የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ያልተንኳኩ ደጆችን አንኳኩ

“የደከሙትን እጆች አበርቱ ፥ የላሉትንም ጕልበቶች አጽኑ ። ፈሪ ልብ ላላቸው ፡- እነሆ ፥ አምላካችሁ በበቀል በእግዚአብሔርም ብድራት ይመጣልና፥ መጥቶም ያድናችኋልና በርቱ ፥ አትፍሩ በሉአቸው ።” ኢሳ. 35 ፡ 3-4 ።

አንድ በዕድሜ የገፉ አባት ደወሉልኝና፡- “በመልኩ የፈጠረውን ፊት አልየው ብሎ ይኸው በፊት መሸፈኛ ተጋርደን እንሄዳለን” አሉኝ ። የእኒህ አባት ንግግር በየቀኑ ይታወሰኛል ። የገዛ እጃችን ለአፍና ለአፍንጫችን እንደ ጠላት ተቆጥሮ ወደ ታች ያዙት ስንባል በጣም ይገርማል ። ልጆቻችን ሊያቅፉን እየፈለጉ ስንርቃቸው ልብ ይነካል ። ቀባሪ ጠፍቶ ፣ ሞት ሳይሆን በዚህ ጊዜ መሞት ሲያሳስበን ጉድ እንደማያልቅ ተገንዝበናል ። ባለፈው ወር በአንድ ገጠር ውስጥ የሰኔ ሚካኤልን ሲያከብሩ በዜማ በግጥም ሆ የሚያሰኘው ሰው እንዲህ ብሏል፡-

አንተ ኮሪና ነፍስህን አይማረው ፣

ወገን እፍር አለ መሳም እያማረው ፤

ቀድሞም በምንበላው ምግብ ፣ በምንለብሰው ልብስ ፣ በምንቀባባው ቅባት ፣ ፍርሃት ነበረብን አሁን ደግሞ ብዙ ፍርሃቶች ተጨመሩብን ። በዚህ ጊዜ በጭንቀት ስለሚያልፉ የሰው ልጆች ልቤ ያዝናል ። እግዚአብሔር የፈጠረውን አየር በነጻነት መሳብ ከመከልከል በላይ ምን አለ ? የሰው ልጆች ወደ እግዚአብሔር አቤት ብለን ብንጮህ እያልሁ እመኛለሁ ። እንዳንጸልይ ልብ በቂም ፣ አገር በክፋት ፣ ሰው በዘረኝነት ተይዞአል ። ከመጣው ችግር በላይ የምንፈጥረው ችግር የአምልኮ መንገዳችንን እየዘጋብን ተቸግረናል ። ይቅር ተባብለን “አቤት ፣ አቤት” ብንል እግዚአብሔር ፈጣን መልስ ይሰጣል ። የመጣውን ሳንመክተው ሌላ ችግር ለምንፈጥረው ልቡና ይስጠን ። 

የእግዚአብሔር ሰዎች የእግዚአብሔርን ድምፅ መስማት ያስፈልገናል ። “የደከሙትን እጆች አበርቱ” ይለናል ። ብዙ እጆች ዝለዋል ማለት ነው ። እጅ ለጸሎት ይዘረጋል ፣ “ጌታ ሆይ ላንተ ተማርኬአለሁ” ይላል ። ለጸሎት የሚዘረጉ እጆች ወንድምን ለመግደል ተግተዋልና የደከሙትን እጆች ማበርታት ይገባል ። ድል በእግዚአብሔር ሲሉ የነበሩ ድል በመግደል ወደ ማለት ገብተዋልና የደከሙትን እጆች ማበርታት ይገባል ። እጆች ለአምልኮተ እግዚአብሔር ካልተዘረጉ ሕንፃ ሥላሴ የሆነውን የሰው ልጅ ለማፍረስ ይተጋሉና የደከሙትን እጆች ማበርታት ይገባል ። እጆች ዘር የሚዘሩ ናቸው ። መሬቱን አለስልሰው ዘር የሚዘሩ እጆች ደክመዋልና ማበርታት ይገባናል ። ብዙ የሚያጽናኑ ፣ ብዙ የሚመክሩ ፣ ብዙ የሚያስተምሩ ተስፋ ቆርጠው ፣ በር ዘግተው ተቀምጠዋልና ማበርታት ይገባናል ። ዘንድሮ ካልተዘራ በሚቀጥለው ዓመት ረሀብ ይሆናል ። መምህራን ዛሬ ካላስተማሩ መካሪዎች ዛሬ ካልመከሩ ቀጣዩ ዘመን ፍሬ የሌለው ይሆናል ። ዕለቱን ዘርቶ ዕለቱን የሚያጭድ የለምና የሚዘሩ እጆችን በርቱ እያልን ማነቃቃት ይገባናል ።

 

እጆች የሚሰጡ ናቸው ። የተራበውን የሚያጎርሱ ፣ የታረዘውን የሚያለብሱ ናቸው ። በሰው ላይ ደግነትን የሚዘሩ እጆች እያጠሩ ነውና ማበርታት ይገባናል ። አጉርሰው ቢነከሱ ፣ ሰጥተው ቢሰደቡ ብዙ እጆች በቃን ብለው ተቀምጠዋል ። እነዚህን እጆች “ዋጋ ያለው ከእግዚአብሔር ነው” እያልን ማበርታት ይገባናል ። ሰው ቢሰፍር በእጁ መጠን ነውና ትንሽ ነው ። እግዚአብሔር ግን ሲሰፍር እጁ ሰፊ ነው ። የሚባርኩ እጆች ታጥፈዋልና ማበርታት ይገባናል ። ጀርባ እየደበደቡ የሚመርቁ ፣ እጅ ጭነው እየጸለዩ የሚፈውሱና የሚክኑ እጆች ደክመዋልና ማበርታት ይገባናል ። ምርቃት ያለው አይወድቅም ፣ አወይ የእግዚአብሔር ሰዎች ላዘኑባችሁ ። የምትሄዱት ወደ ተዘጋ መንገድ ነው ። መባረክ ሲገባን በድፍረታችን እንደ ሮቤል ምርቃት ያጣን ከሆንን ፈጥነን ይቅርታ መጠየቅ ይገባናል ። ዘመኑ እንኳን ለተረገመ ለተመረቀም አስቸጋሪ ነው ። ውሉደ ክህነትም ለቀጣይ እንዲሸጋገር ፣ ቃለ እግዚአብሔርን የሚማሩ ተማሪዎች እንዳይበተኑ ማበርታት ይገባናል ። አንዲት አገር ጽኑ ጨለማ የሚወርሳት ትምህርትን በጣለች ጊዜ ነው ። መምህራን ዛሬ ጉባዔ ፈትተዋል ። ተማሪዎች ተበትነዋል ። ሰባኪዎች የሚበሉት አጥተዋል ። ማበርታት ይገባናል ። 

“የላሉትንም ጕልበቶች አጽኑ” ይላል ። ጉልበት ሲላላ መራመድ አይቻልም ። ጉልበት ሲላላ መቆም አይቻልም ። ጡንቻ ካልጠነከረ ሥጋ ቀጤማ ነው ። ብዙ ጉልበቶች ላልተዋል ። ጽኑ የነበሩ ሰዎች ፈርተዋል ። ሌላውን ይሸከሙ የነበሩ እያንዳንዱ ቀን የማይገፋ ተራራ ሆኖባቸዋል ። እኛ የምንበረታው ሌላውን ስናበረታ ነውና የትላንት ጽኑዎችን ልናጸናቸው ይገባል ። አቋም የነበራቸው አቋም አጥተው ፣ ታጋሽ የነበሩ ገዳይ ሁነው ፣ በሃይማኖት የጸኑ በኑፋቄ ተበክለው ፣ ቤተ ክርስቲያንን ተግተው የሠሩ ተግተው ሲያፈርሱ ፣ ሕፃናትና ወጣቶችን የሚያንጹ ተልእኮአቸውን ሲያቋርጡ ፣ ክፉ እየበረታ ፣ ደጎች ሲደክሙ እያየን ነውና የላሉትን ጉልበቶች ማጽናት ይገባል ። ይሮጡ የነበሩ ሲራመዱ ፣ ይራመዱ የነበሩ ሲቆሙ ፣ ይቆሙ ነበሩ ሲወድቁ ስናይ ለማጽናት የታዘዝነው እኛ ነንና ሥራችንን መሥራት ይገባናል ። ዛሬ ደክመው ከመስመር የወጡትን፡- “ጎበዝ ነህ ፣ ጎበዝ ትሆናለህ ፤ ሥራህን ቀጥል” በሉአቸው ። እግዚአብሔር በዚህ ድምፅ ውስጥ ኃይለ መንፈስ ቅዱስን ያሳልፋል ። 

“ፈሪ ልብ ላላቸው ፡- እነሆ ፥ አምላካችሁ በበቀል በእግዚአብሔርም ብድራት ይመጣልና ፥ መጥቶም ያድናችኋልና በርቱ ፥ አትፍሩ በሉአቸው” ይላል ። 

የምንሰማው የምናየው ነገር ሁሉ የሚያስፈራ ይመስላል ። “እንደውም እንደው ነሽ ፣ እንኳን ተልባ ሸቶሽ ዘጠኝ ቂጣ ትፈጃለሽ” ይባላል ። ሰውነታችንን ስንዳብስ የምናገኘው ትንሽ ጠጣር ነገር ሁሉ ያስፈራናል ። የሐኪም ቀጠሮአችን ያስጨንቀናል ። የሚሰማንን ሕመም ጎግል እያደረግን እንቅልፍ እናጣለን ። በአጭር ቃል እምነት እየከዳን ነው ። ዓለም ዕለት ዕለት በመረጃ ታስጨንቀናለች ። እግዚአብሔር በቃሉ ሊያሳርፈን ሲል ከቃሉ ርቀናል ። አንድ ጽሑፍ አንብቤአለሁ፡- በጣም ከባድ ነው ይላል ።

አንድ ብር ለኔ ቢጤ መስጠት ከባድ ነው ፣ አሥር ብር ቲፕ መስጠት ግን በጣም ቀላል ነው ።

ሁለት ደቂቃ ጸሎት ማድረግ በጣም ከባድ ነው ፣ ሁለት ሰዓት ፊልም ማየት ግን በጣም ቀላል ነው ።

ከሥራ በኋላ ቤተሰብን መርዳት በጣም ከባድ ነው ፣ ከሥራ በኋላ ወደ መዝናኛ ቦታ መሄድ ግን በጣም ቀላል ነው ።

የተጎዳን መርዳት በጣም ከባድ ነው ፣ ፎቶ አንሥቶ ፖስት ማድረግ ግን በጣም ቀላል ነው ።

ይህን መልእክት ሼር ማድረግ በጣም ከባድ ነው ፣ ወሬዎችንና አሉባልታዎችን ሼር ማድረግ ግን በጣም ቀላል ነው ። 

ስለ ራሳችሁ ፣ ስለ ልጆቻችሁ ፣ ስለ አገራችሁ ፍርሃት ያለባችሁ እግዚአብሔር ክፉውን ሊበቀለው ዳግም የሚመጣበት ዘመን ደርሶአልና በርቱ ፣ አትፍሩ ። ነፍሳችሁም በዘላለም ማዳን ውስጥ ታርፋለች ። የሚፈሩትን ወዳጆቻችሁን በርቱ በሉአቸው ። እግዚአብሔር በአንደበታችሁ እንዲያጽናና ፍቀዱለት ። ከገንዘብ ስጦታ በላይ የማጽናናት ስጦታ ወሳኝ ነው ። ገንዘብ ለሁሉ ላያስፈልግ ይችላል ። የብርታት ድምፅ ግን ለነገሥታትና ለባለጠጎች ሳይቀር የሚያስፈልጋቸው ነው ። ያልተንኳኩ ደጆችን ዛሬ በብርታት ድምፅ አንኳኩ ። እግዚአብሔር የሚሠራውን ድንቅ ትሰማላችሁ ። ብቸኛ የሆኑ ሰዎችን ዛሬ አስታውሱ ። እግዚአብሔር በእናንተ ውስጥ ሁኖ አለሁ ሊላቸው ይፈልጋል ።

አቤቱ ጉልበቴ ሆይ እወድድሃለሁ ። 

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ነሐሴ 5 ቀን 2012 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ