የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የጊዜ ፈጣሪ

“ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደ ሆነ፥ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ” የሐዋ. 17፡26-27
አንድ ራሽያዊ፡- “ትንሽ ድግስ ነበረኝ” አለ ። “ምንድነው ?” ሲሉት “ሚስቴ ሠላሳ ዓመቷን ያከበረችበትን አሥረኛ ዓመት እያከበርን ነበር” አለ ይባላል ። ዕድሜ በቀደመው ዘመን ተጨምሮ ይነገር ነበር ። ባለንበት ዘመን ደግሞ ተቀንሶ ይነገራል ። ኖሮ አልኖርኩም ከማለት በላይ ክህደት የለም ። ዕድሜ የሚደበቀው የሠራሁበት ነገር የለም ብለን ስናስብ ነው ። እኛ ባንሠራም እግዚአብሔር ሠርቶልናል ። እርሱ ባይዋጋልን ኑሮ ይህን ዕድሜ ማግኘት አይቻለንም ነበር ። ዕድሜን የሚሰጥ እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ነገሥታትና ጠቢባን ፣ ደግሞም ባለጠጎች ሊሰጡት የማይችለውን ዕድሜ ካገኘን በጣም ዕድለኞች ነን ። ዕድሜ ለማግኘት ነገሥታትን ለምኑ ብንባል “ያለፈውን ዓመት ግብር ስላልከፈልህ አይሰጥህም” ይሉን ነበር ። ዕድሜን ለማግኘት ጠቢባንን ጠይቁ ቢባል “ተጨማሪ ጥናት ላይ ስለሆንሁ ልረዳህ አልችልም” ይሉናል ። ዕድሜን ለማግኘት ባለጠጎችን ለምኑ ብንባል “ባለፈው ስቀልድ አልሳቅህልኝም ፣ ስለዚህ መኖር አይገባህም” ይሉናል ። ዕድሜን በሰው ፊርማ ብናገኝ ለአንድ ለሁለት ጊዜ ይፈርሙልናል ። ከዚያ በኋላ በራቸውን ዘግተው የለሁም ብለው ይመልሱናል ። ዕድሜ የአንድ አምላክ ስጦታ ነው ። በዚህ ቀን ሥልጣን የማይስበው ፣ ገንዘብ የማይገዛው ፣ ጥበብ የማይጠራው ዕድሜ ስለተሰጠን ልናመሰግን ይገባናል ።
ሐዋርያው ጳውሎስ በአቴንስ ጉብኝቱ እንግዳ ነገሮችን አየ ። የአርዮስ ፋጎስ አደባባይ አዲስ እውቀትና መገለጥ አለኝ ብሎ የሚያስብ ሰው በነጻነት የሚናገርበት ሲሆን እንግዳ ነገርን ለመስማት የተራቡ ጆሮ ያላቸው ግሪካውያንም  ተከማችተው የሚሰሙበት ነው ። ሐዋርያው ጳውሎስም እኔም የምናገርለት ጌታ አለኝ ፣ የደረስኩበት ሳይሆን የደረሰልኝ ጥበብ አለ በሚል ድምፀት መናገር ጀመረ ። አቴንስ ብዙ ሺህ ጣዖታት ያሉባት ብቻ ሳትሆን “ለማይታወቅ አምላክ” የሚል ስም የተጻፈበት አዲስ መሠዊያም የታየባት ናት ። አዲስ አምላክ ሲገኝ ይህ መሠዊያ ይሰየማል ማለት ነው ። ብዙ አማልክት የአምልኮን ጥም አይቆርጡም ። እውነተኛውን አምላክ እስካላመለክን በማምለካችን ብቻ ደስታ አናገኝም ። ማምለካችን ብቻ ክብር አይሰጠንም ፣ የምናመልከው እውነተኛ አምላክ መሆኑን ማወቅ አለብን ።
ሐዋርያው የንግገሩ ማዕከል ሊመለክ የሚገባው ሁሉን የፈጠረ ፣ ዘመንን ያስጀመረ ዳግመኛም ሊፈርድ የሚመጣው ነው እያለ ነው ። ጣዖታት ግን የሰው እጅ ሥራ በመሆናቸው ፈጣሪነት የሌላቸው ፍጡራን ፣ ዘመንን ማስጀመር የማይችሉ ግዑዛን ፣ ሊፈርዱ የማይችሉ ድኩማን ናቸው ። ጣዖታት የምንሸከማቸው ፣ እግዚአብሔር ግን የሚሸከመን አምላክ ነው ። ሐዋርያው፡- “ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደ ሆነ” ይላል ። ምርምሮችን አልነቀፈም ። በምርምሮች ግን ሁለት ነገሮችን አስተውሏል ። የመጀመሪያው ሰው አምላኩን ካላገኘ እረፍት የለውም ። ምርምር እረፍት አልባነት ነውና ። ሁለተኛው በምርምር የሚያገኙ ጥቂቶች ናቸው ፣ ምርምርም ስለ እውነተኛው አምላክ የማሳወቅ አቅሙ አነስተኛ ነው እያለ ነው ። በምርምር ውስጥ ምናልባት “አንድ ኃይል አለ” የሚሉ ሰዎችን ማግኘት ይቻላል ። ያ ኃይል ግን እግዚአብሔር መሆኑን ለማወቅና ለመገንዘብ የስብከት ድምፅ ያስፈልጋል ። እግዚአብሔር ከምርምር ይልቅ በመገለጥ የሚታወቅ አምላክ ነው ። እርሱን ለሚፈልጉት ሁሉ ራሱን ይገልጣል ። የአቴንስ ሰዎች የፍልስፍና ሰዎች ስለሆኑ ወደ እውነተኛው አምላክ መድረስ አልቻሉም ። ፍልስፍና በራስ መመራት ሲሆን እምነት ግን በእግዚአብሔር ፈቃድ መራመድ ነው ። የፍልስፍና መነሻው ምድር ሲሆን እምነት ግን ሰማያዊ መገለጥ ነው ። ፍልስፍና በራስ መተማመን ሲሆን እምነት ግን በእግዚአብሔር መደገፍ ነው ።
ሐዋርያው በመቀጠል፡- “እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ” ይላል ። ከአንድ ፈጠረ የሚለው በቀጥታ ከአንድ አዳም የተገኘን እንደሆንን የሚያስረዳ ነው ። ሐረጉ መብዛቱ እንጂ ሥሩ አንድ ነው ። ሁላችንም የአዳም ልጆች ነን ። በሁሉም እምነቶች አዳም መነሻ እንደሆነ ይነገራል ። ስለዚህ ይህ ዓለም ሰፊ ቤተሰብ እንጂ ብዙ ቤተሰብ አይደለም ። ወንድማማች እንጂ ባላጋራ አይደለም ። ከአንድ መፈጠርም ከአንዱ እግዚአብሔር መበጀትም ነው ። በዚያ ዘመን የነበሩ ሰዎች ሁለት አማልክት አሉ ብለው ያምኑ ነበር ። የሚታዩ ነገሮችን የፈጠረ ንዑስ አምላክ ሲሆን ረቂቅ ነገሮችን የፈጠረው ግን ዐቢይ አምላክ ነው ብለው ይናገሩ ነበር ። ይህ ዓለም ግን ሥርዓቱና መገናዘቡ አንድ አምላክ እንዳበጀው ምስክር ነው ። በአንድ ግዛት ውስጥ ብርሃን ፣ ነፋስ ፣ ሙቀት አሉ ። አይገፋፉም ። አንድ አምላክ ስለፈጠረን መገፋፋት አይገባንም ። እግዚአብሔር አምላክ የፈጠረን እርሱን እንድንፈልግ ነው ። ሰው አምላክን መፈለጉ በታሪክ ሂደቱ ያዳበረው ፣ ወይም ያስፈልገኛል ብሎ ያመነበት ሐቅ ሳይሆን ያለ እግዚአብሔር እንዳይኖር ሁኖ የተፈጠረ ነው ። ከብት ዕለቱን ተወልዶ ይቆማል ፣ ሰው ግን ይታቀፋል ። ከብት ፍቅር ባያገኝም አይጎዳም ። ሰው ግን ብቸኝነት መንገዱን ያዘገይበታል ። የሚያቅፈውና አለሁ የሚለው ግን እግዚአብሔር ነው ። መፈለግ ታላቅ ጥማት ነው ። መፈለግ አምልኮ ነው ። መፈለግ የምንፈልገውን ለማወቅ መጓጓት ነው ።
“የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው ። ቢሆንም ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም” ይላል ። የምንኖርበትን ቦታና ዘመን የመደበ እግዚአብሔር ነው ። ኢትዮጵያ ለመወለድ ለእግዚአብሔር አሳብ ያቀረበ የለም ። እኛን ከዚህ አገር ሲፈጥረን አልተሳሳተም ። እርሱ ቦታችንና ዘመናችንን የመደበ ነው ። የተወሰኑት የሚለው ቃል በእውነት ድንቅ ነው ። የተሰፈረ ዕድሜ ነው ያለን ። ያንን በጉልበታችን ማለፍ አንችልም ። እስከ መቼ እንደምንኖር አናውቅም ። አንዳንድ ነገሮች መሆን አለመሆናቸውን እርግጠኛ አይደለንም ። መሞታችን ግን እርግጥ ነው ። ከእርግጡ ነገር ጀምረን ማሰብ ብንጀምር ሁሉም ነገር ቀና ይሆን ነበር ። ቢሆንም ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም ። ነገሥታት ሕዝባቸውን የሚያውቁት በነፍስ ወከፍ ሳይሆነ በጅምላና በቊጥር ነው ። እርሱ ግን ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም ። እውነተኛው አምላክ ከእኛ ዓለም የራቀ ነው ብለው ያስተምሩ ነበር ። የእግዚአብሔርን ሰው መሆን መቀበል ያቃታቸው ቅዱሱ ጌታ ርኩስን ሥጋ ሊለብስ በፍጹም አይችልም ብለው በማመናቸው ነው ። በእነርሱ እምነት ሥጋ ግዙፍ በመሆኑ ርኩስ ነው ። እርሱ ግን ከሥጋችን ሥጋ ፣ ከነፍሳችን ነፍስ ነሥቶ ከእኛ ጋር የተዛመደ ነው ።
ዘመንን የሰጠና ፣ የዕድሜን ዳርቻ ያበጀ እርሱ ነው ። ዘመንን የሚሰጠንም እርሱን እንድናከብርበት ነው ። ስንኖር የተመጸወትነው ዕድሜ እንደሆነ ማሰብ አለብን ። ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ስንነሣ ብኖርና እግዚአብሔር ቢፈቅድ ማለት አለብን ። ሐዋርያው ያዕቆብ፡- አሁንም፡- ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህ ከተማ እንሄዳለን በዚያም ዓመት እንኖራለን እንነግድማለን እናተርፍማለን የምትሉ እናንተ ፥ ተመልከቱ ፥ ነገ የሚሆነውን አታውቁምና ። ሕይወታችሁ ምንድር ነው ? ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፍዋለት ናችሁና ። በዚህ ፈንታ፡- ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም ይህን ወይም ያን እናደርጋለን ማለት ይገባችኋል።” በማለት አዝዟል ። ያዕ. 4፡13-15 ። እኛ ታይቶ ጠፊ ነን ። ሩቅ አስበን ቅርብ የምናድር ነን ። ለዓመት አቅደን ዛሬ ማታ የምንጠራ ነን ። ፈረንጆቹ፡- “ሰው ሲያቅድ እግዚአብሔር ይስቃል” ይላሉ ። በሰርግ ካርዶች ላይ ብንኖርና ጌታ ቢፈቅድ የሚል ቃል ሰፍሮ ብዙ ጊዜ ይነበባል ። ሰርግ ይደገሳል ግን ብንኖር ነው ። ወረቀት ይበተናል ግን ብንኖር ነው ። ሚዜዎች ይለማመዳሉ ግን ብንኖር ነው ። ከወር በኋላ የሚያገቡ በአደጋ ሞተዋል ። በሙሽርነት ቀናቸው የሞቱ አያሌ ናቸው ። ለደስታ የተተኮሰ ጥይት ሙሽሮችን ገድሏል ። የሰርጉ ድግስ የሬሳ መሸኛ ይሆናል ። እኛ በጣም ደካማዎችና ከእግዚአብሔር ፈቃድ በቀር ምርኩዝ የሌለን አፈር ነን ።
የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አባት ራስ መኰንን ከግዛታቸው ከሐረር ወደ አዲስ አበባ ተጠርተው ሊመጡ ሲሉ የታያቸው ነገር ነበርና “ልጄን ተፈሪን አደራ” አሉ ። ወዳጆቻቸውም ልባቸው ስለ ፈራ፡- “መቼ ይመለሳሉ?” አሏቸው ። ራስ መኮንንም፡- “ስለመሄዴ እንጂ ስለመመለሻ ጊዜዬ አላውቅም” አሉ ። ጥቂት ጉዞ እንደ ጀመሩ ቁልቢ ላይ ታመው እዚያው ሞቱ ። ስለመውጣታችን እንጂ ስለመመለሳችን የሚያውቅ እግዚአብሔር ብቻ ነው ። እኛ አፈርና ትቢያ ነን ። ተንጠራርተን የምንናገር ሳይሆን ትሑት ሁነን ለአምላክ ክብር መስጠት የሚገባን ነን ።
የዓመታት ዘመናት ፈጣሪ እግዚአብሔር ሆይ ጊዜም ሎሌህ ነውና እናመሰግንሃለን ። በጊዜ ውስጥ ልደትና ሞትን ፣ ክብርና ዝቅታን የምታፈራርቅ ፣ ጊዜን መንበርህ መፍረጃህ አድርገህ ስንት የምታሳየን ጌታ ተመስገን ። በሰጠኸን ዕድሜ አንተን አስደስቶ ማለፍ ይሁንልን ። ሥጋችንን ቀድስ ፣ ነፍሳችንን አሳርፍ ። ለዘላለሙ አሜን ።
የዕለቱ መና 24
ግንቦት 24 ቀን 2011 ዓ.ም.
ዲአመ

ያጋሩ