የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ያልተማርነው ክርስቶስ

/ማሳሰቢያ፡- ይነበብ/

“እናንተ ግን ክርስቶስን እንደዚህ አልተማራችሁም ፤” ኤፌ. 4 ፡ 20 ።

አዳም በልምድ ፣ በቅብብሎሽ ፣ በትምህርት ፣ በምርምር ፣ በፍልስፍና ፣ በታሪክ ፣ በግኝት ከሚገኘው እውቀት ይልቅ ሰፊ የሆነ ጥበብን ተቀብሎ ነበር ። ጥበብ በኃጢአት ትጎሳቆላለች ። ፈሪሀ እግዚአብሔር ሲጠፋም የሰው እውቀቱ ከእንስሳት እያነሰ ይመጣል ። የትምህርት የመጀመሪያው ክፍል የሰው ልቡና ነው ። ሰው ራሱን በራሱ ፣ ራሱን በክስተት ፣ ራሱን በተፈጥሮ ፣ ራሱን በመንፈሳዊ መብራት የሚያስተምርበት የልቡና ክፍል ከሁሉ የላቀ ነው ። ከዚህ በፊት ሰምቶት ፣ አስቦት የማያውቀውን እውነት ሲሰማ ልክ ነው ይላል ። ልክ ነው ያለበት መመዘኛ ከየት መጣ ካልን በኃጢአት ምክንያት ተዳፍኖ የነበረ የእግዚአብሔር መብራት የሆነ እውቀት በውስጡ ስላለ ነው ። የሚሰማው እውቀት የተዳፈነውን መብራት ፍርድ ይሰጥ ዘንድ ገለል ያደርግለታል ። እውቀት እንደ ነፋስ ነው ፣ ትቢያን ያራግፋል ። እንደ እሳት ሆኖም እርጥቡን ያደርቃል ። ሰው በእውቀት አይለወጥም ፣ እውቀቱ በመንፈሳዊነት ሲታገዝ ግን እየተለወጠ ይመጣል ። በኖረ ቍጥር ፀጉሩ እያረረ ፣ ጥፍሩ እየዘረዘረ/እየጠነከረ ይመጣል ። እንዲሁም በኖረ ቍጥር ጠባዩ እየገነተረ ይመጣልና ዕድሜም አይለውጠውም ። ልቡናን የመጀመሪያው የትምህርት ክፍል ብንለውም ከዚያ በፊት የሚቀድሙ አሉ ። የትምህርት ሁለተኛው ክፍል የእናት እቅፍ ነው ። በእናቱ እቅፍ ውስጥ ሁኖ ፍቅርን ከወተት ጋር እየተመገበ ሕጻኑ ያድጋል ። ፍቅሩ ያለ ወተት ፣ ወተቱም ያለ ፍቅር አይሟሉም ።

ሦስተኛው የትምህርት ክፍል ቤተሰብ ነው ። ቤተሰብ ለሕጻኑ ይህችን ዓለምና ማኅበራዊነትን የምታስተምር የመማሪያ ክፍል ናት ። ጭካኔን ወይም ርኅራኄን ሕጻኑ ይማራል ። ሕጻኑ ግን ከቃል ይልቅ በቤተሰቡ ጠባይ እየተቀረጸ ይመጣል ። ሰው ቤተሰቡን ይመስላል ። እግዚአብሔር በመልኩና በምሳሌው ፈጠረን ፤ ቤተሰብ ደግሞ በመልኩና በምሳሌው ያሳድገናል ። በመልኩ ሲያሳድገን አፍቃሪ ወይም ዘረኛ አድርጎ ይስለናል ። በምሳሌው ሲያስተምረንም በውይይት ወይም በዱላ እንድናሳምን አድርጎ ያዘጋጀናል ። እስክንሞት ድረስ ወላጆቻችንን ተሸክመን የምንዞር ነን ። ከዚህ ከአሮጌው ቤተሰብ የምንለየው ክርስቶስን ሕይወት ስናደርግ ብቻ ነው ።

አራተኛው ትምህርት ቤት ዜማ ነው ። ስብሐተ እግዚአብሔርን ለማድረስ የአምልኮ ጥማተኛ ያደርገናል አሊያም ዘፈን ወዳድ የዝሙት ሎሌ ያደርገናል ። ዜማ በሰው ነፍስ ውስጥ ነውጥ ይፈጥራል ። ሁሉን ስለሚወድ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር የምንማረው በዜማ ነው ። ዘፈን ያለበት ዜማ ደግሞ ፍቅር ከተቃራኒ ጾታ ውጭ ለሌላ የማይሰጥ አድርጎ የሚቀርጸን ነው ። በርግጥ ሁሉም ዘፈን የዝሙት ማስታወቂያ አይደለም ። አገርንና ተፈጥሮን የሚያሳይ ዜማ አለ ። ጾታዊ ፍቅር ተገቢ ቢሆንም ጅማሬውና ፍጻሜው ሥጋዊ ፈቃድ ከሆነ ነፍስ የተለየው በድን ነው ። መምህራን ይህችን ዓለምና ሕይወትን የምንማርባቸው አምስተኛ ትምህርት ቤት ናቸው ። ለመምህራን ክብር የማይሰጥ አገር ትውልድን የከሰረ ነው ። ነገ ምን እንደሆነ የምናውቀው ለመምህራን በምናደርገው እንክብካቤ ነው ። መምህራን ሲራቡ ብስጩ ፣ ሲበሳጩ ሱሰኛ ፣ ሱሰኛ ሲሆኑ የተማሪ ጓደኛ ይሆናሉ ። መምህሩን መምሰል ለአንድ ተማሪ የተፈጥሮ ተጽእኖ ነው ። በመንፈሳዊውም ሆነ በሥጋዊ ጎዳና መምህራን ይቀርጹናል ። ሐረገ ትውልድ በቤተሰብ ብቻ ሳይሆን በትምህርት ቤትም አለ ። የአባት ዕዳ ለልጅ እንደሚተርፍ የመምህር ዕዳም ለተማሪ ይተርፋል ።

ስድስተኛው ትምህርት ቤት እንቢ የማንለው ኑሮ ነው ። ትዳር የሚጣፍጠው ትምህርት ቤት መሆኑን አምነው ለገቡበት ነው ። ሰው ራሱን የሚያገኝበት ትምህርት ቤት ነው ። “በሦስት ጉልቻ ይቅጣሽ” የሚል ርግማን በትዳር ተቀጪ ማለት ነው ። “ወልደህ እየው” የሚለው ርግማን ፣ ሲሰማ ቀላል ሲመጣ ግን ከባድ ነው ። ሰባተኛው ትምህርት ቤት ሰዎች ናቸው ፤ ሰዎችም ትልቅ መማሪያዎቻችን ናቸው ። ጎረቤት ተለዋዋጭነትን ማለትም በቀን ሰባት ጊዜ ማበድን ያስተምረናል ከጠዋት እስከ ማታ ወጥ ሰው መሆን መታደል ነው ። የሥራ ባልደረቦች ለእንጀራ መስገድን ፣ ለሚጠፋ መብል መኖርን በግርምት ያስተምሩናል ፤ ሰው ለኑሮው ሕይወትን ለምድር ዘላለምን ይሠዋል ። አለቃ በሌላ አለቃ እየደነበረ የሚኖር መሆኑን ፣ ለአለቃም አለቃ እንዳለው ይነግረናል ። ቀላል ሰዎች ክብርን እንደማይወዱ ፣ ወዳጆችም በስሜት እንጂ በእውነት መውደድ እንደማይችሉ ያስተምሩናል ።

በዚህ ዓለም ላይ ብዙ ትምህርት ያስተማሩን ቢኖሩም የተማርናቸው ሰዎች ግን ላይኖሩ ይችላሉ ። የተማርናቸው ሰዎች ካሉ እነርሱ ክርስቶስን የሚመስሉ ናቸው ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እውነት ነው ። እውቀት እውነት ይፈልጋል ። አሊያ አለማወቅ ነው ። አዳም እግዚአብሔርንና መልካምን የማወቅ እውቀት ነበረው ። ክፉን ግን በትእዛዝ እንጂ በገቢር አያውቃትም ነበር ። እግዚአብሔርም ክፉን በትእዛዝ እንጂ በተግባር አትወቃት ብሎ ሕግ ሰጠው ። አዳም ግን ክፉን በተግባር ሲያውቅ ወደቀ ። ሞትን ሞቶ አወቀ ። ጥይት እንደሚገድል ያወቅነው ቀምሰነው ሳይሆን ተምረነው ፣ በሌሎች ሞት አይተነው ነው ። አዳምም በትእዛዝ ማወቅ ፣ በሰይጣን ውድቀት መገንዘብ ሲገባው ሞትን ሞቼ ልወቅ አለ ። እውነተኛ እውቀት ግን ሕይወትን የሚሰጥ ነው ። ኒውክለርን የሠሩ ሄሮሽማና ናጋሳኪን ሲያስቡ ደስተኛ አይሆኑም ። ስልክ የሠሩ ግን በሰላም በአልጋቸው ይተኛሉ ። የዕለቱንም ዘላቂውንም እንቅልፍ /ሞትን/ በደስታ ያንቀላፋሉ ።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምንማረው እውነት ነው ። እርሱ መንገድ ሁኖ ወደ እውነት ያደርሰናል ። እውነት ደግሞ ነጻ ታወጣናለች ። ነጻነትም ሕይወትን ትሰጠናለች ። መንገድም ፣ እውነትም ፣ ሕይወትም ክርስቶስ ነው ።

ክርስቶስን እንዲህ አልተማርነውም ። ደስ ካለኝ ሁሉም ነገር ትክክል ነው ብለን ክርስቶስን አልተማርነውም ። ደስታ ለእግዚአብሔርና ለሰዎች መኖር ነው ። አላውቅም ፣ አልሰማም ፣ አላይም እያሉ መኖርን ከክርስቶስ አልተማርንም ። መፍትሔ ፈላጊነትን ተምረናል ። ብራብ አብልታችሁኛል የሚለው ረሀብተኛን ማየትን የሚጠቁም ነው ። አላይም ያለ ረሀብተኛን ፣ አልሰማም ያለ እስረኛን አይጎበኝም ። ሽሽትን ከክርስቶስ አልተማርንም ። እርሱ በጓዳ ሳይሆን በአደባባይ መሰቀሉ በር ከፍተን እንድንወጣና መሥዋዕት እንድንሆን የሚያስተምረን ነው ። ላለመውደድና ላለመወደድ ተጠንቅቆ መጓዝን ከክርስቶስ አልተማርንም ። የሚያደነዝዝ የዝሙት ትእይንትን ስናይ ለመዋልና ለማደር አልተጠራንም ። ራሳችንን ለክርስቶስ መስጠትን እንጂ ለሴሰኝነት አሳልፎ መስጠትን ክርስቶስን ከመሰሉ አባቶች አልተማርንም ።

የተማርነውን ክርስቶስን እንኑረው ።

ቸር ክርስቶስ ሆይ አንተን ለሚወድዱ ፀሐይ ይውጣላቸው ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 17 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ