የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ እሑድ ሚያዝያ 16/2008 ዓ.ም.
“እንኪያስ። ማን ነህ? ለላኩን መልስ እንድንሰጥ፤ ስለራስህ ምን ትላለህ? አሉት” /ዮሐ. 1፡22/፡፡
ከአይሁድ ማኅበረሰብ፣ ከካህናት ሸንጎ የተወከሉት ቡድኖች ዮሐንስን ሊያሳርፉት አልቻሉም፡፡ ልባቸው ታውኳል፡፡ ዙፋን መርጦ ሳይሆን መሬት መርጦ፤ ከተማን ወዶ ሳይሆን በረሃን ተጠግቶ ያስጨንቃል፡፡ ለዓለም ከከፍታችን ይልቅ ዝቅታችን ጭንቅ ነው፡፡ ጌታችን ወደዚህ ዓለም የመጣውና በመስቀል ላይ የሞተው ጠላትን በሞቴም እረታዋለሁ ብሎ ነው፡፡ በመለኮቱ ከፍታ ቢረታው አይደንቅም፤ በክብሩ አሸናፊ ነውና፡፡ በውርደቱ ግን ድል ነሣው፡፡ ልክ እንደ ጌታችን ዓለምን ስንንቅ ለዓለም ጭንቅ እንሆናለን፡፡ ይህን ዓለም በከፍታ ሳይሆን በዝቅታም እናሸንፈዋለን፡፡ ክርስቲያን ባለሥልጣን፣ ባለጠጋ ቢሆን መልካም ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ግን ባለጠጋምና ባለሥልጣን የሆኑ ክርስቲያኖች ለእምነታቸው ያላቸው ድጋፍ ዝቅተኛ ነው፡፡ ዮሴፍ ዘበኛ ሆኖ የጲጥፋራን ቤት አስባርኳል /ዘፍ. 39፡5/፡፡ ያች ትንሽ ምስክር የሆነችው የእስራኤል ብላቴና በቤት ሠራተኛነት የንዕማን ለምፅ በምን እንደሚነጻ መንገድ መርታለች /2ነገሥ. 5፡3/፡፡ ዳዊት ከእረኝነት ስፍራ ተጠርቶ በገና እየደረደረ ንጉሥን አጽናንቷል /1ሳሙ. 16፡23/፡፡ መርዶክዮስ ድንጋይ ላይ ተቀምጦ የአርጤክስስን ሕይወት ከሞት፣ የእስራኤልን ሕዝብ ከመደምሰስ ታድጓል /አስ. 6፡1-9፤4፡1-17/፡፡
እግዚአብሔር በትንሹ ትልቅ፣ በደካማው የብርታቱን ሥራ ይሠራል፡፡ እንደውም ለእግዚአብሔር የሚመቸው ዝቅታችን ነው /2ቆሮ. 12፡7-10/፡፡ ጋኖቹ ባዶ ካልሆኑ አዲሱ ወይን አይገኝም /ዮሐ. 2፡7/፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር በሰው ጥንስስ አይቀጥልምና፡፡ ውጭ አገር ብሄድ፣ ገንዘብ ባገኝ፣ ሥልጣን ብጨብጥ ብላችሁ የተሳላችሁ የለመናችሁት ሆነ፤ የእግዚአብሔርን ሥራ ግን እንደዚያ እንደ ደካማነት ዘመናችሁ አልሠራችሁትም፡፡ እግዚአብሔር የሚላችሁ ማንነታችሁን ስጡኝ፣ መንፈሴን ልስጣችሁና ልሥራባችሁ ነው፡፡ ዛሬ የእስላም ባለሥልጣናት ሲሰግዱ ይታያሉ፤ የክርስቲያን ባለሥልጣናት ግን ቤተ ክርስቲያን ለመሄድ ይሸማቀቃሉ፡፡ ከፍታ ወጥመድ እንዳይሆንብን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ክርስቲያን ካልተወጋ አያመልክም፡፡ የሚወጉ ችግሮች ባይኖሩብን ይህን ቃል እንኳ ለመስማት እንፈተን ነበር፡፡
ዮሐንስ በምድረ በዳ ተቀምጦ ለአገሩ ስጋት ነበረ፡፡ ሠራዊት አላደራጀም፡፡ ነገር ግን ከሠራዊት በላይ ይፈራ ነበር፡፡ በምድረ በዳ አንድ የእግዚአብሔር ሰው አለ እያለ ያ ሕዝብ ማሰቡ በራሱ ደስ ይላል፡፡ ግራ ሲገባው እርሱ ጋ እየሄደ ይናዘዛል፡፡ ይጠመቃል፡፡ ዛሬ ግራ በገባን ሰዓት አማራጭ የሚሆነን የእግዚአብሔር ሰው ላይኖር ይችላል፡፡ የሰማውን የማያሰማብን፣ ያየውን የማያሳይብን የእግዚአብሔር ሰው ማጣት ከባድ ነው፡፡ ቢሆንም እግዚአብሔር አለልን፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለም ወይ ታላቅ መልስ ወይም ታላቅ ጥያቄ ነው፡፡ መልሳችን ካልሆነ ጥያቄአችን ነውና ዕረፍት የለንም፡፡ ሲቃወሙት የሚውሉት ስሙ ሲጠራ ከሰይጣን እኩል የሚደነግጡት ጥያቄአቸው ስለሆነ ነው፡፡ መልሳችን ከሆነ ግን ጥያቄአችን አይደለም፡፡ እርሱ ለእያንዳንዱ ሰው ወይ መልስ ወይም ጥያቄ ነው፡፡ ልክ እንደ ጌታችን እኛም በስሙ ስናምን ወይ ጥያቄ ነን፣ ወይም መልስ ነን፡፡ እርሱን የሚያውቁ ያርፉብናል፡፡ እርሱን የማያውቁ ግን ይረበሹብናል፡፡ ስንወዳቸው ለማታለል ነው፣ ስንረዳቸው ለመደለል ነው እያሉ ግራ ይጋቡብናል፡፡ ዮሐንስም እንዲህ የማይፈታ ቅኔ ሆኖባቸው ነበር፡፡ መልሱን ቢነግራቸውም ማረፍ አልቻሉም፡፡ ምክንያም መስማት የሚፈልጉት የሚያስቡት ነውና፡፡ ከሚያስቡት ውጭ መስማት አይፈልጉም፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “በሚድኑቱና በሚጠፉቱ ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ ነንና፤ ለእነዚህ ለሞት የሚሆን የሞት ሽታ ለእነዚያም ለሕይወት የሚሆን የሕይወት ሽታ ነን። ለዚህም ነገር የሚበቃ ማን ነው?” ይላል /2ቆሮ. 2፡15-16/፡፡ ሮማውያን በጦርነት ሲያሸንፉ የሚያጤሱት አንድ ሽታ ነበር፡፡ ያ ሽታ ሲሸት ወዳጆቻቸው በደስታ ይሞላሉ፤ ጠላቶቻቸው ግን ሞት ይሸታቸዋል፡፡ በዚያ ምሳሌ ሐዋርያው ለሚድኑቱ የሕይወት ሽታ፣ ለሚጠፉት የሞት ሽታ ነን ብሏል፡፡ አንዱ ሽታ በወዳጅና በጠላት ሰፈር ሁለት ትርጉም አለው፡፡ አንድ ትርጉም ብቻ ካለን ራሳችንን እንመርምር፡፡ እየተወደድን እየተሞገስን ከሆነ እንፍራ፡፡ ስንነቀፍ ስንሰደብ ግን የክርስትናውን ጠባይ እናሟላለን፡፡
ስለ አንተ መነቀፍን እንደ ሙገሳ እንድናየው፣ ስለ አንተ መገረፍን ካባ እንደ ተሸለመ ሰው እንድንኮራበት እርዳን፡፡