የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የጠዋት መስተዋት

 ወዳጄ ሆይ !

ምክር መልካም የምትሆነው ለሚተገብራት ነው ። ምክርና ፍቅር ያለ ቦታቸው ርካሽ ናቸው ። በነጻ በምክር ካልተማርህ በበትር በዋጋ ትማራለህ ። መልካም ምክር ለጊዜው መራራ ፣ ቆይቶ ጣፋጭ ናት ። ክፉ ምክር ደግሞ ለጊዜው ጣፋጭ ፣ ቆይቶ ግን መራራ ናት ። የመልካም ምክር ምሬት ለጊዜው ፣ ጥፍጥናው ግን ለሕይወት ዘመን ነው ። የክፉ ምክር ጣፋጭነትም ለአሁን ፣ ምሬቱ ግን ለዘላለም ነው ። መላእክትን አጋንንት ፣ አዳምንም አሮጌ ሰው ያደረገው ክፉ ምክር ናት ። የሰውን ነጻ ፈቃድ የምታከብር ምክር ናት ፤ ካልተቀበልሃት ትሄዳለች ። መልካም ምክር መድኃኒት እንጂ ማር አይደለችምና አትጣፍጥም ። መድኃኒት እየመረረ ያድናል ፣ መልካም ምክርም ለጆሮ እያሳከከ ይፈውሳል ። ምክር አራት ነገሮች አሏት፡- እነርሱም መካሪ ፣ ተመካሪ ፣ ምክሩና ውጤቱ ናቸው ። የሁሉንም ሰው ምክር የምትሰማ ከሆነ ብቻህን ትቀራለህ ። መልካም ምክርን የናቀ የሞተው ዛሬ ነውና አልቅስለት ። የአንዳንድ ሰዎች ሞታቸው ይቀድምና ቀብራቸው ይዘገያል ። ቀና ምክር ንጹሕ ልብ ካለውና መንፈስ ቅዱስ ከሞላበት ሰው ይገኛል ። ምክር ሞልቶ መፍሰስ ነውና መካሪዎች የእውቀት ፣ የዕድሜ ፣ የልምድ ፣ የመንፈሳዊ ተጋድሎ ሙላት በውስጣቸው አለ ። 

ወዳጄ ሆይ !

በትምህርት የምታውቀውን በኑሮ ስታውቀው ሌላ ነው ። ምክር የኑሮ ጭማቂ ናት ። አንደኛው ታምሞ ሌላው እንዳይታመም የሚጥርባት የደግነት መድረክ ናት ። አምጠው የሚመክሩ ጀማሪዎች ናቸውና ያስከፍላሉ ፣ ሰምተው የሚመክሩ ጎበዞች ናቸውና ይደነቃሉ ፣ ሞልተው የሚፈስሱ ግን ምክራቸውን ለተቀበለው ደመወዝ ይሰጣሉ ። መጥምቁ ዮሐንስ ጭው ባለ በረሃ ላይ የእግዚአብሔር ድምፅ እንደ ነበረ ፣ መካሪዎችም በዚህ ዓለሙና ሰዉ በረሃ በሆነበት ዘመን የመጽናናት ድምፅ ናቸው ። 

ምክር ሁሉ ዋጋ ይከፍላል ። ለሰሙት ደስታን ሲከፍል ፣ ያልሰሙትን ፀፀት ይከፍላል ። ስላልሄድክበት መንገድ ከሄዱት ሰዎች ጋር አትከራከር ። ምክር አለመስማት የሚመጣው አፍ ተከፍቶ ጆሮ ሲደፈን ነውና ። ከአዋቂች ፊት መቅደም ፣ ከአባቶች ፊት አስተማሪ መሆን ፣ በማመን በቀደሙን ፊት ስለ መንፈሳዊ ተጋድሎ ማውራት አለመመከርን ይወልዳል ። “ስጡ ይሰጣችኋል” ለገንዘብ ብቻ የተነገረ ሳይሆን ለእውቀትና ለምክርም ነውና መካሪ ስትሆን እውቀትህና ምክርህ ስስት አይኑረው ። ስትሰጥ ይሰጥሃልና ። 

ወዳጄ ሆይ !

 

መልካም መካሪዎች በዓለም ላይ ውድ ናቸው ። ከተገኙ ግን እግዚአብሔር በመልካም አስቦሃል ማለት ነው ። ምግብን አስደሳች የሚያደርገው ማቅረቢያው ንጹሕህና ያማረ ሲሆን ነው ። የጠራ ቋንቋና የከበረ የቃላት አጠቃቀም ለምክር እጅግ ወሳኝ ነው ። የንግግር ችሎታም በራሱ እውቀት ነውና አታናንቀው ። ሰው ምንም ቢማር መግለጫ ቋንቋና ርቱዕ አንደበት ከሌለው እውቀቱ የጋን ውስጥ መብራት ነው ። ብዙ መንገዶች ቢኖሩም የምትሄደው በሚያደርስህ መንገድ ነው ፣ ብዙ ምክሮች ቢኖሩም እውነት የሆነው ምክር ሊገዛህ ይገባል ። መልካም ምክርን በእውነትነቱ እንጂ በስሜትህ አታጣጥመው ። ከሰው ላለመለየት ብለህ የምታደርገው ተግባር ፣ የምትፈጽመው ግዳጅ ራስን የማጥፋት ሂደት ነው ። ምክር በነጻ ቢገኝም ውጤቱ ግን ውድ ነው ። ወደ ገደል የሚገባን ሰው ለማዳን ብትጮህ ክብሬን አጣሁ እንደማትል እየጠፋ ያለ ወገንን ለማትረፍ መቆጣትህ ራስህን ማዋረድ አይደለም ። ያንተ ቍጣ ብቻውን ሊለውጠው አይችልምና ጸጋ መንፈስ ቅዱስ እንዲረዳው ጸልይለት ። 

ወዳጄ ሆይ !

የአባት ምክር ማረሻ  ነው ፣ መንገድ ይከፍታል ። የእናት ምክር ቀንበር ነው ፣ ስለ ሌሎች መኖርን ያስተምራል ። የመንፈሳውያን አባቶች ምክር ስንቅ ነው ፣ በረሃውን ያሻግራል ። የሸንጋዮች ምክር ዘበት ነው ፣ መሳቂያ ያደርጋል ። የአድር ባዮች ምክር እንብላ እንብላ ነው ፣ ለውርደት ይዳርጋል ። የጨካኞች ምክር የቃየን ወንድም ነው ፣ እጅን በደም ይነክራል ። የፈሪ ምክር ሽብር ነው ፣ ከድል ያስቀራል ። የክፉ ሴት ምክር ረግረግ ነው ፣ ወጣሁ ሲሉ ይይዛል  ። ያልሰማኸው የአባትህ ምክር ስኬት ባጣህ ቀን ፣ የናቅኸው የእናትህ ምክር ሁሉም በር በተዘጋብህ ጊዜ ይታወስሃል ። የመንፈሳውያን አባቶች ምክር ዓለም በከፋብህ ጊዜ ከፊትህ ድቅን ይላል ። መከራ የተመከርከውን ያስታውሳል ።

የሰማይ አምላክ ቀኑን ይቀድስልህ !!!

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ጥቅምት 16 ቀን 2013  ዓ.ም.

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።