የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የዮሐንስ ወንጌል ትርጓሜ / 8

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ማክሰኞ የካቲት 1/2008 ዓ.ም.
የዮሐንስ ወንጌል ዋና ዋና ትምህርት

1-   “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ” /ዮሐ. 11፡25/።
በአልዓዛር መቃብር ላይ የተናገረው ነው። ጌታችን የጊዜውን ትግል ድል በሚነሣ ስሙ፣ ቃሉና ተአምራቱ ይገለጣል። አብርሃም አልችልም በሚልበት ሰዓት እግዚአብሔር በኤልሻዳይ ስሙ ተገለጠለት /ዘፍ.17፡1/። አለመቻል ችግር አይደለም፣ በሚችለው አለማመን ግን ችግር ነው። ሞት ነግሦ ባለበት ስፍራ ስለ ትንሣኤ ይናገራል። ትንፋሽ ሲጨለጥም እርሱ ስለ ሕይወት ይናገራል። እግዚአብሔር ስለ አሁን ተናግሮ አያውቅም። ስለ አሁን ለመናገር ሰው መሆን በቂ ነው። ስለ ቀጣዩ ለመናገር ግን አምላክነት ያሻዋል። ያልኖርንበትን ኋላና የማናውቀውን ነገ የሚገዛ ጌታ ነው። እርሱ ትንሣኤ ብቻ አይደለም ሕይወትም ነው። ትንሣኤ ከሞት መንቃት ነው። ሕይወት ግን መኖር ነው። ትንሣኤ ሞትን ተበቃይ ነው፣ ሕይወት ግን እግዚአብሔርን የሚያከብር ነው። ትንሣኤ ከጨለማው ሥልጣን መላቀቅ ነው፣ ሕይወት ግን በክርስቶስ ግዛት ማረፍ ነው። ከሞት የነቁ ግን የማይኖሩ አሉ። ጌታችን ግን ትንሣኤ ብቻ ሳይሆን ሕይወትም ነው። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመጨረሻው የሚጀምር ትንሣኤ፣ በልምላሜ የሚገልጥ ሕይወት ነው። እርሱ ባለበት ሞትና ጭንገፋ የለም። ትንሣኤ ለሥጋ፣ ሕይወት ለነፍስ ነው። እርሱ በሥጋም በነፍስም የሚረዳ ነው። ከመቃብር ስፍራ አውጥቶ ከሰው ቁጥር የሚደምር፣ ትንሣኤ ልቡና ሰጥቶ በፍቅር የሚያኖር ነው። በሥጋ ተምሮ በልጥጎ በነፍስ ግን ፍቅር አልባ መሆን ትንሣኤን ከሕይወት ጋር አለመካፈል ነው። እኛስ የተነሣነው ለመኖር ይሆን? የአንዳንድ ሰው አነሣሥ ለመውደቅ ነው። የአንዳንድ ሰው አነሣሥ ሌላውን ለመጣል ነው። የአንዳንድ ሰው አነሣሥ ለኃጢአት ነው። ሕዝቅያስ ተነሥቶ ነበር። ከሞት መንገድ ተመልሶ አገርን የሚጎዳ ተግባር ፈጸመ /2ነገሥ. 20/። መነሣት ለመኖር ይሁንልን።

             2-   “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ” /ዮሐ. 14፡6/።
ቀጣዩ ምሥጢር ነው። የምሥጢርን አምላክ ለያዙ ግን ያለ መረጃ ቀጣዩ የሚያስደስት ነው። በዓለም ላይ የሚያኖረን ማወቃችን ብቻ ሳይሆን አለማወቃችንም ነው። የወዳጆቻችንን ስሜት፣ የአጋሮቻችንን ተግባር፣ የጠላቶቻችንን ዱለታ አለማወቃችን አንዱ የደስታችን ምሥጢር ነው። እግዚአብሔር እያወቀልን መኖር ልዩ ዋስትና ነው። ነገን አናውቅም፣ የነገን አምላክ ግን እናውቀዋለን። እግዚአብሔርን ብናውቅ አንዳንድ ነገሮችን ለማወቅ አንሻም። እርሱ ያውቅልናል። እግዚአብሔርን ስናውቅ እንደሚያውቅልን በማሰብ ደስ ይለናል። አንድ ንጉሥን ከማወቃችን በላይ እርሳቸው ቢያውቁን ደስ ይለናል። እግዚአብሔርን ከማወቃችን በላይ በእርሱ መታወቃችን ደስ ይላል። “እንዴት” የሚል ጥያቄ አፈጻጸምን የሚያመለክት ነው። እግዚአብሔር እንዴት? አይባልም። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእንዴት መልስ ሲሰጥ ነው፡- “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ” ያለው /ዮሐ. 14፡6/።

አዎ እርሱ መንገድ ነው፣ እርሱ እውነት ነው፣ እርሱ ሕይወት ነው። ያለ መንገድ መድረስ፣ ያለ እውነት ማወቅ፣ ያለ ሕይወት መኖር የለም። የማያሳስተው የቀና ጎዳና፣ የማይታበለው እውነት፣ የማይጠፋው ሕይወት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በእርሱ መንገድነት የሚሄዱ እውነትን ያውቃሉ፣ እውነትም ነጻ ታወጣቸዋለች። በዘላለም ሕይወትም ታከብራቸዋለች።
             3-   “እውነተኛው የወይን ግንድ እኔ ነኝ” /ዮሐ. 15፡1/።

አዳም ግንዳችን ነበር። ያ ግንድ በመበከሉ ቅርንጫፉ ሁሉ ተበክሎ ፍሬው መራራ ሆነ። ቅርንጫፉ እንደ ግንዱ ነው። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ዳግማዊ አዳም ሆኖ ወደ ዓለም መጣ። በእርሱ ያመኑ ሁሉ በእርሱ ላይ ይበቅላሉ። በእርሱ ላይ የበቀሉ ያፈራሉ። ማሻሻያ ለማድረግ አልመጣም። ከአሮጌው ግንድ ነጥሎ በራሱ ላይ ተከለን። በአሮጌው ግንድ ያለ ሐረግና ቅርንጫፍ ዕዳን ሲካፈል ይኖራል። በአዲሱ ግንድ ያለ ግን ሕይወትን ይካፈላል። አንዳንዴ ቤተሰባቸው በባዕድ አምልኮ ያለ ይፈራሉ። ግንዱ ላይ ስላሉ እኔንም ቢያጠቃ ይላሉ። በዘራቸው ርግማን ወይም ዕዳ ያለባቸው ይፈራሉ። መድኃኒቱ ግን አዲሱ ግንድ ላይ ሲተከሉ ከአሮጌው ግንድ በግድ ይለያሉ። በክርስቶስ ያልሆነ በአዳም ነው። ሦስተኛና ገለልተኛ ግንድ የለም። በአዳም ካለ የዘር የትውልድን አበሳ ይሸከማል። በክርስቶስ ያለ የዕዳውን ክፍያ ይቀበላል።

በእርግጥም አንተ አንተ ነህ። አንተ አንተ ስለሆንህ ይኸው እንኖራለን። ምስጋና ለስምህ ይሁን።

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።