የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የጸሎት ግብ

“ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው።” 1ጢሞ. 2፡3-4 ።
ሐዋርያው ስለ ሰው ሁሉ ጸልዩ ብሎ ነበር ። ጸሎትን ክቡርና ሥሙር የሚያደርገው ስለ ሌሎች መማለድ ካለበት ነው ። ምልጃ የእግዚአብሔር ፍቅር ሲነካን የምናደርገው ልመና ነው ። ስለ ሌሎች ለመጸለይ ፍቅር ያስፈልጋል ። ምልጃ የእግዚአብሔርን ክብር መጋፋት አይደለም ። ምልጃ በሰው ልጆች መካከል መተሳሰብን ፣ በሰማይና በምድር ባሉት ዘንድ መተሳሰርን የሚያሳይ ልዩ መንገድ ነው ። የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚያጸናም የሚያጎላም ምልጃ ነው ። ሐዋርያው ስለ ሰው ሁሉ እንዲጸለይ ይመክራል ። በዚህም ሦስት ነገሮች እንረዳለን፡-
1-  ሰው ሁሉ በችግር ውስጥ እንደሚያልፍ ፣
2-  የማንጸልይለት ሰው እንደሚያውከን ፣
3-  በጸሎት አድልኦ እንደሌለ እንገነዘባለን ።

ስለ ነገሥታትና ስለሚያስተዳድሩ ሰዎች አብዝቶ መጸለይ ይገባል ። ስለ ቤተ ክርስቲያን አባቶችም ጸሎት መደረግ ግድ ያስፈልጋል ። ስለ ሌሎች ስንጸልይ አብዝተን እየተቀበልን ነው ። ስለ ሌሎች መጸለይ መክሰር ሳይሆን በእጥፍ ማትረፍ ነው ። ስለ ሌሎች ስንጸልይ ልባችን በፍቅር ይሞላል ። ደግሞም ከመፍረድ ይድናል ። ሐዋርያው ይህን መልእክት በሚጽፍበት ጊዜ አብዛኛውን የዓለም ክፍል ይገዛ የነበረው ኔሮ ቴሣር ነው ። ኔሮ ቄሣር ከ54-64 ዓ.ም. ለአሥር ዓመታት ያህል በክርስቲያኖች ላይ ጥላቻ አልነበረውም ።ቤተ ክርስቲያን ትፈተን የነበረው በአረማውያንና በአይሁድ ነበረ ። የጢሞቴዎስ መልእክት ከተጻፈ ቢያንስ ከሁለት ዓመት በኋላ ኔሮ ታላቅ መከራ በክርስቲያኖች ላይ አመጣ ። የሮምን ከተማ የሚበዛውን ክፍል በእሳት አጋይቶ ይህን ያደረጉ ክርስቲያኖች ናቸውና ማንም ሰው ነጻ እርምጃ ሊወስድባቸው ይችላል አለ ። በኔሮ ቄሣር የጀመረው የመከራ ዘመን በ313 ዓ.ም. ታላቁ ቆስጠንጢኖስ ተነሥቶ የእምነት ነጻነት እስኪያውጅ ዕረፍት አልነበረውም ። ይህም ከ64-313 ዓ.ም. ማለት ነው ። ቤተ ክርስቲያን ለሦስት መቶ ዓመታት በሮማ ቄሣሮች ታላላቅ መከራዎችን ተቀብላለች ። ኑሮዋንም በዋሻና በምእመናን ቤት ውስጥ አድርጋለች ። ሐዋርያው ከሁሉ በፊት ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንት ጸልዩ ሲል ይህ ታይቶት ሳይሆን አይቀርም ።
ሐዋርያው ያዕቆብ፡- አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም” ይላል ። /ያዕ. 4፡2።/ አንዳንድ መከራዎች ያለ መጸለይ ውጤት ናቸው ። ጸሎት ቅጥር ነውና ሊጠብቅ ይገባዋል ። ቅጥሩ ከላላ ሕይወታችን ሊደፈር ይችላል ። ዛሬም ስለሚያስተዳድሩት ሰዎች ስለማንጸልይ በዚያ ፈንታ ስድብና እርግማን ስለምናወርድ ሳንግባባ እንኖራለን ። የበላዩ ለበታች እንዲያዝን ፣ የበታች ለበላይ እንዲገዛ ጸሎት በጣም ያስፈልጋል ።
ስለ ሰው ሁሉ ይልቁንም ስለ ነገሥታትና መኳንንት መጸለይ ያስፈለገበት ምክንያትና ግቡ ምንድነው ? ብለን መጠየቃችን አይቀርም ። ሐዋርያው፡- “ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው ።” ይላል ። 1ጢሞ. 2፡3-4 ።
የምንጸልይበት ምክንያቱም በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ስለሆነ ነው ። ግቡ ደግሞ ሰው ሁሉ እንዲድንና እውነትን ወደ ማወቅ እንዲደርስ ነው ። ስለ ሰዎች ልንጸልይ እንችላለን ። የምንጸልየው ግን ስለ ምድራዊ ጉድለታቸው ብቻ ነው ። በዋናነት እንዲድኑ መጸለይ ይገባል ። የዚህ ዓለም ማግኘቱም ማጣቱም ፣ መታመሙም ፈውሱም ያልፋል ። የማያልፈው የዘላለም ሕይወት ነው ። ልብ አድርጉ እንዲድኑ እንጸልያለን ፣ እውነቱን እንዲያውቁ እናስተምራለን ። ይህ ብቻ አይደለም እውነቱን እንዲያውቁ ከማስተማራችን በፊት ልንጸልይላቸው ይገባል ። ምክንያቱም ልባቸውን የሚያዘጋጅ የእግዚአብሔር መንፈስ ነው ። ገበሬ መሬቱን አለስልሶ እንዲዘራ ጸሎትም የሰውን ልብ ማለስለሻ ነው ። ቃሉ ደግሞ ዘር ነው ። በጠፍ መሬት ላይ እየዘራን አልበቀለም ብለን እናዝናለን ።
ሰዎች ሁሉ እንዲድኑ እግዚአብሔር ይፈልጋል ። ክርስቶስ የመጣው አንዱን አዳምን ፍለጋ ነው ። ስለዚህ የአዳም ልጅ ያልሆነ የለምና ሁሉን አድራሻ አድርጎ መጥቷል ። ክርስቶስ የሞተው ለዓለም ሁሉ ነው ። በሙሉነት ለእነ እገሌ በከፊል ለእነ እገሌ ሞተ የሚል የለም ። ይህ ከሆነ ሁለት ነገሮችን መገንዘብ ያስፈልገናል ።
1-  ክርስቶስ ለሞተለት ወገን እኛ ለመጸለይ ልንደክም አይገባም ።
2-  ሰው ሁሉ እንዲድንና እውነቱን እንዲያውቅ እግዚአብሔር ይወዳልና የተመረጡና ያልተመረጡ አሉ ብለን መናገር ተገቢ አይደለም ።
ነገሥታትን የረሳናቸው በጸሎት ብቻ አይደለም ፤ በምስክርነትም ረስተናቸዋል ። በዚህ ምክንያት የሚበዙት የዓለም መሪዎች ከሀዲዎች ናቸው ። የሃይማኖት አባቶችም ቤተ መንግሥት ተጠርተው ፣ መድረክ ተሰጥቷቸው የሚናገሩት ዘላለማዊውን ነገር አይደለም ። ሰይፍ ሳይመጣ እንዲህ ዝም ካልን የመጣ ቀን ምን ልንሆን ነው ?
እውነትን ማወቅ የሰው ልጅ ሥነ ልቡናዊና መንፈሳዊ መብቱ ነው ። ጋዜጠኞች ራሳቸውን የሕዝብ ዓይንና ጆሮ አድርገው ይቆጥራሉ ። ሕዝብ መረጃ የማግኘት መብት አለው ይላሉ ። ድምፅ አልባ ለሆኑትም ድምፅ እንሆናለን በማለት ለፍትሕ ይጮኻሉ ። እግዚአብሔርም ሰዎች እውነቱን እንዲያውቁ ይፈልጋል ። እውነት በትምህርት ቤት ፣ እውነት በፍርድ ቤት ስትፈለግ ትውላለች ። እግዚአብሔር እንድናውቀው የወደደው እውነት ግን የዘላለም ሕይወት የሚገኝበትን እውነት ነው ። እርሱም ራሱ እግዚአብሔር ነው ። እውነት ብርሃን ነው ፣ እግዚአብሔርም ብርሃን ነው ። እውነት ነጻ ያወጣል ፣ እግዚአብሔርም ነጻነትን ይሰጣል ። እውነት ያሳርፋል ፣ እግዚአብሔርም ዕረፍት ይሰጣል ።
በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኙ ነገሮች አሉ ። እነርሱም፡-

1-  ሌሎች እንዲድኑ መጸለይ ፣
2-  እውነቱን እንዲያውቁ ማስተማር ናቸው ።
እግዚአብሔር እንደ ቃሉ የሆነ ትጋት ይስጠን !!
1ጢሞቴዎስ /24/
ታኅሣሥ 16 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ