“አቤቱ ፥ ረድኤቴ መድኃኒቴም ፥ የአፌ ቃልና የልቤ አሳብ በፊትህ ያማረ ይሁን ።” መዝ. 18 ፡ 14 ።
ጌታ ስለሆንህ ጌታ የምንልህ ፣ አምላክ ስለሆንህ አምላካችን ያልንህ ፣ ንጉሥ ስለሆንህ ንጉሣችን ብለን ያነገሥንህ ፤ ለጥበብህ መመርመር ፣ ለባሕርይ ሞት ፣ ለብልጥግናህ እጦት ፣ ለኃይልህ መድከም ፣ ለህልውናህ መታጣት ፣ ለመቅረብህ መራቅ ፣ ለርቀትህ መደረስ የማይስማማህ ፣ እኔ ብለህ ለመናገር አንተ የሆንከው ፣ ለጠባይህ ለውጥ የሌለብህ ፣ ሰው ወዳጅ እግዚአብሔር ሆይ አቤቱ አቤቱ እንልሃለን ። ከርግብ አንሰን በአንድ ቃል ኪዳን መጽናት ቢያቅተን ፣ ከውሻ አንሰን ታማኝነት ቢጎድልብን አቤት አቤት እንልሃለን ። ታላላቆች የታሪክ አቧራ ሲጫናቸው ፣ ጠቢባን የዘመን ትቢያ ሲከድናቸው የማትደብስና የማትደበዝዝ ወርቅ ኢየሱስ ሆይ እናደንቅሃለን ።
ሰዎች እንዲሆንላቸው አንፈልግም ፣ እንዲሆንልን ግን እንከጅላለን ። የልባችን አሳብ ክፉ ነውና እባክህ አሰማምረን ። የጣለው በረዶ ፣ የወረደው መብረቅ ምሬተኛ ቢያደርገን አፈ ማር ክርስቶስ ሆይ ፣ አንደበታችንን አጣፍጥልን ። የምንችለውን ማድረግ ተስኖን የማንችለውን ለማድረግ እንመኛለን ፣ ባለ ቃልኪዳኑ አማኑኤል ሆይ ለጽድቅ ቀጠሮ ከማብዛት እባክህ አድነን ። ከወፎች ዝማሬ ጋር የማለዳ ምስጋናችንን አስማማልን ። ስታነጋልንና ስታኖረን ያልከበደህ አንተ ሆይ ለማመስገን ከብዶናልና እባክህ ይቅር በለን ። ይህች ቀን ምሕረትህን ለሚጠባበቁ ዕለተ ብርሃን ትሁን ። ብዙዎች በተሳፈሩበት ስምህ ለዘላለሙ አሜን !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 18 ቀን 2015 ዓ.ም.