“የዳዊት ልጅ የአብርሃም ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ትውልድ መጽሐፍ።” /ማቴ. 1፡1/ ።
ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌሉን በአራማይክ ቋንቋ በ44 ዓ.ም ገደማ ጽፎታል ። አራማይክ የዕብራይስጥ ቤተሰባዊ ቋንቋ ነው ። ጌታችን በምድር በነበረ ጊዜ በስፋት በምድረ እስራኤል የሚነገር ቋንቋ ነበር ። ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌሉን የጻፈው ለአይሁዳውያን ነው ። በአዲስ ኪዳን ውስጥ በቀጥታ ለአይሁዳውያን የተጻፉ መጻሕፍት የዕብራውያን መልእክት ፣ አንደኛና ሁለተኛ ጴጥሮስ እንዲሁም የያዕቆብ መልእክት ናቸው ። እነዚህ መልእክታት የተጻፉት ለክርስቲያን አይሁዶች ሲሆን ዓላማቸውም ክርስቶስን በማመን እንዲጸኑ ነው ። የማቴዎስ ወንጌል ግን የተጻፈው በክርስቶስ ላላመኑ አይሁድ ሲሆን ክርስቶስ የብሉይ ኪዳን ትንቢት ፈጻሚ መሆኑን አምነው እንዲቀበሉት ለማስገንዘብ ነው ። ቅዱስ ማቴዎስ በእያንዳንዱ ምዕራፍ ላይ ከብሉይ ኪዳን ትንቢት በመጥቀስ በክርስቶስ ፍጻሜ እንዳገኘ ይገልጻል ። ቅዱስ ማቴዎስ ክርስቶስ መሢሕ መሆኑን ለመግለጥ የተጠቀመው ሌላው ዘዴ የትውልድ ሐረግን በመዘርዘር ክርስቶስ የዳዊትና የአብርሃም ልጅ መሆኑን መግለጥ ነው ። አይሁዳውያን በዘር ቆጠራ ያምናሉ ። ስለዚህ ክርስቶስ ከአብርሃም ዘር ተወልዶ ተስፋውን የፈጸመ ፣ በርግጥም የዳዊት ልጅ እንደሆነ ይገልጣል ።
ለአይሁዳውያን ዳዊት የሚያከብሩት ንጉሣቸው ፣ አብርሃም ታላቁ አባታቸው ነው ። ክርስቶስ በሥጋ የመጣው ከእነዚህ ዘር ነው ። አብርሃም ስምንት ልጆች ቢኖሩትም ከይስሐቅ ዘር ክርስቶስ መጣ ፣ ዳዊትም ብዙ ልጆች ቢኖሩትም ከሰሎሞን ዘር ክርስቶስ መጣ ። እነዚህ ቅዱሳን በልጆቻቸው ክርስቶስን አይተዋል ። አብርሃም ለእግዚአብሔር ያለውን ፍቅር ለመግለጥ ልጁን መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል ። ይስሐቅ ግን ሌላ ቤዛ በማግኘቱ ተርፏል ። በጌታችን ቤዛነት ግን እግዚአብሔር ለሰው ያለው ፍቅር ተገልጧል ። ዳዊትም በሰሎሞን ክርስቶስን አይቷል ። ሰሎሞን ማለት ሰላማዊ ማለት ነው ፣ ክርስቶስም የሰላም አለቃ ተብሏል ። በይስሐቅ አምሳል ለክርስቶስ የተነገረውን ትንቢት ሐዋርያው ይገልጣል፡- “መጽሐፍም እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ፡- በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ።” /ገላ. 3፡8/ ። በሰሎሞን አምሳልም ለክርስቶስ የተነገረውን ትንቢት የዕብራውያን ፀሐፊ ይገልጣል፡- “እኔ አባት እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል” ዕብ. 1፡5 ። ይህን ቃል ለዳዊት የነገረው እግዚአብሔር ነው ። 2ሳሙ. 7፡14 ።
እንደ ዳዊት እነ አብርሃም በትንቢት መነጽር ፣ በተስፋ መስተዋት ያዩትን ክርስቶስ አይሁድ አይተው ሊያምኑበት ስላልቻሉ ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌሉን ይጽፍላቸዋል ። ምክንያቱም አይሁድ የሚመኩበት ብሉይ ኪዳን ወይም ቶራ ክርስቶስን ካላመኑ ሐሰተኛ ትንቢት የያዘ መጽሐፍ ይሆናል ። ዳግመኛም በክርስቶስ ካላመኑ ሕጉም ይጣላቸዋል ። ክርስቶስን መጣል የያዙትንም መጣል ነውና ።
አብርሃም የብኵር ልጁ እስማኤል ቢሆንም እግዚአብሔር ግን በታናሹ ልጅ በይስሐቅ በኩል በሥጋ መጣ ። ሰሎሞንም ከቤርሳቤህ የተወለደው ሁለተኛ ልጅ ቢሆንም ክርስቶስ በሥጋ ከእርሱ ዘር መጣ ። እግዚአብሔር ታናናሾችን አይንቅም ። የክርስቶስን የዘር ሐረግ ስናጠና እግዚአብሔር የተናቁትን እንደሚያከብር እንረዳለን ። አብርሃም ስምንት ቢወልድም በአንዱ እግዚአብሔር ሠራ ፣ ዳዊትም ብዙ ቢወልድም በአንዱ እግዚአብሔር ተጠቀመበት ። ምናልባት ብዙ ወገን የለኝም እንል ይሆናል ። እግዚአብሔር ግን በአንዱ ይሠራል ። የአገራችን ሰው፡- “ሺህ ቢወለድ ጠቃሚው አንድ ነው” ይላል ። ክርስቶስ የአብርሃም ዘር ነውና ምድርን ባርኳል ። የዳዊት ዘር ነውና ምድርን ገዝቷል ። ከአብርሃም ዘር በመወለዱ መላውን ዓለም ባረከ ፣ አብርሃምም አበ ብዙሃን /የብዙዎች አባት/ ሆነ ። ዘላለማዊው ንጉሥ ክርስቶስ ወልደ ዳዊት ተብሎ በመወለዱ የዳዊት ስም የማይጠፋ ሆነ ።
ዘመን የማይቆጠርለት መለኮት በለበሰው ሥጋ ዘመን ተቆጠረለት ። በማይመረመር ልደት ከአብ የተወለደው ምሥጢር በሆነ ልደትም ከድንግል ተወለደ ። እግዚአብሔር አብ ሰው ቢሆን በሰማይ አባት በምድር ልጅ ይባል ነበረ ። ነገር ግን የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ በመሆኑ አብ አንድ ልጅ በሰማይና በምድር አለው ። በዚህም እምነታችን ወልድ ዋሕድ /አንድ ልጅ/ ብሎ የሚያምን ሆነ ።
የትውልድ መጽሐፍ ይላል ። በክርስቶስ የትውልድ ሐረግ ውስጥ የተጠሩት ወገኖች እንደ ይሁዳ ያሉ የሕይወት ድካም ያለባቸው ሰዎች ፣ እንደ ሩት ያሉ አሕዛባዊ ወገኖች ናቸው ። እርሱ እኛን ይቀድሳል እንጂ በእኛ አይረክስም ። ክብርም ምስጋናም ከገናናው መንግሥቱ ይሁን ። አሜን ።