዚህ ነው አብን አባ አባት ብለን እንጠራለን /ሮሜ. 8፡15/፣ ወልድንም የዘላለም አባት እንለዋለን /ኢሳ. 9፡6/፣ ሳይወልዱ አባት መሆን የለምና ቢወልደን ከዚያም አልፎ ቢፈጥረን አባት እንለዋለን። ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስም እንደምንወለድ ተነግሯልና መንፈስ ቅዱስም ይወልደናል /ዮሐ. 3፡5/። ይህ ማለት በአፍአዊ ግብር ተወልደናል ማለት ነው። አፍአዊ ግብር አንድ ነውና አንድ ወላጅነት ነው። አፍአዊ ግብር አንድ ነው። ሦስቱ አካላት በአንድነት የሚጋሩት ነው።
6- ልደቱ ስግደት ተቀባይ ነው። የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ብለው ሰግደውለታል። “በታንኳይቱም የነበሩት። በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ብለው ሰገዱለት” /ማቴ. 14፡33/።
የእኛ ልጅነት በክርስቶስ በማመን የምናገኘው ነው። ልጅነታችንም ከልጅነቱ ልዩነት አለው፡-
1-  የእርሱ ልጅነት ከዘላለም ነው፣ የእኛ በጊዜ ውስጥ ነው።
2-  የእርሱ ልደት ባሕርያዊ ነው፣ የእኛ የጸጋ ነው።
3-  እርሱ አንድ ልጅ ነው፣ እኛ ብዙ ልጆች ነን።
4-  እርሱ ከአብ ይወለዳል፣ እኛ ከሥላሴ እንወለዳለን።
5-  የእርሱ ልደት ስግደት ተቀባይ ነው፣ የእኛ ልጅነት ስግደት አቅራቢ ነው።
ይህን አስረግጠን ማወቅ ያስፈልጋል። ዛሬ በአገራችን፡- “ክርስቶስም እኛም እኩል ልጆች ነን፣ ስለዚህ ይህን አምጣ ብለን እርሱን መለመን አይገባንም ማዘዝ እንችላለን” የሚል ትምህርት በጣም እየተስፋፋ በመሆኑ ማስተዋል ያስፈልገናል። ይህ ትምህርት ሲገፋም “ትንንሽ አምላኮች ነን” የሚልም እሳቤ ይይዛል።
በአባቱ እቅፍ፡- “በአባቱ እቅፍ ያለ” ይለዋል። ሁለት ነገሮችን ያመለክታል። ፍቅርንና አለመለየትን። አብ ልጁን ይወዳል። ልጁም ከአባቱ ሳይለይ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይኖራል። አንድ ልጅ ከእናቱ ሲወለድ ያለ እናቱ መኖር ይችላል። የሚወለደውም እትብት ተቆርጦ ነው። እንደውም ለመኖር መለየት ያስፈልገዋል። የአብና የወልድ ግንኙነት ግን እንደ ልብና እንደ ቃል ነው። ቃል ከልብ ሳይለይ ከልብ እንደሚወጣ እንዲሁም ወልድ ከአባቱ ሳይለይ ተወልዷል። ቃል ከልብ ሳይለይ በብራና ላይ እንደሚጻፍ ገዝፎም እንደሚዳሰስ እንዲሁም ቃል የተባለው ወልድ ከአባቱ ሳይለይ በሥጋ ገዝፎ መጥቷል።
ተረከው፡- አብን ለመተረክ በአብ ክብር ያለ መሆን አለበት። እግዚአብሔር ራሱን ያውቃል። እግዚአብሔር በልዕልናው ርቆ፣ በሀብቱ መጥቆ የሚኖር ሳይሆን እንዲህ የሚወደን የእኛ ነገር የሚሰማው መሆኑን ክርስቶስ ሰው ሆኖ ገልጧል። ተረከው ይላል። ትረካ ቀስታና የፍቅር ቅላጼ ያለው ነው። ክርስቶስ እንዲህ ነው የተረከው። ለዚህ ነው በነቢዩ፡- “አይከራከርም አይጮህምም፥ ድምፁንም በአደባባይ የሚሰማ የለም” የተባለለት /ማቴ. 12፡19/።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ