የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ዓርብ ጥር 27/2008 ዓ.ም
የወንጌሉ ዓላማ
የዮሐንስ አምስት መጻሕፍት ተመሳሳይና ተከታታይ አሳብ አላቸው። ተመሳሳይነታቸው ሁሉም ስለ መጀመሪያ ይናገራሉ። ወንጌሉ ስለ ቀዳማዊ ቃል፣ መልእክታቱ ጌታን መጀመሪያ ስላዩ ደቀ መዛሙርት፣ ራእዩ ስለ ዘላለም ዘመን መነሻ ይናገራሉ። ተከታታይነታቸው ፍቅርን መሠረት ያደረገ ነው። ወንጌሉ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር፣ መልእክታቱ የእግዚአብሔርን ፍቅር በኅብረት ውስጥ ስለ መግለጥ፣ ራእዩ በፍቅር ዓለም ለዘላለም ስለመጠቅለል ይናገራሉ። የዮሐንስ ወንጌል ስለ ሕይወትና ስለ እውነት ይናገራል። ሕይወትንና እውነትንም በብርሃን ይመስላል። ሕይወትና እውነት የሰው አይደሉም። ከእግዚአብሔር ተቀብለን እፎይ የምንልባቸውና የምንገለጥባቸው ስጦታዎች ናቸው። ያለ ሕይወት መኖር፣ ያለ እውነትም ማወቅ የለም። ያ ሕይወትና ያ እውነት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። የወንጌሉን ዓላማ ራሱ ሲገልጥ እንዲህ ብሏል፡- “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል” /ዮሐ. 21፡31/።
ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ማለት የባሕርይ አምላክ ነው ማለት ነው። እኛ ከሰው የተገኘን ሰው እንደ ሆንን ኢየሱስ ክርስቶስም ከእግዚአብሔር የተገኘ እግዚአብሔር ነው። የእግዚአብሔር ልጅ የሚለው በዮሐንስ ወንጌል አገላለጥ፡-
1- የእግዚአብሔር አብንና የእግዚአብሔር ወልድን ጽኑ ፍቅር ይገልጻል። “መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው” /ዮሐ. 1፡18/። እቅፍ የሚለው ቃል ሁለት ነገሮችን ይገልጣል። የመጀመሪያው ፍቅርን ሲሆን ሁለተኛው አለመለየትን ነው። እግዚአብሔር ወልድ ከእግዚአብሔር አብ ጋር ባለመለየትና በፍቅር ከዘላለም ነበረ።
2- በአብና በወልድ መካከል እኩያነትንና አቻነትን ያመለክታል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር አባቴ ነው ሲል እኩያነትን ለማመልከት ነው። “ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ፥ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር” /ዮሐ. 5፡18/። ለአንድ አይሁዳዊ እግዚአብሔር አባቴ ነው ማለት ዕለታዊ መፈክሩ ነው። ኢየሱስ ግን አባቴ ነው ያለበት ድምፅ እኩያነትን አመልካች ስለነበር ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር።
3- የወልድ ልጅነትም እኛ ልጆች ከተባልንበት የተለየ ምሥጢርን ያሳያል። እርሱ ራሱ ቀላቅሎ አባታችን አላለም። አባቴ ብሏል። “እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ … ዓርጋለሁ” /ዮሐ. 20፡17/። እኛ ልጆች የሆነው በጸጋ፣ በልግስና፣ በማደጎ እንጂ እንደ ክርስቶስ በባሕርይ አይደለም።
የእኛ ልጅነትና የእርሱ ልጅነት ልዩነት እንዳለው።
1- እኛ የምንወለደው ከሥላሴ ነው። አብም አባት /ሮሜ. 8፡15/፣ ወልድም አባት /ማቴ. 19፡19/፣ መንፈስ ቅዱስም አባት /ዮሐ. 3፡5/ ተብሏል። የምንወለደው ከሥላሴ ነውና። ወልድ ግን የተወለደው ከአብ ብቻ ነው። በሥላሴ ውሳጣዊ ግብር አብ ወልድን ይወልዳል። በሥላሴ አፍአዊ ግብር እኛ ከሥላሴ እንወለዳለን።
2- የእኛ ልጅነት ፍጡርነትን አያስቀርም። እርሱ ልጅ ስለሆነ የአብ እኩያ ነው። በልጅነቱ ስግደት ተቀባይ ነው። እኛ ግን ልጆች ብንሆንም ስግደት አቅራቢ ነን። አንዳንድ የስህተት ትምህርቶች እየተሰሙ ነው። “ኢየሱስም ልጅ ነው እኛም ልጆች ነን። እኩል ነንና እርሱን መለመን የለብንም። በሥልጣን ማዘዝ ብቻ እንችላለን” የሚል ትምህርት በአደባባይ እየሰማን ነው። ይህ ብቻ አይደለም “ኢየሱስ ልጅ የሆነው በቤተ ልሔም ከተወለደ በኋላ ነው” የሚል ትምህርት እየተስፋፋ ነው። የዚህ ችግሩ በእኛና በክርስቶስ መካከል ያለውን ልጅነት ልዩነት እንዳለው አለመረዳት ነው። ከዘላለም የእግዚአብሔር ቃል ከሆነ ከዘላለም የእግዚአብሔር ልጅ ነው። አዎ የዮሐንስ ወንጌል የተጻፈው ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አምነን የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ነው። እግዚአብሔር ከስህተት ትምህርት ይጠብቀን።