የክርስቶስ ትንሣኤ ምስጋና ይገባዋል ። ውዱስ ፣ ቅዱስ መባል ያስፈልገዋል ። ታላላቅ ነገሥታት ቢነሡ ከድሀ ሰፈር ነው ፣ ክርስቶስ ግን ከሞት መንደር ተነሥቷል ። በቤተ ልሔም እጅግ ዝቅ ያለው ፣ በትንሣኤው እጅግ የገነነው አንዱ ክርስቶስ ነው ። ታላላቅ ሰዎች ከፍ ቢሉ በምክንያቶች ነው ፣ ክርስቶስ ግን በኃይሉ የተነሣ ነው ። ተነሥተው የነበሩ ኃያላን በመውደቃቸው መተረቻ ሁነዋል ፣ የክርስቶስ ትንሣኤ ግን ዳግም ድካምና ሞት የለበትምና ሲደነቅ ይኖራል ። ሌሎች ቢነሡ ለበቀል ፣ ለጥፋት ነው ፣ የክርስቶስ ትንሣኤ ግን ቅዱስ ነው ። ገንዘብ ላጡ ገንዘብ የሰጡ ቸር ተብለው ይመሰገናሉ ፣ ሕይወት ላጡ ሕይወት የሰጠ ክርስቶስ ሲመለክ ይኖራል ። ሁሉ ቢነሡ እርሱን ሥልጣንና በኵር አድርገው ነው ። እርሱ ግን በራሱ ሥልጣን ተነሥቷል ፣ በኵረ ትንሣኤ ሲባል ይኖራል ። ሳይንስ ፍልስፍና ገና ያላለቀ ነውና አይታመንም ፣ የክርስቶስ ትንሣኤ ግን የተፈጸመ ነውና ሊያምኑት ይገባል ።
ክርስቶስ ተነሣ ! ምእመን ሆይ ለበጎ ተግባር ተነሣ !