የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ዮሐንስ፣ ዮሐንስ ነው

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ዓርብ ሚያዝያ 14/2008 ዓ.ም.
 
“እንኪያስ ማን ነህ? ኤልያስ ነህን? ብለው ጠየቁት። አይደለሁም አለ። ነቢዩ ነህን? አይደለሁም ብሎ መለሰ” /ዮሐ. 1፡21/።
ከኢየሩሳሌም የአይሁድ ማኅበረሰብና የካህናት ጉባዔ የተወከሉት ሰዎች ዮሐንስን እየወተወቱት ነው። ዓለምን ርቆ ቢሄድም ዓለም ግን እየተከተለች ትወተውተው ነበር። ዓለም ሲሮጡ ትሮጣለች፣ ሲቆሙ ትቆማለች። የእንደገና ዕድል የላትም። ዓለም ጥላ ናት፣ ሲሸሿት ትከተላለች፣ ሲከተሏት ትሸሻለች። የዮሐንስ ሕይወቱ ይወቅሳቸው ነበር። እነርሱ በካህንነት ሥልጣን ሲሻሙ እርሱ ግን ሊቀ ካህንነትን ንቆ ገዳም/በረሃ/ በመግባቱ ይህማ መሢህ እንጂ ተራ ሰው አይደለም ብለው እንዲዛቡ አደረጋቸው። የተጨነቁት መሢሁን ለማግኘት ሳይሆን እነርሱ የሚጋደሉለትን ሥልጣን ዮሐንስ እንዴት ሊንቅ ቻለ? ለሚለው ጥያቄአቸው መልስ ለማግኘት ነው። መሢህ ነህን? ሲሉት አይደለሁም ሲላቸው መቀበል አይፈልጉም፣ መሢህ እንዲሆንላቸው ይፈልጋሉ። እኔ መሢህ ነኝ ብሎ ክርስቶስ ሲመጣ ግን ሊቀበሉት አይፈልጉም። ሊያምኑ የሚፈልጉት ስሜታቸውን እንጂ እውነትን አልነበረም። መስማት የሚፈልጉት የሚያስቡትን ነው።

የዮሐንስ የሕይወት ምርጫ አስጨንቋቸዋል። ለላኩአቸው አንድ መልስ ይዞ ለመመለስ ፈልገዋል። የሊቀ ካህንነትን ሥልጣን የናቀው ከፍ ያለ መሢህ ቢሆን ነው በሚል አሳብ መሢህ ነህ ወይ? በማለት ጠየቁት አይደለሁም አለ። ምናልባት ኤልያስ ሊሆን ይችላል በማለት ኤልያስ ነህን? አሉት። እርሱም አይደለሁም አለ። ምክንያቱም ዮሐንስ፣ ዮሐንስ ነበረ። ሰዎች የራሳቸውን ስያሜ በመስጠት በራሳቸው ግምት ይጨነቃሉ፣ ያስጨንቃሉ። እገሌ እንዲህ ነው በማለት ይፈርጃሉ። ስለ ሰዎች ያላቸውን እውቀት ያህል ግን ስለራሳቸው የላቸውም። ስለራሳቸው ያላቸውን እውነተኛ እውቀት ሐሰተኛ መጽናናት ያስገቡበታል፣ ስለ ሰዎች ባላቸው የተሳሳተ እውቀት ቀጥተኛ ፍትሕ ይጨምሩበታል። በቂ እውቀት በሌለበት በቂ ፍርድ ሊኖር አይችልም። ሰውን ከራሱ በቀር ሊያውቀው የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው። ስለዚህ በትልቅ ፍርዳችን ብቻ ሳይሆን በትልቅ ክብራችንም ውስጥ ኃጢአት አለበት። ሰዎች ከፍ ሲያደርጉም ሲያዋርዱም ከራሳቸው ግምትና ስሜታቸውን ከማመን ነው። ስሜት ነገሮችን በልካቸው እንዳናይ የምታደርገን ሚዛን ማፍረሻ ናት።

ሰው እኔ እንዲህ ነኝ ሳይል እንዲህ ነህ ማለት ትልቅ ድፍረት ነው። እኛ ልናምን ልናሳምን እንጂ ልናልቅ ልናኮስስ ሥልጣን የለንም። እስከምንችለው ከሰዎች ጋር እንጓዛለን፣ ካልቻልን ለሚችለው ጌታ ሰጥተን እናርፋለን እንጂ ጠልቻለሁ ጥሉልኝ፣ ወድጃለሁ ውደዱልኝ ልንል አይገባም። ፍቅርም ሆነ ጠብ ሁለቱም ከደቦ/ከቡድን/ ውጭ ናቸው። ስንወዳቸው መልአክ እንላቸዋለን። እኔ ሰው ነኝ ቢሉን እንኳ ለትሕትና እንጂ በርግጥ መልአክ ናችሁ እንላለን። እግዚአብሔርንም ሰዎችንም ሳናዳምጥ የራሳችንን የስሜት ብይን እናሳልፋለን። ታዲያ ራሳችንንም እግዚአብሔርንም ሳናዳምጥ መልሰን እናኮስሳቸዋለን። ይብላኝለት በሰው ምስጋና ልቡ ለነሆለለ። ሲረግሙት መሸከም ያቅተዋልና። አንዳንዴ በቅጡ የሚያመሰግን አይደለም፣ በቅጡ የሚሰድብ ከተገኘም መልካም ነው። በራሱ የማይመራ ማኅበረሰብ ሲፈጠር የሚያቆመው ሕግ አይኖርም።
መፈራረድ የመጨረሻው ዘመን መገለጫ ነው /ማቴ. 24፡10/። እገሌ እንጂ እኔ የማይል፣ ንስሐን ጥሎ ሐሜትን ገንዘብ ያደረገ ዘመን ነው። ንስሐና ሐሜት ሁለቱም ኃጢአትን ማውራት ናቸው። ንስሐ የራስን፣ ሐሜት ግን የሰውን በደል ያወራል። ንስሐ ለእግዚአብሔር፣ ሐሜት ለሌሎች ያወራል። ንስሐ መንጻትን ይሻል፣ ሐሜት ማቆሸሽን ይፈልጋል። ይልቁንም ዘሎ ሰው ላይ ቁብ ማለት፣ በቡድንነተኝነት ስሜት አንዱን ማንሣት ሌላውን መጣል በሽታችን ሆኗል። ልክ እንደ አራዊት ያገኙትን መስበር ልምድና ጀግና የሚያሰኝ እየሆነ መጥቷል። በዓለም ላይ ብዙ ሕግጋት ተፈራርቀዋል። ሕገ ኦሪት እስኪመጣ ሕገ ልቡና ነበረ። ሕገ ልቡና ከውስጥ የሚሰማ ድምፅ ነውና ብዙ ወገን ሊያስተውለው ስላልቻለ ከኃጢአት ብዛትም የተነሣ ሕገ አራዊት እየጸና መጣ። በሕገ አራዊት ለተበላላው ዓለም ሕገ ኦሪት መጣ። የሌላውን መብት አትንካ የሚል የዛሬን ስልጡን አገር መገለጫ የምትመስል ሕግ ጸናች። ሕገ ኦሪት ገደብን እንጂ ፍቅርን ልታመጣ አልቻለችም። ባለመነካካት ብቻ የዓለም ቁስል አይፈወስም። ለሌላው መቆረስ ያስፈልጋል። ስለዚህ ራሱን መስቀል ላይ በሰጠው መሪያችን በክርስቶስ ሕገ ሐዲስ ጸናች። ዛሬ ያለንበት ዘመን ስለ መብት የሚነገርበት የእኩያነት ዘመን ሳይሆን ለራሳችን የምንፈልገውን መልካም ለሌላው የምናደርግበት የፍቅር ዘመን ነው። ሕገ ሐዲስ እንዲህ ነዋ! በሰው ሰቃይነትና አውራጅነት የተሰቀቀው የአገራችን ሰው፡- “ጽድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኰነነኝ” ይላል። ሰው የወደደውን ያጸድቃል። የአገሬ ሰው ግን ጽድቁን ሳይሆን በቅጡ ጥፋቴ በተነገረኝ እያለ ይለምናል። ሕገ ሐዲስ በጣም ርቃናለች። ተራርቀን ነው የምንኖረው። እንኳን ጠላትን መውደድ ወዳጅንም መውደድ እየከበደን ይመስላል። የሚሰድቡንን መመረቅ አስበን እንኳ አናውቅም። እንደ ሰለጠኑት ሕዝቦች እንኳ የሌላውን መብት በማክበርም ኦሪታውያን ለመሆን አልዳዳንም። ያልበደሉንን የምንበላ ከሆነ፣ ያልነኩንን የምንነካ ከሆነ፣ በራቸውን ዘግተው የተቀመጡትን እያንኳኳን የምንሰድብ ከሆነ ያለነው በሕገ አራዊት ውስጥ ነው። በቅጡ ኦሪት ጋ ብንደርስ ሐዲስ ላይ መድረሳችን አይቀርም ነበር። ዛሬ ነኝ ሳይሉ ናችሁ የሚባሉ ብዙዎች ናቸው። ሰቃይና አውራጅ የሰው ልጆች ሥራ ሆኗል። ጭንቀት እየበዛ ሲመጣ ሰዎች በሰዎች ማንነት ውስጥ መደበቅ ይፈልጋሉ። ዮሐንስን መሢህ ነህን? ያለች ዓለም ኋላ ላይ አንገቱን ቆረጠችው። ንግግሩ ቢያውካት ምላሱን መቊረጥ ፈራች። በምልክትስ ቢናገር ብላ ደነበረች። አንገቱን በመቁረጥ ማረፍ ፈለገች። የመቅረዙ ብርሃን ሲጨርስ ግን ፀሐዩ ክርስቶስ እንደሚጀምር አልገመተችም።
ኤልያስ ከጥንት ጀምሮ ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል። በቅርብ ዓመታት እንኳ አዲስ አበባ መጥቷል የሚል ወሬ ጠግበን ነበር። አልሞተምና ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል። አለመሞት አያሳርፍም። እኛም ለዓለም ካልሞትን ይመጣል ብላ ትጠብቀናለች። ዓለም በእኛ፣ እኛም በዓለም ተስፋ እስክንቆርጥ በሞት ሕግ መለያየት አለብን። ጌታችንንም ኤልያስ ነው ብለው ያስቡት ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ግን ማንነቱን እንዲያውቁት ስለፈለገ በደብረ ታቦር ኤልያስን አምጥቶ አሳያቸው /ማቴ. 17፡3/። ጌታ ዓለሙ ለሚለየው አይጨነቅም፣ የሚያምኑት ግን በትክክል እንዲያውቁት ይፈልጋል።
ዮሐንስን ኤልያስ ነህን? አሉት። እርሱ ግን አይደለሁም አለ። ዮሐንስ፣ ዮሐንስ ነበረ። ኤልያስና ዮሐንስ ተመሳሳይ የሕይወት ዘይቤ ነበራቸው። ሁለቱም መናንያን ነበሩ። ሁለቱም የተግሣጽ አገልጋዮች ነበሩ። ሁለቱም ነገሥታትን ይቆጡ ነበር። በዚህ ምክንያት ኤልያስ ነህን? አሉት። ሰዎች ለሚሰጡን ሥዕል ሳይሆን ለሆንነው ማንነት ዋጋ መስጠት ይገባናል። ዓላማችን ዛሬ ባይገባን እንኳ የተፈጠርነው በዓላማ መሆኑን እያሰብን መጽናናት ይገባናል። እኛ አንሠራም፣ ጌታችን ግን በእኛ ይሠራብናልና ደስ ይበለን። የሌሎች የክብር ስም ለእኛ አይሆንም። የሌሎች ሙገሳም አያጸድቀንም። ምስጋናቸው ካላስታበየን ስድባቸው አይደንቀንም። እኛ፣ እኛ እንሁን። እየተነዳን አንኑር። እየተመራን ጌታችንን እንከተል። በሌሎች የሚነዳ ይጋጫል፣ መሪና ምሪት ያገኘ ይደርሳል።

ያጋሩ

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።