የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ክርስቶስ አይደለሁም

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ረቡዕ ሚያዝያ 12/2008 ዓ.ም.
                                          
 
“አይሁድም። አንተ ማን ነህ? ብለው ይጠይቁት ዘንድ ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን በላኩበት ጊዜ፥ የዮሐንስ ምስክርነት ይህ ነው” /ዮሐ. 1፡19/፡፡
ወንጌላዊው ዮሐንስ መጥምቅን ለሦስተኛ ጊዜ ያነሣዋል፡፡ የከበረው ዮሐንስ ስለ ክርስቶስ ታላቅነት መስክሯል፡፡ ዮሐንስን የምታከብሩት ከሆነ ዮሐንስ ያከበረውን አክብሩ ለማለት ያነሣዋል፡፡ የወንጌላዊው አሳብ የክርስቶስን አምላካዊ ክብር፣ ሰማያዊ ፍቅር መግለጥ ነው፡፡ ዮሐንስ የሊቀ ካህናቱና የጻድቁ ዘካርያስ ልጅ ነው፡፡ በስተርጅና የተወለደ የተአምራት ልጅ ነው፡፡ ስለዚህ የቤተ መቅደሱ ተከታይ ሊቀ ካህን ነው፡፡ ዮሐንስ ይህን ክብር ለቅቆ በረሃ መግባቱ የአይሁድ መሪዎችን አስጨንቋል፡፡ ሊቀ ካህናት ማለት አንድ ፓትርያርክ ማለት ነው፡፡ ዛሬ አንድ ፓትርያርክ በበረሃ ገብተው አገልግሎት ቢጀምሩ ሁሉን ያስጨንቃሉ፡፡ ስለዚህ በኢየሩሳሌም የሚገኘው የሃይማኖት ሸንጎ ተወያይቶ ወኪሎችን ወደ ዮሐንስ ላከ፡፡ ዮሐንስ በምድር ላይ የነበረውን ትልቁን ሹመት፣ ሊቀ ካህንነትን እንቢ ስላለ ምናልባት ክርስቶስ ይሆንን? የሚል ስሜት አሳድሮባቸዋል፡፡ ዓለም ሥልጣንና ገንዘብን እንቢ ያለ ሰውን ትፈራለች፡፡ ሰው ሁሉ የሚጠመደው በዚህ ነውና ከወጥመዱ ሲያመልጣት ምን ቢኖረው ነው? በማለት ትሸበራለች፡፡ ዓለምን የሚመስሉ የዓለም ስጋት አይደሉም፡፡ ዓለም በምድራዊ ክብር ከሚራኮቱት አገልጋዮች ይልቅ ምድራዊውን ክብር የናቁትን ትሰጋለች፡፡ የቀደሙት አባቶች ሁሉ ከዚህ ዓለም ምንም ጉዳይ የለኝም እያሉ በድህነታቸው ይመኩ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ አገልጋይ በሀብቱ ይመካል፡፡ በቂ ንብረት አለኝ ካስፈለገ አገልግሎቱን ለቅቄላቸው እሄዳለሁ ይባላል፡፡ መንግሥትም የቆረጠ፣ ጫካ የገባውን እንጂ በከተማ ያለውን አይሰጋም፡፡

ይህች ዓለም አሸባሪዎችን የፈራችው ለምንድነው? ስለሚገድሉ ብቻ ነውን? አይደለም፡፡ ሞትንም ስለማይፈሩ ነው፡፡ የዚህ ዓለም የመጨረሻው ማስፈራሪያ ሞት ነው፡፡ እነዚህ ክፉ ስብከት የሰሙ አሸባሪዎች ግን ሞትን ሲሻሙ በጣም ያስፈራሉ፡፡ ከአንበሳ ሥጋ እየነጠቁ የሚኖሩ የኬንያ ዘላኖች የሚያደርጉት አንበሳውን ዓይናቸውን ሳይነቅሉ ትኩር ብለው ያዩታል፡፡ ዓይናቸውን ሳይነቅሉ ወደ እርሱ ሲሄዱ ፈርቶ የሚበላውን ሥጋ ጥሎ ይሸሻል፡፡ የሚያስፈራው አንበሳ በማይፈሩ ይፈራል፡፡ ዮሐንስም የመነጋገሪያ ርእስ ነበረ፡፡ ከደማቋ ኢየሩሳሌም እንዴት በረሃን መረጠ? ከክብር ወንበር እንዴት ዋሻን ማደሪያው አደረገ? በማለት ኢየሩሳሌም ታወከች፡፡ ዛሬ ዓለምን ስለመናቁ የሚያስጨንቅ ይኖር ይሆን? እንደውም እየተጋፋ የዓለምን መስመር ያጨናነቀ የበዛ ይመስላል፡፡ እግዚአብሔር ሁላችንንም ይቅር ይበለን፡፡
ዮሐንስ ይህን ክብር በመናቁ፣ ከብሉይ ትልቅነት የሐዲስን ሎሌነት በመምረጡ ይህን ውሳኔ የሚያስወስን መሢህነት ነው ብለው አሰቡ፡፡ በርግጥ መሢህን ማግኘት ብቻ ይህን ውሳኔ ያስወስናል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በበረሃ፣ ዮሐንስ በከተማ ለምን አላገለገሉም?  ቢባል ጌታችን ከሰማይ ወርዶ በረሃ ቢገባ ሰዎች ኑሮአችንን ተካፈለ አይሉትም ነበር፡፡ ሰማይ ሩቅ በረሃም ያው ሩቅ ነው ይሉ ነበር፡፡ ዮሐንስ በተወለደበት አገር ቢከብር ሥልጣን ፈላጊ ይባል ነበር፡፡ የሚያምረው ዮሐንስ በበረሃ፣ ጌታችን በከተማ ሲሰብኩ ነው፡፡ ጌታችን ወደ ሰዎች ድረስ መጣ፣ ሰዎች ደግሞ ዮሐንስ ያለበት ድረስ መጡ፡፡ ዮሐንስ የመዘጋጃውን አገልግሎት ሰጠ፣ ክርስቶስ ግን የፍጻሜውን ሕይወት አበሰረ፡፡ ዮሐንስ መቅረዝ ነበርና ዘይት ዕድሜው አለቀ፣ ጌታችን ግን ፀሐይ ነውና ከሞት ተነሥቶ ያበራል፡፡
“አይሁድም። አንተ ማን ነህ? ብለው ይጠይቁት ዘንድ ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን በላኩበት ጊዜ፥ የዮሐንስ ምስክርነት ይህ ነው” /ዮሐ. 1፡19/፡፡ አይሁድ የሚለው የማኅበረሰቡ መጠሪያ ነው፡፡ የይሁዳ ነገድ ትልቅ ነገድ፣ የነገሥታት ዘር በመሆኑ በይሁዳ አይሁድ ይባላሉ፡፡ አይሁድ ምሥጢራዊ ትርጉሙ የእግዚአብሔር ሕዝብ ማለት ነው፡፡ ዛሬ አይሁድ በማለት ሰዎች ለመሳደብ ይሞክራሉ፡፡ ትክክል አይደለም፡፡ ይልቁንም የእስራኤል መንግሥት በሮብዓም ዘመን ለሁለት ሲከፈል ደቡቡ የይሁዳና የብንያን ነገድ ነበር፡፡ ስለዚህ መንግሥቱም የይሁዳ መንግሥት ተባለ፡፡ ወደ ዮሐንስ የተላኩት የማኅበረሰቡንም አሳብ ይዘው ነው፡፡ ኢየሩሳሌም ትልቅ የሃይማኖት መዲና ናት፡፡ ዛሬ አይሁዳውያን፣ ክርስቲያኖችና እስላሞች የሃይማኖት መዲና ብለው ይሻሙባታል፡፡ የብሉይ ኪዳንም የአምልኮ ማዕከል ናት፡፡ መሥዋዕት ያሳርጉ የነበረው በኢየሩሳሌም ባለው መቅደስ ነው፡፡ ዛሬም ክብሯ አልቀነሰም፡፡ ከዚህች ከኢየሩሳሌም የሃይማኖትና የፖለቲካ መዲና ወደ ዮሐንስ መልእክተኛ ላኩ፡፡ የተላከው መልእክት አንተ ማን ነህ የሚል ነው፡፡ ማንነቱ ረብሾአቸው ነበር፡፡ ጌታችን በከተማ ሰዎችን ቀርቦ፣ ዮሐንስ በበረሃ ከሰዎች ርቆ አገለገሉ፡፡ ሰዎችን ምክንያት በማሳጣት ወደ እውነት ለማምጣት ነው፡፡ ከእኛ ጋር እየኖረ እንዳይሉ ዮሐንስ በበረሃ አለ፣ ከእኛ ርቆ የከተማውን ኑሮ መች ያውቀውና እንዳይሉ ጌታችን በከተማ አገለገለ፡፡ በገዳም በጽሞና በከተማ በቀና የሚያገለግሉ ያስፈልጋሉ፡፡
ወደ ዮሐንስ የተላኩት ካህናትና ሌዋውያን ናቸው፡፡ ካህናትም ሌዋውያንም ሁለቱም የሌዊ ዘር ናቸው፡፡ የካህናት ሥራ በቤተ መቅደስ ውስጥ ሲሆን የሌዋውያን ሥራ ደግሞ በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ነው፡፡ ከሌዊ ነገድ የአሮን ቤት ብቻ ለካህንነትና ለሊቀ ካህንነት ይመረጣል፡፡ ሌሎች ሌዋውያን ግን የጽዳቱን ሥራ፣ የቤተ መቅደሱን ንዋያተ ቅድሳት በመሸከም ያገለግላሉ፡፡ እነዚህ ካህናትና ሌዋውያን ወደ ዮሐንስ ተላኩ፡፡
 ይህ ዮሐንስ መኖሪያ የሌለው በበረሃ የተጣለ፣ የሚበላና የሚጠጣ የሌለው የበረሃ ማርና አንበጣ ተመጋቢ የሆነ፣ ልብስ የሌለው የግመል ፀጉር የሚለብስ ነው፡፡ በንግግሩ እንኳን ብዙዎቹን ያሳምናል እንዳይባል ንግግሩ ሰይፍ ነበረ፡፡  ካህናትና ሌዋውያን ግን ዮሐንስን አልናቁትም፡፡ መሰላል የሚለቅ ሠገነቱን ያገኘ ብቻ ነው፡፡ የሚበልጠውን ያልያዘም ዓለምን መናቅ አይችልም፡፡ ዮሐንስ ምን እንዳገኘ አላወቁም እንጂ እንዳገኘ እርግጠኛ ናቸው፡፡ ክርስቶስ ዓለምን ያስንቃል፡፡
“መሰከረም አልካደምም፤ እኔ ክርስቶስ አይደለሁም ብሎ መሰከረ” /ዮሐ. 1፡20/፡፡ ምስክነት እንዲህ ነው የሚል ነው፡፡ ይህ ምስክርት ግን እኔ ክርስቶስ አይደለሁም የሚል ነው፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን እንደ አምላክ ያዩአቸው ራስ ተፈሪያን የሚባሉ ነበሩ፡፡ የዓለም የክርስቲያን ማኅበረሰብ እርስዎ አምላክ አለመሆንዎን ይመስክሩ እያሉ ለመጠየቅ ሞክሯል፡፡ እነዚህን ወገኖች በጊዜው ማስተማር ቢቻል ኖሮ ዛሬ ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አያጥኑም ነበር፡፡ እንደውም ርስት ተሰጣቸው፡፡ አምልኮታቸውን የሚያሳርጉት በአደንዛዥ ዕፅ በመታጀብ በመሆኑ ለብዙ ወጣቶች እንቅፋት ሆነዋል፡፡ አይደለሁም ማለት ትልቅ እንቅፋትን ያነሣል፡፡ ዮሐንስ ክርስቶስ ነኝ ቢል ይሰግዱለታል፡፡ ነገር ግን አያድናቸውም፡፡ ሰዎች ለእግዚአብሔር የሚገባውን አምልኮ ሊሰጡን ቢችሉ እንኳ እግዚአብሔር የሚሰጠውን ዕረፍትና መዳን ግን ልንሰጣቸው አንችልም፡፡ ዮሐንስ ስለ መሢህ የሚያውቅ የመሢህ ምስክር መሆኑን በግልጥ ተናገረ፡፡ መሢህነትን ቢወስድ ኖሮ ነቢይነትን ያጣ ነበር፡፡ የማይገባ ክብር እንዳከሰረ ይኖራል፡፡ የሌለንን ቦታ ስንይዝ የተሰጠንን ቦታ እንለቃለን፡፡ የመላእክት ዓለም የተፈታው፣ አዳም ከገነት የወጣው የአምላክን ቦታ በመፈለግ ነው፡፡ ሄሮድስ በትል ተበልቶ እንዲሞት የተቀጣው ሕዝቡ “የእግዚአብሔር ድምፅ ነው የሰውም አይደለም” ሲሉ ዝም ብሎ በመስማቱ ነው /የሐዋ. 12፡23/፡፡ ያለ አድራሻው የመጣውን ክብር በአድራሻው አለመመለስ ያስቀጣል፡፡ በምድራዊም ሕግ የእኛ ያልሆነውን ተቀብሎ ዝም ማለት ያስጠይቃል፡፡ መስረቅ ብቻ ሳይሆን የተሰረቀንም መቀበል ያስቀጣል፡፡ ከሁሉ በላይ የአምልኮ ሌባ ይጠየቃል፡፡ ሌሎች ኃጢአቶች ድካም ናቸው፡፡ አምልኮን መስረቅ ግን ዓመፅ ነው፡፡ ዮሐንስ እኔ አይደለሁም አለ፡፡ በአንድ ወቅትም በጳውሎስና በበርናባስ እጅ የተደረገውን ተአምራት አይተው ሊሠውላቸው ሲሉ ልብሳቸውን ቀደው ሮጠዋል /የሐዋ. 14፡11-18/፡፡ ሰዎች ሲያከብሩ አምላክ፣ ሲጠሉ ሰይጣን ማለታቸው የተለመደ ነው፡፡ ሁለቱም ተገቢ አይደለም፡፡ ሰውን ሰው ማለት ብቻ ከመሳትና ከመሳሳት ይጠብቃል፡፡ ዛሬ ፍቅራችን ወደ አምልኮ የተለወጠባቸው ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ብዙ መከዳዳቶች ብዙ አምልኮ የነበራቸው ግንኙነቶች ናቸው፡፡ ዮሐንስ ግን እኔ ክርስቶስ አይደለሁም ብሎ መሰከረ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ