የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የጸና ግንብ

 “የእግዚአብሔር ስም የጸና ግምብ ነው ጻድቅ ወደ እርሱ ሮጦ ከፍ ከፍ ይላል።” ምሳሌ 18፡10
በህልውና የተገኘ ነገር ሁሉ ስም አለው ። እያንዳንዱ የሰው ልጅም ከሌላው ተለይቶ የሚታወቅበት የመጠሪያ ስም አለው ። ስም የህልውና መግለጫ ፣ ስም የአካል መታወቂያ ፣ ስም የግብር ማሳያ ነው ። የተጸውዖ ፣ የመዐርግ ፣ የሙያ ፣ የመንፈሳዊ ደረጃ መግለጫ የሆኑ ስሞች አሉ ። እነዚህ ሁሉ ስሞች ግን ከጊዜ በኋላ የተሰየሙና በጊዜ ውስጥም የሚያበቁ ይሆናሉ ። መነሻና መድረሻ የሌለው ዘላለማዊ ስም ያለው እግዚአብሔር ብቻ ነው ። በዚህ ዓለም ላይ ያሉት ስሞች ከመለያነት ባሻገር የማማጸን አቅማቸው ዝቅተኛ ነው ። ስምም ከስም አይበልጥም ። የእግዚአብሔር ስም ግን የሚያስጠጋ ስም ነው ። ከስሞች ሁሉ በላይ የሆነው ስምም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው ። ፊልጵ. 2፡9-10 ።
በዚህ ዓለም ላይ ብዙ ግንቦች አሉ ። አንዳንድ ግምቦች ከጊዜ ብዛት የተነሣ በእርጅና ምክንያት ሰው ላይ በመውደቅ አደጋ ያደርሳሉ ። የሰሊሆም ግንብ ተደርምሶ አሥራ ስምንት ሰዎች እንደ ሞቱ ጌታችን አስታውሷል ። ሉቃ. 13፡4 ። አንድ ግንብ ግን የማይፈርስ ነው ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ስም ነው ። ግንብ መሠረቱ የጸና ወደ ላይ ከፍ ያለ ነው ። ሰውና አራዊት የሚያሳድዳቸው ሰዎች ሮጠው ፣ ሮጠው ግንቡ ላይ ከወጡ ጠላታቸው ታች ሁኖ ይጮኻል እንጂ አያገኛቸውም ። እነርሱም በሩጫ የምትመታውን ልባቸውን ማስተካከል ፣ ትንፋሻቸውን ማደስ ይጀምራሉ እንጂ ከሥር ሁኖ የሚጮኸው ጠላት አያሰጋቸውም ። የእግዚአብሔር ስም ሮጠን ከፍ የምንልበት የጸና ግንብ ነው ። የምንሮጠውም በጸሎት ነው ። የምንሮጠውም ቃሉን በማሰስ ነው ። የምንሮጠውም ስሙን በመጥራት ነው ።
ጠቢቡ ሰሎሞን ይህን ሲገልጥ አባቱ ዳዊት የነገረውን በማስታወስ ይመስላል ። ዳዊት ከንጉሥ ሳኦል እስከ ልጁ አቤሴሎም ሁሉም ያሳደደው ፣ አማካሪዎችና ካህናት ያደሙበት ሰው ነው ። የንጉሥ ጠላት ፣ የልጅ ባላጋራ ፣ የአማካሪ አሳዳሚ ፣ የካህን አዋራጅ ሊሸከሙት የሚከብድ የመከራ ቋጥኝ ነው ። ዳዊት ሮጦ ሮጦ ከፍ ያለው በጸናው በእግዚአብሔር ስም ነው ።
በዚህ ክፍል ላይ ይሮጣል የተባለው ጻድቅ ነው ። ጻድቅ መሆን ማለት ከዓለም መገፋት ፣ በወዳጅና በልጅ ሳይቀር መከዳት ነው ። መገፋት የለም አልተባለም ፣ የሚያስጠጋ ግን አለ ። መሰደድ የለም አልተባለም ፣ የሚያስጠልል ግን አለ ። መታመም የለም አልተባለም ፣ የሚፈውስ ግን አለ ። መሮጥ የለም አልተባለም ፣ ከፍ የሚያደርግ ግን አለ ። መሮጥ ለውድድር ካልሆነ ክብር ላለው ሰው ብዙም አያሳርፍም ። የሚያሯሩጡ ቀኖች ግን አሉ ። በዚህ ሰዓት ወደ ዘመድ ፣ ወደ ባለሥልጣን ፣ ተስፋ ወደ ሰጡን ሰዎች ከመሮጥ ወደ እግዚአብሔር ስም መሮጥ ዋጋ አለው ። የእግዚአብሔር ስም የጸና ግንብ ነው ። የተሳፈሩበትንም ከፍ ያደርጋል ። አባራሪውና ተባራሪው ቅድም በምድር ላይ እኩል ነበሩ ። ተባራሪው ግን ግንቡ ላይ ሲወጣ አባራሪው ታች ፣ ተባራሪው ከላይ ሆኑ ። አባራሪው ግንቡን መምታቱ አይቀርም ። ግንቡ ካልጸና ይፈርስና ተባራሪው ተጨፍልቆ ይሞታል ። የጸና ግንብ ከሆነ ግን አባራሪው ጠላት አፍሮ ይቀራል ። የእግዚአብሔር ስም የጸና ግንብ ነው ። ኅሊና ፣ ሰዎችና ሰይጣን ሲያባርሩን ወደዚህ ስም እንሩጥ ። ውጤቱ ከፍ ማለት ነው ።
“ያንተን ስም ሰምቶ ሞት ይደንግጥ ፤ ቀላያትም ይሰንጠቁ ጠላትም ይረገጥ ። የጥፋት መንፈስም ይንቀጥቀጥ፤ ከይሲም ይወገድ፤ አለማመንም ይራቅ ። ወንጀለኛ ይቸገር ቊጣ ጸጥ ይበል ፤ ቅናት ጥቅም አያግኝ ፤ ኃጢአትን የሚያዘወትር ይገሠጽ ። ወርቅን የሚወዱ ይነቀሉ ፤ ድካም ይወገድ ፤ ሐሰተኛ ይጣል፤ መርዝ ያላቸው የፍጥረት ወገን ሁሉ ይበተን።” /ቅዳሴ እግዚእ – የጌታ ቅዳሴ ቊ. 53 ።
ከሰማያት በላይ ከፍ ያልከው ፣ አሳብህም ከውቅያኖስ ይልቅ የጠለቀው ፣ ብልሃትህ የማይደረስበት ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ አመሰግንሃለሁ ። እያንዳንዱ ቀን የራሱ የሆነ አባራሪ አለው ። የተለያዩ አባራሪዎች አሉ ፣ እኔ ግን ያው እኔ ነኝ ። እባክህን በመስቀልህ ማማ ላይ አሳፍረኝ ። ጠላቴን ከታች ሳየው እርሱ ወደ እኔ በማንጋጠጥ ይድከም ። ወደ ጸና ስምም ልጠጋና ቁርጥ ፣ ቁርጥ የምትለው እስትንፋሴ እንደገና መጓዝ ትጀምር ። የሚመታው ልቤ ፣ በፍርሃት የሚርደው ማንነቴ ይጠንክር ። ኃይሌን ብታመን ወደ አንተ አልመጣም ። ምንም የለኝምና እግዚአብሔር ሆይ አስጠጋኝ ። ለዘላለሙ አሜን ።
የዕለት መና /ክፍል 1/
ተጻፈ አዲስ አበባ
ዲአመ ሚያዝያ 30 ቀን 2011 ዓ.ም.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ