ቤተ ጳውሎስ፤ ሐሙስ፣ መስከረም 3 2005 ዓ.ም.
‹‹ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ፣
ወይጸግቡ ጠላተ ገዳም፣
ወይረውዩ አድባረ በድው፡፡ ›› –
‹‹በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፣
ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል፣
የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ፡፡››
(መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ 64፡11-12)
ዘመኑ የተቀየረው፤ ማክሰኞ፣ መስከረም 1 ቀን 7505 ዓመተ ዓለም፣
2005 ዓመተ ሥጋዌ፣ 2013 ዓመተ ምሕረት፣
1729 ዓመተ ሰማዕታት፣1 ዓመተ ወንጌላዊ – ዘመነ ማቴዎስ
September 11, 2012 AD (Anno Domini)/ Year of Our Lord
በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መስከረም 1 ቀን ቅዱስ ዮሐንስ፣ የዘመን ነገርና ተዘዋዋሪዎቹ አጽዋማትና በዓላት በዓመቱ ውስጥ የሚውሉባቸው ዕለታት ተለይተው የሚታወጁበት ነው፡፡ አዋጁ የሚታወጀውና የአወጣጡ መንገድም የሚገለጸው ዕለቱ ጾም ካልሆነ ከቅዳሴ በኋላ፣ ጾም ከሆነ ከቅዳሴ በፊት ይሆናል፡፡ የባሕረ ሐሳቡ መምህር ሥነ ፍጥረቱንና የአጽዋማትና በዓላቱን አወጣጥ ሲተርኩ መስማት እጅግ ደስ ያሰኛል፡፡ በዓላትና አጽዋማት ሲወጡም አሥርቆት ይደረጋል፡፡ አሥርቆት ማለት የሌሊትና የመዓልት መባቻ የሚታወቅበት መንገድ ነው፡፡ የአጽዋማትና የበዓላቱን አወጣጥ በዝርዝር እንመልከት፡፡
የ2005 አጽዋማትና በዓላት የሚውሉባቸው ዕለታት
ጾመ ነነዌ የካቲት 18 ቀን፣ ሰኞ
ዐቢይ ጾም መጋቢት 2 ቀን፣ ሰኞ
ደብረዘይት መጋቢት 29 ቀን፣ እሑድ
ሆሣዕና ሚያዝያ 20 ቀን፣ እሑድ
ስቅለት ሚያዝያ 25 ቀን፣ ዓርብ
ትንሣኤ ሚያዝያ 27 ቀን፣ እሑድ
ረክበ ካህናት ግንቦት 21 ቀን፣ ረቡዕ
ዕርገት ሰኔ 6 ቀን፣ ሐሙስ
ጰራቅሊጦስ ሰኔ 16 ቀን፣ እሑድ
ጾመ ሐዋርያት 17 ቀን፣ ሰኞ
ጾመ ድኅነት ሰኔ 19 ቀን፣ ረቡዕ
እነዚህ አጽዋማትና በዓላት እንዴት ተገኙ?
አጽዋማቱና በዓላቱ የተገኙት በመደበኛው የፀሐይ አቆጣጠር ብቻ ሳይሆን በሁለቱ ብርሃኖች ፀሐይና ጨረቃ ጥምር አቆጣጠር ነው፡፡ በፀሐይ ዓመት 365 ቀንና በጨረቃ ዓመት 354 ቀን መካከል ያለው የየዓመቱ የ11 ቀናት ልዩነት ለበዓላቱ ማግኛ የሚረዳ በመሆኑ አበቅቴ ይባላል፡፡ ተረፈ ዓመት ማለት ነው፡፡
አበቅቴ በየ19 ዓመቱ የሚመላለስ ዐውድ አለው፡፡ ይህም ዐውደ አበቅቴ ይባላል፡፡ ከአበቅቴ ጋር ተዘምዶ ያለው መጥቅዕ ነው፡፡የጨረቃ ዓመት በነሐሴ ወይም በጳጉሜን ይጀምርና በመስከረም ወይም በጥቅምት 30ኛ ቀኗን የምታከብርበት ዕለት መጥቅዕ ይባላል፡፡ መጥቅዕ ደወል ማለት ሲሆን የአይሁድን አዲስ ዓመት ያመለክታል፡፡ ከመስከረም 15 እስከ ጥቅምት 13 ቀን ድረስ ባሉት 29 ቀኖች መካከል ይውላል፡፡
አበቅቴ በየ19 ዓመቱ የሚመላለስ ዐውድ አለው፡፡ ይህም ዐውደ አበቅቴ ይባላል፡፡ ከአበቅቴ ጋር ተዘምዶ ያለው መጥቅዕ ነው፡፡የጨረቃ ዓመት በነሐሴ ወይም በጳጉሜን ይጀምርና በመስከረም ወይም በጥቅምት 30ኛ ቀኗን የምታከብርበት ዕለት መጥቅዕ ይባላል፡፡ መጥቅዕ ደወል ማለት ሲሆን የአይሁድን አዲስ ዓመት ያመለክታል፡፡ ከመስከረም 15 እስከ ጥቅምት 13 ቀን ድረስ ባሉት 29 ቀኖች መካከል ይውላል፡፡
መጥቅዕ ከመስከረም 15 እስከ መስከረም 30 ሲውል ነነዌ በጥር ይውላል፡፡ ከጥቅምት 2 እስከ ጥቅምት 13 ሲውል ነነዌ በየካቲት ይውላል፡፡የባሕረ ሐሳብ መነሻው ዓመተ ዓለም መቁጠሪያው ዐውደ አበቅቴ ስለሆነ፡-
መጀመሪያ የ2005 ዓ.ም. ዓመተ ዓለምን እንፈልጋለን፡፡
5500 + 2005 = 7505 ይሆናል፡፡
አሁን 7505ን ለ 19 አካፍለን ቀሪውን እንይዛለን (እንገድፋለን)፤
7505 ÷ 19 = 395 ስለደረሰ ቀሪ አልተገኘለትምና 19 ይያዛል ፡፡
ይህም ዓለም ከተፈጠረበት እስከ 2005 ዓ.ም. ድረስ 395 ዐውደ አበቅቴ መሙላቱን የ395ኛው ዐውድ 19ኛ ዓመት ላይ መድረሱን ያሳያል፡፡ 2005 ተጀመረ እንጂ ስላልተፈጸመ ከ19ኛው ዓመት ላይ አንድ ቀንሰን 18 እንገኛለን፡፡ ይህን ወንበር እንለዋለን፡፡ ባለፉት 18 ዓመታት ስንት አበቅቴዎች (በፀሐይና በጨረቃ መካከል ያለው የ11 ቀን ልዩነት(365-354 = 11) እንዳለፉ ያሳየናል፡፡ በዚህም መሠረት የ2005 አበቅቴ 11 × 18 = 198 ይደርሳል፡፡ እርሱም ለ 30 ይካፈላል፡፡
198 ÷ 30 6 ደርሶ 18 ይቀራል፡፡ አበቅቴው 18 ሆነ ይሏል፡፡ መጥቅዕን ለማወቅ ቀላሉ መንገድ አበቅቴ + መጥቅዕ =30
መጥቅዕ = 30 – አበቅቴ
= 30 -18 = 12
የመጥቅዕ ወሰን በመስከረም 15 እና በጥቅምት 13 መካከል በመሆኑ 12 ደግሞ ከ15 በታች በመሆኑ መጥቅዕ ጥቅምት 12 ይውላል፡፡
መጥቅዕ ጥቅምት 12 መዋሉን ካወቅን በኋላ ምን ቀን ላይ እንደሚውል ማወቅ ያስፈልገናል፡፡ እርሱን ለማወቅ ደግሞ የግድ መስከረም 1 ቀን ምን ቀን እንደዋለ ማወቅ አለብን፡፡
መስከረም 1 ምን ቀን እንደዋለ ለማወቅ፡-
ዓመተ ዓለሙን ለዓውደ ፀሐይ እናካፍላለን፡፡ ዓውደ ፀሐይ በየ28 ዓመቱ ይመላለሳል፡፡ በየ28 ዓመቱም መስከረም 1 ቀን ማቴዎስና ረቡዕ ዓመቱን እኩል ይጀምራሉ፡፡ ዓመተ ዓለሙን ለዐውደ ፀሐይ ስናካፍል
7504 ÷ 28 = 71 ደርሶ 17 ይተርፋል፡፡ እንደሚታወቀው ሁሉ በአንድ ዓመት ውስጥ 365 ¼ ቀናት አሉ፡፡
በአንድ ዓመት 52 ሳምንታት አሉ፡፡ 52 × 7 = 364 ቀን ይሆናል፡፡በአንድ ዓመት 1 ¼ ቀን ተንጠልጥሎ ይገኛል፡፡ በአንድ ዓመት 1 ሙሉ ቀን ከተገኘ በ 17 ዓመት 17 ቀን ይገኛል፡፡ ¼ ኛው በ የአራት ዓመቱ 6ተኛ ጳጉሜን ሆኖ ይያዛል፡፡
በ17 ዓመት ውስጥ ጳጉሜን 6 የምትሆነው 4 ጊዜ ነው፡፡ስለዚህ 17 + 4 = 21 ቀን ይሆናል፡፡
ይህንን 21 ቀን ለሳምንቱ ቀናት ስናካፍል 3 ይደርሳል፤ 21 ÷7 = 3 ፡፡ ቀሪ ስለሌለው ወይም እኩል ስለመጣ 7 ይሆናል፡፡
ፀሐይና ጨረቃ ከተፈጠሩበት ከረቡዕ ተነሥተን ስንቆጥር ረቡዕ 1 ብሎ፣ ሐሙስ 2፣ ዓርብ 3፣ ቅዳሜ 4፣እሑድ 5፣ ሰኞ 6፣ ማክሰኞ 7 ብሎ ያበቃል፡፡በዚህም መሠረት መስከረም 1 ቀን ማክሰኞ ውሏል፡፡
መስከረም 1 ማክሰኞ ስለዋለ ጥቅምት 1 ሐሙስ ይብታል፤ ጥቅምት 12 ሰኞ ይውላል፡፡ ተዘዋዋሪ በዓላቱና አጽዋማቱ የሚገኙት መጥቅዕ፣ መጥቅዕ የሚውልበት ተውሳክና የበዓላትና የአጽዋማት ተውሳክ በመደመር ነው፡፡
በዚህም መሠረት የጥቅምት 12 ሰኞ ተውሳክ እና መጥቅዑን አንድ ላይ እንደምራለን፡፡
የዕለት ተውሳክ ከቅዳሜ 8 ብሎ ይነሣል፡፡ ቅዳሜ 8፣ እሑድ 7፣ ሰኞ 6፣ ማክሰኞ 5፣ ረቡዕ 4፣ ሐሙስ 3፣ ዓርብ 2፤
ስለዚህ የሰኞ ተውሳክ 6 ይሆናል፡፡ የሰኞ ተውሳክ 6 ከመጥቅዕ 12 ጋር ሲደመር (6+12) 18 ይሰጠናል፡፡ ይህም መባጃ ሐመር ይባላል፡፡ በእርሱም ጾመ ነነዌ ይታወቃል፡፡
ነነዌ፣ ሰኞ የካቲት 18 ቀን 2005 ዓ.ም. ይያዛል፡፡
ዐቢይ ጾም (ሁዳዴ)፣ የነነዌ ጾም ከገባባት ማግስት ጀምሮ ከ14 ቀን በኋላ ይገባል፡፡
18 + 14 = 32፡፡ ይህም 30ው የየካቲት 2ቱ የመጋቢት ሆኖ ዐቢይ ጾም መጋቢት 2 ቀን ይያዛል፡፡
ደብረዘይት = 18 + 11(41) =29 = መጋቢት 29 ይውላል፡፡
ሆሳዕና = 18 + 2(62) = ሚያዝያ 20
ስቅለት = 18+7(67) = ሚያዝያ 25
ትንሣኤ = 18 +9(69) = ሚያዝያ 27
ረክበ ካህናት = 18 + 3(93) = 21 = ግንቦት 21
ዕርገት = 18 + 18(108) = 36(6) = ሰኔ 6
ጰራቅሊጦስ = 18 + 28(118) = 46(16) = ሰኔ 16 ይውላል፡፡
ጾመ ሐዋርያት = 18 + 29(119) =47(17) = ሰኔ 17 ይያዛል፡፡
ጾመ ድኅነት = 18 + 1(121) = ሰኔ 19 ይያዛል፡፡
የቀመሩ መንገድ ይህ ነው፡፡
የእግዚአብሔር ቸርነት፣ በረከቱና ሰላሙ ዓመቱን ሙሉ አይለየን፡፡
አሥርቆት
ከጌታችንና ከአምላካችን ከመድኃኒታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ሕግና ትዕዛዝ የተገኘው የዘመናትና የዓመታት ቁጥር፣የሌሊትና የመዓልት ወሮች መባቻ አቆጣጠር ሥርዓት በምንናገርበት በዛሬው [መስከረም አንድ] ቀን ለልዑል እግዚአብሔር ምስጋናን እያቀረብን፣ አሁን ካለንበት ከወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ [2005] እንዳደረሰን እንዲሁም ወደ ዜናዊው ቅዱስ ማርቆስ ዘመን [2006] እንዲያደርሰን ፈቃዱ ይሁን፡፡ አሜን፡፡
ዓመተ ዓለም በፀሐይ 7505 ዓመት፣ በጨረቃ 7734 ዓመት፣ 9 ወር 22 ቀን ነው፡፡ ይህ ዓመተ ዓለም መዋዕለ ዓለም ይባላል፡፡ ከዚሁም፡- በፀሐይ 5500 ዓመት፣ በጨረቃ 5668 ዓመት 10 ወር ከ9 ቀን ዓመተ ፍዳ ዓመተ ኩነኔ፣ ዘመነ ብሉይ ይባላል፡፡ እንዲሁም በፀሐይ 2005 ዓመት፣ በጨረቃ 2065 ዓመት 11 ወር 13 ቀን ዓመተ ሥጋዌ ፣ ዘመነ መሢሕ ይባላል፡፡ በፀሐይና በጨረቃ ጥምር አቆጣጠርም 2013 ዓመት ይሆናል፡፡ ይህም ዓመተ ምሕረት ዘመነ ሐዲስ ይባላል፡፡ ዛሬ በዚሁ ቀን ከመስከረም ወር መባቻ እንደደረስን እንዲሁም ወደ ጥቅምት ወር መባቻ በሰላም እንዲያደርሰን ፈቃዱ ይሁን፤ አሜን፡፡
የሌሊት መባቻ 20፣
የጨረቃ መባቻ 24፣
የመዓልት መባቻ 1፣
ዕለተ ዮሐንስ 3 (ከእሑድ ተነሥቶ ሲቆጥር)፣
ጥንተ ቀመር 1 (ከማክሰኞ ተነሥቶ ሲቆጥር)፣
ጥንተዮን 7 (ከረቡዕ ተነሥቶ ሲቆጥር) ነው፡፡
ፀሐይ ከታላላቆቹ መዓርጋት በአንደኛው ማዕርግ፣ በአራተኛው ደጃፍ ሚዛን ማኅፈድ [ሰገነት]፣ በሕልመልሜሌክ [ዐቢይ ኮከብ] የምግብና ወራት በፀጋመ ሰማይ [በሰማይ ግራ] ሳለ፣ የጨረቃ ተረፍ 18፣ የፀሐይ ተረፍ 12 ሆነ፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፡፡አሜን፡፡ ይህ የመስከረም 1 ቀን የአሥርቆት ሥርዓት ነው፡፡ የሌሎቹ ዕለታት አሥርቆትም በዚሁ መንገድ ማውጣት ይቻላል፡፡
ስብሐት ለእግዚአ አዝማን ወዓመታት፣ወመዋዕል ለዓለመ ዓለም አሜን፡፡
ምስጋና ለዘመኖችና ዓመቶች፣ለወቅቶችም ጌታ ይሁን፡፡ አሜን፡፡
ምንጭ፡- በአለቃ ያሬድ ፈንታ ወልደ ዮሐንስ በ2004 ዓ.ም. የታተመው ‹‹ባሕረ ሐሳብ የቀመርና የሥነ ፈለክ ምሥጢር›› መጽሐፍ