የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የጥብርያዶስ ዳርቻ

የገሊላ ባሕር ፊት ለፊቴ ይታየኛል። ከጥቁር ከሰማያዊ ቀምሞ የሠራው፣ ብዙ ታሪክ ያዘለ ያ ስመ ብዙ ጥብርያዶስ ይናገረኛል። አንድ ለእናቱ የሆነው የጌንሴሬጥ ባሕር ተንጣሎ የዘመን ሰሌዳነቱን ይገልጥልኛል። ብሉይና አዲስ በውስጡ አሉ። ጴጥሮስና እንድርያስ፣ ዮሐንስና ያዕቆብን ዛሬም ያስታውሳቸዋል። የበረከቱን ጌታ፣ የሁልጊዜ ፈላጊውን ወዳጅ ኢየሱስን ያስተነትነዋል። ፍለጋ አያልቅም ይለኛል ጥብርያዶስ። ጌታ ከዓሣ አጥማጅነት ደቀ መዛሙርቱን ፈለገ። እርሱ ሞቶ የቀረ፣ ጠላት አሸንፎ የገነነ የመሰላቸው ደቀ መዛሙርትን እንደገና በጥብርያዶስ ፈለገ። የእንደገናውን አምላክ ጥብርያዶስ ያስታውሰዋል /ዮሐ. 21/። በእንደገና ዕድል የሚኖሩ ብዙ ሺዎችን ጥብርያዶስ ይሰብካል። ተስፋ ቆርጠው እንደሆነ ጌታ አይጥልም ተመለሱ ይላል። ከስብከት በሚበልጠው ስብከት በህልውናው ይተርካል። በብዙ ውለታ ላይ ተኝተው እንደሆነ ጥብርያዶስ ለምስጋና ይቀሰቅሳል። እስራኤል ነጻ መንግሥትነቷን ስታውጅ አሜሪካ ከሁሉ ቀድማ እውቅና እንደ ሰጠች እርሷን ተከትለው ብዙዎች እውቅና እንደ ሰጡ ጌታም ምሕረት ሲያደርግ ከኅሊና በፊት እውቅና የሚሰጠን ያው የማረን ምሕረት ነው። ስለተቀበለው ብዙ ይቅርታ፣ የማይሰፈር ምሕረት የሚዘምር በጣም ጥቂት ነው። ጥብርያዶስ ግን ዘምሩ፣ ከኅሊና ከሰዎች በፊት ራሱ ምሮ ራሱ እውቅና ስለሰጣችሁ፣ ክዳችሁት ሳለ ላልካዳችሁ፣ በጨለማ ቀን ላልጨለመባችሁ ጌታ ተቀኙ ይላል። ወይ ጥብርያዶስ ብዙ ይናገራል፣ ብዙ ያናግራል። ተናጋሪ አናጋሪ እንዲሉ። ጥብርያዶስስ ቢያናግሩት የሚያድሰውን የጌታን ምሕረት ተናግሮ ያናግራል።
ገብተን የማናልቀውን የሚፈልገውን ጌታ ጥብርያዶስ በዝምታ ያደንቀዋል። አሁንም በዳርቻው ላይ ያሉቱን ቤቶች አሻግሬ በቀስታ አየሁት፣ ተናገር ጥብርያዶስ አልኩት። ማዶ ዮርዳኖስን ጠቀሰልኝ። ዮሐንስ የንስሐ ጥምቀት ሲያጠምቅ መልኩን አሳየኝ። ንስሐ የሌለበት ጌታ ጥምቀቱ ድረስ መጣ። ዮሐንስ የእግዚአብሔርን ምሕረት ተጨባጭ ለማድረግ ፣ ምሕረትን ለመቀበል ቀጠሮ ለሚፈልገው ለሰው ባሕርይ አስረጂ እንዲሆን በውሃ ያጠምቃል። ኃጢአታችሁ እንዲሁ ውልቅ ብሎላችሁ ይሄዳል። ቆሻሻ በአካላችሁ ላይ ያለ ነው። የባሕርያችሁ አይደለም። ኃጢአትም ባሕርያችሁ አይደለም። ባሕርያችሁ በኃጢአት ወደቀ እንጂ ኃጢአት ባሕርያችሁ አይደለም። በንስሐ ሙልጭ ብሎ ይወገዳል ለማለት በውሃ ያጠምቅ ነበር። ብዙ ኃጢአተኞችም ለመጠመቅ ለመናዘዝ ወደ እርሱ ይመጡ ነበር። የዚያን ጊዜ ኃጢአተኞች በአደባባይ ሲናዘዙ አያፍሩም ነበር። ሰሚም የለ፣ ሁሉም ተናዛዥ ነበር። በረጅሙ የኃጢአተኞች ሰልፍ አንድ ኃጢአት የሌለበት ንጹሕ ተሰልፏል። ልቅደም አላለም። ተራ እስኪደርሰው በጽሞና ይጠብቃል። ፀሐይ በቆሻሻ ቦታ ብትወጣ እንደማትቆሽሽ በእኛ መካከል በመቆሙ የክርስቶስ ቅድስና አይጎድፍም። ዮሐንስ ባየው ጊዜ ደነገጠ። የዮሐንስ አገልግሎት ኢየሱስን ይገልጠዋል እንጂ አይጠቅመውም። ንስሐ የሌለበት ቅዱስ ነውና።
ጥብርያዶስ ብዙ ያጫውታል። ፀሐዩ አዘቅዝቆ ምሽቱ እየመጣ ነው። በማታ ባይታይም ያሳያል። ሳይታይ የሚያሳይ እንዴት ደስ ይላል። ደቀ መዛሙርቱ በማዕበል ሲጨነቁ የነበረበትን ያን ሌሊት አሳታወሰኝ። ከሌሊቱ አራተኛው ክፍል ነበር። አራተኛው ክፍል የመጨረሻው ክፋይ ሲሆን ከዘጠኝ ሰዓት እስከ ንጋት ያለው ጊዜ ነው። በዚያ ጊዜ በማዕበል ሲጨነቁ ጌታ ደረሰላቸው። እኛም በመጨረሻው የሌሊቱ ክፍለ ጊዜ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ነን። በማዕበል ብንጨነቅም ጌታ ይደርስልናል።
 ጥብርያዶስ የጴጥሮስን አደራ ያስታውሳል /ዮሐ. 21፡15/። ጴጥሮስ ትወደኛለህን? ሲለው እንደ ቀድሞው በራሱ አልፎከረም። እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ጥያቄው ተራ ፍቅርን የሚመለከት አይደለም። “ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን?” የሚል ነው። ከምትወዳቸው ይልቅ ትወደኛለህን? ማለቱ ነው። ጥያቄው ከባድ ነው። የምንወዳቸውን ያህል ኢየሱስ ክርስቶስን መውደድ ቀላል ነው። ከምንወዳቸው በላይ እርሱን መውደድ ግን ከባድ ነው። ቢሆንም ጴጥሮስ አደራ ተሰጠው። ሕጻናትን፣ ወጣቶችና ሽማግሌዎችን በአደራ ተቀበለ። በጌታ ፍቅር ካልሆነ እረኝነት ከባድ ነው። የሚያስችለን ፍቅሩ ብቻ ነው።
 ጥብርያዶስ እባክህ ተወኝ። ለእውነት የመደብነው ጊዜ በጣም ጥቂት ነው። ለጨዋታና ለፌዝ ሰፊ ሰዓት መድበናል። ላንደማመጥ እንጯጯሃለን። ስለዚህ መሄድ ፈልጌአለሁ፣ ደግሞም እራቴን አስባለሁ። ከታጠፈ አይዘረጋም የሰው ገበታ። ጥብርያዶስ በዝምታው የዘመናትን መልክ ያሳያል። ሥዕል የዝምታ ነጋሪት አይደል! የእግዜሩ ሥዕል፣ የሠራው ክርስቶስ የተራመደበት ጥብርያዶስ ብዙ ይናገራል። ጥብርያዶስን በጀልባ እረግጠዋለሁ፣ ጌታዬ ግን በእግሩ ይረግጠዋል። የስበት ሕግ እርሱን አይዘውም። የማልችለውን ኢየሱስ ክርስቶስ ይችላል።
“ድል ለነሣው” የሚለውን ርእስ በጥብርያዶስ ዳርቻ ለመጻፍ ስሰናዳ ጥብርያዶስ እያወራ አስቸገረኝ። ንግግሩ መልካም፣ ልብን የሚያጸና ሆኖ ተደሰትኩኝ። “ድል ለነሣው” ምን ተዘጋጅቶ ይሆን? 
ይቀጥላል

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።