የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ያማረንን ሳይሆን የሚያምርብንን

“ቁልቋል የወደቀው ቅርንጫፍ ስላበዛ ነው ።” /የትግርኛ ተረት/

እጅግ ዝግ የሆኑ ሰዎች ሰፊውን ዓለም እንደ መቃብር የሚኖሩበት ተንቀሳቃሽ ሬሳ ናቸው ። ገለልተኛ ኑሮ የሚመሩ ሰዎች አኗኗራቸው ጭንቅ ያለበት ሲሆን ሞታቸውም ቀባሪ የለውም ። ዘመናዊነት ከእግዚአብሔር ፍቅር ወደ እኔነት ፍቅር ፣ ከሰው ፍቅር ወደ ዕቃ ፍቅር የሰውን ልጅ ዝቅ ያደረገ የኑሮ ሥርዓት ነው ። እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥረው ሰው ለሰው ረዳቱ እንዲሆን ነው ። ሰው ሥጋ ፣ ነፍስና መንፈስ ያለው ሦስትነት በአንድነት የሆነ ፍጡር ነው ፤ በሥጋው ሲርበው እንዲያበላው ፣ በነፍሱ ሲያዝን እንዲያጽናናው ፣ በመንፈሱ ሲያጠፋ እንዲገሥጸው ለሰው ሰው ተፈጥሮአል ። ሰው ይህን ረዳትነቱን ጠብቆ የሚኖረው ግን ከእግዚአብሔር ጋር ስምም ሲሆን ብቻ ነው ። ሔዋን አዳምን ወደ ገደል የገፈተረችው ፣ ቃየን አቤልን የገደለው ረዳትነታቸውን በመዘንጋትና የእግዚአብሔርን ሕግ በመተላለፍ ነው ። የሰው ልጅ በነጻ የሚሰጥና በነጻ የሚቀበል ፍጡር ነው ። ካልሰጠ ባለ ዕዳ ፣ ካልተቀበለ ጎዶሎ ነው ። ዝግ ሰዎች እግዚአብሔር ሰውን ለማኅበራዊነት እንደ ፈጠረው ዘንግተዋል ። በዚህ ዓለም የሚጎዳውን ክፉ ነገር ብቻ ሳይሆን በልክ ያልተያዘ መልካም ነገርም ኑሮአችንን ያቃውሳል ።

ጓደኛ ያበዙ ሰዎች መከራ አብዝተዋል ። እውነተኛ ጓደኛ በምድር ላይ ውድ ነው ። ንጉሥ ዳዊት እንኳ ሁለት ወዳጆች ነበሩት ። አንደኛው ኬጢያዊው ኦርዮን ሲሆን ሁለተኛው የሳኦል ልጅ ዮናታን ነው ። ኬጢያዊው ኦርዮን ከአሕዛብ ወገን ቢሆንም ከእስራኤል የጠፋው ታማኝነት የተገኘበት ሰው ነበር ። ጓደኛ የሚገኝበት ስፍራ ከዚህ ነው ማለት አስቸጋሪ ነው ። ወንድም ከሚባለው የሃይማኖት አጋር ጠፍቶ ከማይጠበቅበት ስፍራ ጓደኛ ሊገኝ ይችላል ። በልባቸው እስራኤል የሆኑ አሕዛብ ፣ በልባቸው አሕዛብ የሆኑ እስራኤል በሁሉም ዘመን ነበሩ ፣ ዛሬም አሉ ፣ ወደፊትም ይኖራሉ ። ኦርዮን ግን በነቢዩ ዳዊት ተከዳ ። ገንዘቡን ሳይሆን ሕይወትና ትዳሩን በአደባባይ ተቀማ ። ሁሉም ሲመቸው ለካ በዳይ ኑሮ ዳዊትም ስደቱ ንግሥና ሲያመጣ አስለቃሽ ሆነ ። ዮናታን አልጋ ወራሽ ፣ ከሳኦል ቀጥሎ የሚነግሥ ነው ። አባቱ ሳኦል የሚዋጋው እንደ ሥጋ ስሌት ለዮናታን ወንበር ብሎ ነው ። ዮናታን ግን በፍቅር ዙፋንን ለዳዊት የለቀቀ ነው ። ዳዊት ዮናታን በሞተ ጊዜ ፍቅሩ ኃያል መሆኑን አስታውሶ አለቀሰ ። ዳዊት እንኳ የታወቁ ወዳጆቹ ሁለት ነበሩ ። አንዱን ራሱ አስገደለው ፣ ሁለተኛው ደግሞ ማለትም ዮናታን በሞተ ጊዜ ፍቅሩን ሲያዘክረው ኖረ ። እውነተኛ ወዳጅ ጥቂት ነው ። ዕድሜም የለውም ። አንዳንዴ ወዳጃችንን አናውቅምና እናስቀይመዋለን ። ሌላ ጊዜም የማንቀየመው ሞት ይወስድብናል ።

ብዙ ጓደኛ ያላቸው ምንም ጓደኛ የላቸውም ። የችግር ቀኖች በምድር ላይ የተዘጋጁት የወዳጅን ልክ የሚያሳዩ ስለሆኑ ነው ። ወዳጅ የመሰሉት ጠላት ሲሆኑ የማንወዳቸው ደግሞ ወዳጆቻችን ይሆናሉ ። ክፉ ቀን አይጠላም ። የሰውን ልክ ያሳያል ።

በዚህ ዓለም ላይ ብዙ አሳብ ማብዛት ይጥላል ። አንዱን መያዝ አንዱን መጣል ከንቱ ነዋሪ ያደርጋል ። ግብ የሌለው ጅማሬ ሁልጊዜ ፍርሃት ነው ። እንደ ቀኑ መዋል ጉልበት ጨራሽ ነው ። ያለ ዓላማ የሚከወን መልካም ነገር ሁሉ ዋጋው ትንሽ ነው ። የአሳብ ድርድሮች ማብዛት ፣ በምኞት ሰክሮ መተኛት አጭሩን ዘመናችንን ይበላብናል ። እኔ የተፈጠርኩትና ላደርግ የምችለው የቱን ነው ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል ። ዘጠኝ ጊዜ አስቦ አንድ ጊዜ መቍረጥ ተገቢ ነው ። አሊያ አንድ ጊዜ አስበን ዘጠኝ ጊዜ እንቆርጣለን ። ውጤቱም ባዶ ይሆናል ። ዕቅድ የሚያበዙ ሰዎችም በሥጋቸው በድካም ፣ በነፍሳቸው በዝለት ፣ በመንፈሳቸው በማጉረምረም ይመታሉ ። ዕቅድ ሲያንስ ውጤት ይበዛል ። ዛሬ የሚያስፈልገው ፣ ዛሬ ላደርገው የምችለው ፣ ዛሬ ላደርገው የሚገባኝ የቱ ነው ብሎ ማሰብ አስፈላጊ ነው ። ብዙ ውጥን ብዙ ወሬ እንጂ ጥቂት ሥራ አያመጣም ። በውጥኑ ልክ ጠላት እያስነሣን በሌለ ነገር ተጨባጭ መከራ እንቀበላለን ።

ብዙ ሥራ መሥራት መልካም ነው ። ሰው ግን አቅሙ አነስተኛ ነውና አንዱን ቢያሳካ የተሻለ ነው ። ብዙ ፎቅ ብንሠራ የምናድረው አንድ ጠባብ ክፍል ውስጥ ነው ። የተበታተነ ኃይል የተሸራረፈ ድል ያመጣል ። ሁሉንም ነካ ነካ ማድረግ ይቻላል ። አንዱን በቅጡ ማድማት ግን የሰው ወጉ ነው ። የብዙ ሙያ ባለቤት መሆን ጥሩ ነው ። የብዙ ሙያ ባለቤት መሆን ግን ጠባይን ዘማ ያደርግና በመጨረሻ መና ያደርጋል ። ሁሉን ለማወቅ ፣ ሁሉን ለመተዋወቅ ፣ ሁሉን ለመሥራት ፣ ሁሉን ለመልመድ አልተፈጠርንም ። ብዙ የፖለቲካ መድረኮችን መርገጥ ለላይም ለታችም ደጋፊ መሆን ውድቀት ያመጣል ። የሁለት አገር ሰላዮች መጨረሻቸው ሞት ነው ። አውሬ አርቢዎች መጨረሻቸው ሞት እንደሆነ በስለላ ቁማር መጫወትም መጨረሻው የከፋ ነው ። ብዙዎቹ የት እንደ ተበቀሩ እንኳን አይታወቅም ።

እኛ አልፋ ኦሜጋ መሆን አንችልም ። እኛ ከጀመርን ሌሎች ይፈጽማሉና ደቀ መዛሙርት ያስፈልጉናል ። የጨረስነው ካለ ሌሎች የጀመሩት ነውና የቀደሙትን ማመስገን ይገባናል ። ብቻ ቅርንጫፋችን ሲበዛ በአሳብ ፣ በመንፈስም ፣ በሥጋም እንወድቃለን ።

ጌታ እግዚአብሔር ሆይ ያማረንን ሳይሆን የሚያምርብንን ይስጠን ።

የብርሃን ጠብታ 14
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ጥቅምት 9 ቀን 2014 ዓ.ም.

ያጋሩ