የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የጠፉ እሳቶች

“የጌታችንም ጸጋ በክርስቶስ ኢየሱስ ካሉ ከእምነትና ከፍቅር ጋር አብልጦ በዛ።” 1ጢሞ. 1፡14 ።
ሐዋርያው እስካሁን እየተናገረ ያለው እርሱን ክርስቲያንና አገልጋይ ስላደረገው ጸጋ ነው ። ኦሪታዊውን ወንጌላዊ ፣ ነፍሰ ገዳዩን ስምዐ ጽድቅ/የእውነት ምስክር/ ፣ ቤተ ክርስቲያን አፍራሹን ምእመናን ጠባቂ ስላደረገው ጸጋ በመገረም እየተናገረ ነው ። የሕግ አስተማሪዎች ሊሆኑ የሚወዱ ከጳውሎስ ይልቅ የሕግ አስተማሪ አይሆኑም ። ሐዋርያው ሕጋዊ መሆኑ ክርስቶስን እንዲገፋ ፣ ምእመናንን እንዲያሳድድ ፣ ቅዱስ እስጢፋኖስን እንዲገድል አደረገው ። በሕጋዊነት ውስጥ ጨዋነት ቢኖርም ፍቅር ግን የለም ፤ ቅንዓት ቢኖርም ሰላም ግን የለም ፤ እልህ ቢኖርም ማዳመጥ ግን የለም ፤ ሥርዓት ቢኖርም የልብ መማረክ የለም ። ሕጉማ መልካም ነው ። ለሚጠብቀው ሁሉ በረከትን ያመጣል ። ሰው ግን ሕጉን መጠበቅ ትቶ የሕግ አስተማሪ ሊሆን ሲወድ የእግዚአብሔርን ስጦታ ከማሰብ ለእግዚአብሔር የሚሰጠውን ማሰብ ይጀምራል ። “እነሆኝ የጌታ ባሪያ” ብሎ እንደ እመቤታችን ከመነሣት እንደ እገሌ ቀራጭና ኃጢአተኛ ስላልሆንሁ አመሰግንሃለሁ ይላል ። /ሉቃ. 1፡38 ፤ 18፡11/ ። የእግዚአብሔርን ጸጋ አሳንሶ ለእግዚአብሔር የሰጠውን አስበልጦ ያያል ። ሐዋርያው ግን ጠፍቶ ስለተገኘበት ፣ ሙቶ ሳለ ስለዳነበት ጸጋ ይናገራል ። ጸጋ እግዚአብሔርን የምናይበት መስተዋት ሲሆን ሕግ ግን ራሳችንን የምናይበት መጽሔት ነው ።ሐዋርያው ይህንን የመጀመሪያይቱን የጢሞቴዎስ መልእክት ሲጽፍ ወደ ክርስትና ከመጣ 22 ዓመት ገደማ ሁኖታል ። እንደ አሁን የሚያስበው ግን የመጠራቱን ነገር ነው ። እኛ እግዚአብሔርን ብንሆን ኑሮ ይህንን ማንነት አንጠራውም ነበር ።

ሐዋርያው በእግዚአብሔር ቤት የሚኖርበትን ምሥጢር ያልረሳ ሰው ነው ። የተጠራበት ፍቅር እንደሚያኖረው እየተናገረ ነው ። የሚዋደዱ ወዳጆች በመጀመሪያው ቀን ፍቅር ሁልጊዜ ካልተገኙ አብረው በደስታ ሊኖሩ አይችሉም ። የዛሬው ፍቅራቸውን የሚለኩበት የሙቀት መለኪያ የመጀመሪያው ቀን ፍቅር ነው ። ሐዋርያው የመጀመሪያው ጸጋ በሕይወቱ ሁሉ የሚመራበት ፍቅር መሆኑን ተረድቷል ። በቸርነቱ ጀምሮ በቸርነቱ ለመፈጸም ቆርጧል ። ሐዋርያው የሚያደንቀው ጸጋ እርሱን ክርስቲያን አድርጎ የተቀበለውን ቸርነት ነው ። የልብሱ ጨርቅ ሳይቀር ድዉይ እንዲፈውስ ያደረገውን የእግዚአብሔር ስጦታ ነው ። እርሱን እስከ መታሰርና መገረፍ ያጸናውን የእግዚአብሔር በረከት ነው ። ጸጋው ይጠራል ። ከጫካ ሕይወት አውጥቶ ከሰው ቊጥር ይደምራል ። ጸጋው አገልጋይ ያደርጋል ። ለራሱ ጠፍቶ የነበረው ወግ ደርሶት ሰው ፈላጊ ይሆናል ። ጸጋው በመከራ ውስጥ ትዕግሥትን ይሰጣል ። የተጠራበትን ጸጋ ስላልረሳ ለሌሎች የሚራራ ፣ ለሕይወቱን ሳይሳሳ የሚያገለግል ሆነ ። ለእግዚአብሔር ክብር መኖር ብቻ ሳይሆን መሞትም ፈለገ ። እንደ ፈቃዱ መኖር ብቻ ሳይሆን እንደ ፈቃዱ መሞትንም ተመኘ ። ይህን ሁሉ ፍቅር ፣ በረከትና ጥንካሬ የሰጠው ጸጋው ነው ።
ጸጋው ባለቤት አለው ። የጌታችን ጸጋ ይለዋል ። ጸጋው ለሰዎች ብቃት የተበረከተ ሳይሆን ጸጋው ኃጢአተኞችን በንስሐና በእምነት ያጸደቀ ነው ። ጸጋው የግል ገንዘብ ሳይሆን ጸጋው ባለ ጸጋ አለው ።
ጸጋው የእግዚአብሔር ሲሆን ከጳውሎስ የሚጠበቀው ግን እምነትና ፍቅር ነው ። ጸጋው ለኃጢአታችን የተከፈለው ዋጋ ነው ። እምነት ኃጢአትን አምኖ መናዘዝ መሢሑንም አምኖ መመስከር ነው ። ፍቅር ደግሞ ለእግዚአብሔር መኖር ነው ። ፍቅር ለሚወዱት መኖር ነው ። ጸጋው ሲነካው ለእግዚአብሔር ያለው እምነትና ፍቅር ጨመረ ። ሲያምን እግዚአብሔር እንደሚወደው አረጋገጠ ፤ ሲያፈቅር ደግሞ ለእገዚአብሔር ተቀደሰ ። ልብ አድርጉ የተቀደሰው ለሰው ሳይሆን ለእግዚአብሔር ነው ። የሚፈልጉትን እስኪያገኙ በሰው ፊት የሚቀደሱ ፣ ውጫዊ ማንነታቸውን የሚያጸዱ አሉ ።
ጸጋ የበዛላቸው አገልጋዮች አሉ ፣ ጸጋ የሚያስተላልፉ አባቶችም አሉ ። ጌታችን ግን ጸጋ የሚያሳተላልፍ ሳይሆን ራሱ ባለ ጸጋው ነው ። ፍጥረታት ዘንድ ያለ ጸጋ የተቀበሉት ሲሆን እርሱ ጋር ያለው ጸጋ ግን የባሕርዩ ነው ። በፍጥረታት ዘንድ ያለ ጸጋ ጉድለት ሲኖረው በእርሱ ዘንድ ያለው ጸጋ ግን ፍጹም ነው ። በፍጥረታት ዘንድ ያለው ጸጋ መጪና ሂያጅ ሲሆን የእርሱ ጸጋ ግን ከዘላለማዊ ህልውናው ፣ አካሉ ፣ ስሙና ባሕርዩ ጋር አብሮ የሚኖር ነው ። ጸጋው የሥላሴ መለኮታዊ ርስታቸው ነው ። የጌታችን ጸጋ ቢባልም የአብና የመንፈስ ቅዱስም ጸጋ ነው ። በአካላት ልዩ ቢሆኑም በሀብታት ግን አንድ ናቸው ። በስም ልዩ ቢሆኑም በመስጠት ግን አንድ ናቸው ።
ሰማይና ምድር በውስጣቸው ያሉ ሁሉ ሀብትነታቸው የሥላሴ ፣ ጸጋነታቸው ለእኛ ነው ። ከተሸከምነው አካል የእኔ ብለን የምንኮራበት ምንም ነገር የለምና እርሱም ጸጋ ነው ። ጸጋ እኛን የሚያሳቅቅ ሳይሆን እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር የምንረዳበት ነው ። እግዚአብሔር አምላክ በዚህ ዓለም ላይ ስንገኝ ራሳችንን የምንረዳበት ጸጋ ሰጥቶናል ። ይህንንም ክህሎት እያልን የምንጠራው ነው ። በተፈጥሮ አማካይነት የተቀበልነው ስጦታ ነው ። ሙያ ብለን የምንጠራቸው ነገሮች ሁሉ የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው ። እንጨት መጥረብም ፣ ወርቅ ማንጠርም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው ። የእግዚአብሔር ስጦታ ነውና አክብረን ልንይዘው ፤ በሰዎች ላይ ስናየውም ልናከብርላቸው ይገባል ። ቃሉ እንዲህ ይላል፡- እይ ከይሁዳ ነገድ የሚሆን የሆር የልጅ ልጅ ፥ የኡሪ ልጅ ባስልኤልን በስሙ ጠርቼዋለሁ ። በሥራ ሁሉ ብልሃት በጥበብም በማስተዋልም በእውቀትም የእግዚአብሔርን መንፈስ ሞላሁበት የጥበብን ሥራ ያስተውል ዘንድ፥ በወርቅና በብር በናስም ይሠራ ዘንድ ፥ ለፈርጥ የሚሆነውን የዕንቍ ድንጋይ ይቀርጽ ዘንድ ፥ እንጨቱንም ይጠርብ ዘንድ፥ ሥራውንም ሁሉ ይሠራ ዘንድ ።” ዘጸ. 31፡2-5 ። ብዙ ጊዜ መንፈሳዊ ጸጋ ያላቸው የእጅ ጥበብ ያላቸውን አያከብሩም ፣ የእጅ ጥበብ ያላቸውም መንፈሳዊ ጸጋ ያላቸውን አያከብሩም ። የእጅ ጥበብ ምድርን ሲያበጅ ፣ የሰውን ልጅ ኑሮ ሲያቀል ፤ መንፈሳዊ ጸጋ ደግሞ ሕይወትን ያንጻል ። ለዘላለማዊ ሕይወት ያበቃል ። የሰው ልጅ ከመላእክትና ከሌሎች ፍጥረታት ልዩ የሚያደርገው የሁለት ዓለም ወራሽ መሆኑ ነው ። እንስሳት የዚህ ዓለም ብቻ ወራሾች ፣ መላእክት የሰማይ ዓለም ወራሾች ናቸው ። ሰው ግን የምድርና የሰማይ ወራሽ ነው ። ይህንን ዓለም ለመውረስ የእጅ ጥበብ ፣ ሰማይን ለመውረስ መንፈሳዊ ጸጋ ያስፈልገዋል ። እንጀራንና ቃሉን የሰጠ እግዚአብሔር ሥጋዊና መንፈሳዊ ጸጋንም ሰጥቷል ። ሥጋዊ ጥበብ በተፈጥሮ ስንቀበል ፣ መንፈሳዊ ጸጋ ግን ከእግዚአብሔር በመወለድ የምንቀበለው ነው ። እንጨት መጥረብም ፣ ወርቅ ማንጠርም ፣ የሚታዩ ውብ ነገሮችን መሥራትም የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ነው ብሎ ለማሰብ ሰው ቢቸገርም የእርሱ ስጦታ ናቸው ።

ጸጋው በክረስትና በሦስት መንገድ ይገለጣል፡-

1-  የሚያድን ጸጋ ፤ ይህ ክርስቲያን የተባልንበት ፣ ውሉደ እግዚአብሔር ተብለን ወራሽ የሆንበት ስጦታ ነው ። /ኤፌ. 2፡8/።
2-  የሚቀድስ ጸጋ ፤ ይህ ለእግዚአብሔር እንድንኖር የሚያደርገን ፣ ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል የተባለበት ፣ ዕለት ዕለት ሥጋና ዓለምን የምንክድበት የመንፈሱ ሙላት ነው ። /ሮሜ. 1፡17/ ።
3-  የሚረዳ ጸጋ ፤ በመከራና በፈተና ሰዓት በድል አድራጊነት ለመሻገር የሚያግዝ ፣ ተራራን የሚደለድል ኃይል ነው ። /ዕብ. 4፡16/።
ሐዋርያው ከጸጋው የተነሣ ወይም ከእግዚአብሔር ስጦታ የተነሣ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለው እምነትና ፍቅር እየጨመረ መምጣቱን ይገልጻል ።እምነት በተባረደበት ፣ ፍቅር በቀዘቀዘበት ዘመን ሐዋርያውን ማሰብ ይገባናል ። እምነታችሁ ተዳክሞ ፣ ፍቅራችሁ ቀዝቅዞ ከሆነ አሁን ተስፋ አድርጉ፤ የተስፋ እሳት የጠፉትን ሁለቱን ሻማዎች ይለኩሳል ። እነርሱም እምነትና ፍቅር ናቸው ።
ጌታ ሆይ የእኛንም እምነትና ፍቅር እባክህን ጨምረው ።
1ጢሞቴዎስ /16/
ኅዳር 24 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.

ያጋሩ

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።