የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የጌርጌሴኖን ታማሚ/2

 ማር. 5፡1-20
የመጀመሪያው በመቃብር ይኖር ነበር ። እያለ የሌለ ፣ እየኖረ ያልኖረ ፣ በቁም የሞተ ፣ የሚንቀሳቀስ ሬሳ ፣ ዕድር ያልተበላበት ሙት ፣ ዕቁብ የማይገባ መናጢ ፣ የማያጭ የማይታጭ ፣ የማይመርጥ የማይመረጥ ፣ ሕዝብ ሲቆጠር የማይቆጠር ፣ ጎረቤት የሌለው በረኸኛ ፣ ዱር ቤቱ የሆነ አመለኛ ፣ ባልተመለሰ የሚባል ፣ ከአራዊት ይልቅ የሚፈራ ፣ እሳት የማያስጭሩ የመቃብር ጎረቤቶች ያሉት ፣ ሲጮህ ቢውል የማይመልሱ ጓዶችን ያፈራ ፣ ከሰፈር የራቀ ፣ ከሕያዋን ማኅበር በግድ የተገለለ ፣ አለሁ የማይል ፣ አለ የማይሉት ፣ ስጡኝ የማይል ፣ ይሰጣል ተብሎ ተስፋ የማይደረግ ፣ የቤት ቊጥር የሌለው ፣ መቃብር አልጋው ፣ ሙታን ትራስ የሆኑለት የጨለማ ነዋሪ ነበር ። ክብር ይግባውና ጌታችን ፣ ሊያገኘው ባሕር አቋርጦ የመጣው ይህን ሰው ነበር ።

ዓለሙ ተስፋ የቆረጠባቸው እነርሱም በዓለሙ ተስፋ የቆረጡ ፣ እንደገና አብባለሁ ብለው የማያስቡ ፣ በቁም የደረቁ ፣ በቁም ያረሩ ብዙ ጎበዞች ዛሬም አሉ ። ሳይነጋ በሱስ የሚቃጠሉ ፣ ከጨዋ ሰው ርቀው መሰላቸው ጋር በደቦ የሚሞቱ ፣ ጠባ ለመጠጥ ፣ መሸ ለሱስ የሚንከለከሉ የመቃብር ነዋሪዎች ዛሬም አሉ ። በሰው የተገለሉ ፣ ብዙ የሆነው ማኅበረሰብ ጥቂትነታቸውን በፍቅር ያላሸነፈው ፣ ለራሳቸው የተተዉ ፣ ይመጣሉ ተብለው የማይጠበቁ ፣ በጎዳና የወደቁ ፣ ክረምት ብርድ ልብሳቸው ፣ ፀሐይ አንሶላቸው የሆኑ ፣ ከእንስሳ አንሰው ከመንደር የወጡ ፣ ትራፊም ለመለመን ነጻነት የሌላቸው ፣ እንደ ሰው ጀምረው እንደ ሰው መኖር ያቃታቸው ፣ ኑሮአቸው ሞት ስለሆነ ሞታቸው ኑሮ እንዲሆን የሚናፍቁ ብዙ ቀበዝባዞች አሉ ። እነዚህን የሚፈልግ ሰባኪ የለም ። በባለጠጋ የሚጣላ አገልጋይ እንጂ እነዚህን ሰው ለማድረግ የሚተጋ የእግዜር ሎሌ እየጠፋ ነው ። ጌታ ግን ሰውን ለማዳን የቤት ቊጥር አይፈልግም ። ያለ ቀብድ የሚወድና የሚያገለግል እርሱ ብቻ ነው ።
ሁለተኛ፡- ይህ ሰው በእጅ ሰንሰለት ፣ በእግረ ሙቅ የታሰረ ሰው ነበር ። ይህ ሰው የመቃብር ነዋሪ ብቻ ሳይሆን በታላቅ ብረት የተዘጋበት ሰው ነበር ። ሰንሰለቱንና ብረቱን ይበጣጥሰው ነበር ። ከቤተሰቡም ፣ ከመንደሩም ያራቀው ይህ ኃይለኝነቱ ነበር ። ከቤተሰብ በላይ ሲሆን መንግሥት ይይዛል ። ፍጹም አቅሉን የሳተውን ግን መቃብር ይቀበለዋል እንጂ ማንም ሊይዘው አይችልም ። ጥፋተኛ ተብሎ መወቀስ ፣ በሕግም ተከሶ ወኅኒ መጣል ተስፋ ለሚደረግ ሰው ነው ። ይህ ሰው ግን ጥፋቱ ፣ ጥፋት ተብሎ አይቆጠርም ነበር ። አእምሮውን ካጣ ሰንብቷል ።
በኅሊና ያለ ሰው የማያደርጋቸውን ነገሮች በማድረግ የታሰሩ ብዙ ወገኖች አሉ ። አብደዋል ተብለው ስህተታቸው የጸደቀላቸው ፣ በፍቅርም በሕግም ሊመለሱ ያልቻሉ አያሌ ናቸው ። እየበዙ ሲመጡ ስህተታቸው የጸደቀላቸው ፣ ኃጢአታቸው የሕግ ከለላ ያገኘላቸው ብዙዎች ናቸው ። ይህን ሰንሰለት ሊበጥስ ፣ ከዚህ የእግር ብረት ሊያድን የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ጌታችን ወደዚህ ሰው መጣ ። ሰው ያቃተውን እኔ ያቅተኛል የማይለው ሊፈልገው መጣ ። ከሰው አቅም በላይ የሆነ ሁሉ ከእርሱ አቅም በታች ነው ። የደረቀውን ተስፋ በማለምለም የታወቀ ነው ።
ሦስተኛው፡- በመቃብርና በተራራ ይጮኽ ነበር ። የሚጮኸው ሌሊትና ቀን ነው ። በቁሙ ሲዖልን ተሸክሞ የሚዞር ሰው ነበር ። ውስጡ ካልጮኸበት የሚጮህ ሰው የለም ። ጩኸት ለጩኸት የሚሰጥ መልስ ነው ። ትልልቅ የድምፅ ማጉያ ሥር ተቀምጠው የማይሰማቸው ፣ በደማቅ ዘፈኖችና ዳንኪራዎች ውስጥ ሌሊትና ቀን የሚጮኹ አሉ ። ከራስ ለማምለጥ ፣ ትላንትን ለመርሳት የሚደረግ ጥረት ነው ። ጌታችን ይህን ሰው ለመፈለግ መጣ ። ዛሬም በዚህ ውስጥ የሚያልፉትን እርሱ ይፈልጋቸዋል ። ደም በደም አይጠራም ፤ በደልም በበደል አይነጻም ።
አራተኛው፡- ሰውነቱን በድንጋይ ይቧጭር ነበር ። ሰውነቱን ራሱ እያፈረሰው ፣ የደሙን ጋን ራሱ እየሸነቆረው ነበር ። ራሱን ለማጥፋት በብርቱ ይታገል ነበር ። ለዚህች ቀን ስላሰበው ግን በሕይወት ቆየ ። ጌታ ይህን ምስኪን ፍለጋ መጣ ። ከኑሮ ይልቅ ሞት ቅርቤ ነው የሚሉ ፣ ሞቼ በተገላገልሁ የሚሉ አያሌ ናቸው ። ሞተው እንደሚያርፉት ግን ምን ያህል እርግጠኛ ናቸው ? ሞቶ የሚያርፈው አሳራፊውን አምላክ ያገኘ ብቻ ነው ። የኃጥአን ሞታቸው ኀሣር ፣ የጻድቃን ሞታቸው ሕይወት ነው ።
ያ ሰው የማያስቀርብ ሰው ፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በሩቅ ሲያየው ሰገደለት ። አጋንንቱ እንዳትሣቅየኝ እለምንሃለሁ አለ ። ያደረበት ሌጌዎን የሚባል ጭፍራ ነበር ። ሌጌዎን ጭፍራ ማለት ነው ። አንድ ጭፍራ በሮማ ወታደር አደረጃጀት እስከ ስድስት ሺህ ሠራዊት ይይዛል ። ይህ ሰው የተሸከመው ጉድ ብዙ ነበር ። ያስጨነቀው የሚጨነቅበት ጊዜ ደረሰ ። በተራራ ላይ ያሉ የእርያ መንጋ ነበሩና አጋንንቱ በዚያ ለመግባት ለመኑት ። አጋንንት በእርያ ላይ እንኳ ሥልጣን የለውም ። ጌታ ፈቀደላቸው ፣ እርያዎቹም እየተጣደፉ ወደ ባሕር ሰጠሙ ። ይህ በሽተኛ ከእንቅልፍ ሲነቃ እንዴት ካለ ነገር እንደ ዳነ አያውቅም ነበር ። ስለዚህ ጌታችን የመዳኑን ታላቅነት እንዲገነዘብ አፋፍ ላይ ያሉ እርያዎች ሲሰጥሙ እንዲያይ አደረገው ። ደግሞም ከንብረት የሰው ዋጋ እንዲበልጥ ለማስተማር ይህን አደረገ ። የከተማው ሕዝብ ግን በሰውዬው መዳን ከመደሰት በእርያዎች ባሕር መስጠም አዝነው ከከተማችን ውጣልን ብለው ለመኑት ። ግባልን እንጂ ውጣልን ተብሎ መለመኑ የሚደንቅ ነው ። በሰው ዘንድ ንብረት ከፍ ያለ ዋጋ አለው ። የሰው ዋጋ ከፍ ያለው በክርስቶስ ዘንድ ነው ።
ዛሬም ለጌርጌሴኖን ታማሚዎች መድኅን አለ ። ከሰው ርቄ ብቻዬን ነኝ ለሚሉ ፣ በሰንሰለት ተይዘው ለሚጨነቁ ፣ በጩኸት ውስጥ ለተደበቁ ፣ ራሳቸውን ለጠሉ እርሱ አለሁ ይላል ። በቁም የደረቁ ዛፎችን ያለመልማል ። ምስጋና ለአዳኝነቱ ይሁን !!!
ተፈጸመ
ሰኔ 14 ቀን 2011 ዓ.ም.
ዲአመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ