የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ረቡዕ የካቲት 2/2008 ዓ.ም.
3- ቅድስት ሥላሴ
በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ከምናገኛቸው ዋና ዋና ትምህርቶች አንዱ ቅድስት ሥላሴ ነው። የቅድስት ሥላሴ ትምህርት የሃይማኖት፣ የአገልግሎት፣ የምስጋና፣ የምግባር መሠረት ነው። ሥላሴ የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ ባይገኝም ትምህርቱ ማለት የሦስትነት ምሥጢር ግን በስፋት ቀርቦአል። በስፋት ከቀረበባቸው ክፍሎች አንዱ የዮሐንስ ወንጌል ነው። ቅድስት ሥላሴ ማለት የተለየች ሦስትነት ማለት ነው። አንድነቱ ሦስትነቱን ሳይጨፈልቀው፣ ሦስትነቱ አንድነቱን ሳያፈርሰው የሚኖረው እግዚአብሔር በእውነት ድንቅ ነው። የተለየ አንድነትና የተለየ ሦስትነት በመሆኑ ከምሳሌ አስረጂነት በላይ ነው። የምናምነው አምላክ በስም፣ በአካል፡ በግብር፣ በኩነት ሦስት ሲሆን በመለኮት፣ በባሕርይ፣ በህልውና፣ በአገዛዝ፣ በሥልጣን አንድ ነው። የአካላት ሦስትነት የምንለው እያንዳንዱ አካል በራሱ አቋም፣ መልክና ገጽ መገኘቱ ነው። አብ የራሱ የሆነ አካል፣ መልክና ገጽ አለው። ወልድ የራሱ ሆነ አካል፣ መልክና ገጽ አለው። መንፈስ ቅዱስም የራሱ የሆነ አካል መልክና ገጽ አለው። የግብር ሦስትነት የምንለው አብ ወላዲና አስራጺ ነው። የወልድ አባት የመንፈስ ቅዱስ አስገኚ ነው። ወልድ ግብሩ ተወላዲነት ወይም መወለድ ነው። የተወለደው ከአብ ነው። የመንፈስ ቅዱስ ግብር መሥረጽ ነው። የሠረጸውም ከአብ ነው። የኩነት ሦስትነት የምንለው ኩነት ማለት መሆን /ኋኝነት/ ማለት ነው። አብ ልብ፣ ወልድ ቃል፣ መንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ መሆኑ ኩነት ይባላል።
የሦስትነት መጠሪያዎች መፋለስ፣ መደባለቅና መቀላቀል የለባቸውም። አብ የራሱ አካል አለው፣ ወልድ የራሱ አካል አለው፣ መንፈስ ቅዱስም የራሱ አካል አለው። የአካላት መጨፍለቅ ሳይኖርበት እግዚአብሔር በአንድ ምስጋና ይኖራል። የስም ተፋልሶ የለም። የአብ ስም ወልድና መንፈስ ቅዱስ አይጠሩበትም። ምክንያቱም አብ የሚለው ስም የአካሉ፣ የህልውናው መጠሪያ ስለሆነ ነው። ወልድና መንፈስ ቅዱስም በስማቸው ጽናት ይኖራሉ። የግብር መደባለቅ ሳይኖርም አብ ወላዲ እንደ ተባለ ይኖራል፣ ወልድም ተወላዲ፣ መንፈስ ቅዱስም ሰራጺ እንደ ተባለ ይኖራል። ሦስት ግብር አንድ መንግሥት፣ ሦስት ኩነታት አንድ ሥልጣን ሆኖ ይኖራል።
የዮሐንስ ወንጌል ይህን በስፋት ይነግረናል። መዳናችን የሥላሴ ምክር እንደሆነ አብ ዓለምን አፈቀረ፣ ወልድ ቤዛ ሆነ፣ መንፈስ ቅዱስ እውነቱን ለሰዎች አተመ በሚል አሰሳ ያስረዳናል /ዮሐ. 3፡16/። ወልድ በመስቀል ላይ ሞቶ የገለጠው የሥላሴን ፍቅር ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር በፍቅር አንድ ነውና። ለዚህ ነው የቀደሙት አባቶች መዳናችንን ሥላሴያዊ ለማድረግ የሚተጉት። ምስጋናቸውን ሲያቀርቡም፡- “በአንድ ልጅህ በእርሱ ያለ ክብር ጽንዕ ላንተ ይገባል ከእርሱ ጋራ ከመንፈስ ቅዱስም ጋራ ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን” ይላሉ።
የዮሐንስ ወንጌል ሦስቱን አካላት በተናጠል ያስረዳል። ስለ አብ ፍቅር፣ ስለ ወልድ ቃልነት፣ ስለ መንፈስ ቅዱስ አስተማሪነት ይናገራል። አብ፣ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የሚሉት ስሞች ኦልኒ ጂሰሶች እንደሚሉት የአንዱ አካል ሦስት መጠሪያ ስሞች ሳይሆኑ የሦስቱ አካላት ስሞች መሆናቸውን ያስረዳናል። ወልድንም በኩነት ስሙ ቃል ይለዋል። ቃል ልብና እስትፋስ አለው። ልቡ አብ፣ እስትንፋሱም መንፈስ ቅዱስ ነው። ይልቁንም የመንፈስ ቅዱስን አካላዊነት የሚክዱ ሰባልዮሳውያንና አርዮሳውያንን የሚያስተምር ብዙ ትምህርት አስፍሯል /ዮሐ. 14፡15፤ቁ. 26/። መንፈስ ቅዱስ አጽናኝ፣ አስተማሪ፣ ወደ እውነት ሁሉ የሚመራ፣ አስታዋሽ መሆኑ ተገልጧል። አካል የሌለው ማጽናናት፣ ማስተማር፣ ማስታወስ አይችልም። ጌታም እርሱን ተክቶ እንደሚያጽናና ተናግሯል /ዮሐ. 14፡18/። አካል ያለውን ወልድ የሚተካ አካላዊ መንፈስ ቅዱስ ነው። መንፈስ ቅዱስ ከአብ ብቻ ይሰርጻል /ዮሐ. 15፡26/። መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ይሰርጻል የሚሉትን የሚያርም ትምህርት ይዟል። ይህ ብቻ አይደለም የሦስቱን አካላት የክብር፣ የህልውና፣ የሥልጣን አንድነትም ይገልጻል /ዮሐ. 14፡9፤10፡30፤5፡21/።
በአሚነ ሥላሴ ያጽናን።