የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ያንተን ላንተ ላቅርብ

“ሁሉ ከአንተ ዘንድ ነውና፥ ከእጅህም የተቀበልነውን ሰጥተንሃልና ይህን ያህል ችለን ልናቀርብልህ እኔ ማን ነኝ? ሕዝቤስ ማን ነው?” 1ዜና. 29፡14 ።
ከሰጠኸኝ የአካል ክፍል የእኔ የምለው የቱን ነው ? ካንተ ውጭስ አላጣውም ብዬ የምፎክርበት ንብረቴ እኮ የቱ ነው ? በየዕለቱ ካንተ በቀር የእኔ የምለውን ነገር እየፈራሁ እኖራለሁ ። ጥዋት ተናግረውለት እስከ ማታ የማያመሽ ፣ አለኝ ሲሉት የጉም ስፍር የሚሆን ይህ ዓለም ምንድነው ? ትላንት የነበርኸኝ ፣ ዛሬም ያለኸኝ ፣ ነገም የምትኖረኝ አንተ ነህ ። ሕፃን ልጅ የሰጡትን አምጣ ሲሉት እንደሚያለቅስ እኔም አንተ ከሰጠኸኝ ላይ አሥራት በኩራት ለመስጠት አለቅሳለሁ ። እባክህን ይህን መንፈሳዊ ሕፃንነቴን አሳድገው ። ነገሥታትን ስለምፈራ በግድ ግብር እከፍላለሁ ። ቅጣትም ፈርቼ በጊዜው እሰጣለሁ ። የፍቅር መንግሥት የምትሆን ያንተን መንግሥት ግን ችላ ብያለሁ ። ወንጌል ሲበደል ፣ አገልጋዮች ተስፋ ቆርጠው ወደ ሥጋዊ ኑሮ ሲመለሱ እያየሁ ገና እሰስታለሁ ። ላለመስጠት ብዙ የደለቡ ምክንያቶችን አዘጋጅቻለሁ ። የማይመለከተኝን እናገራለሁ ። እባክህን የሰጪ ጌታ ልጅ ፣ ስስታም አይደለምና መስጠትን አለማምደኝ ። የማይሰጥ ደስታ የለውምና እባክህን ይህን ብፅዕና ጨምርልኝ ። ብሰጥም ያንተን ላንተ ነው ።ስለሰጠሁም ራሴን ከማድነቅ ጠብቀኝ ። ገበሬ ዘሩን አይበላምና ዘር የተባለውን አሥራት በኩራት ከመብላት አድነኝ ። ሕይወቱን በመስቀል ላይ ሰጠኝ እያልሁና እየሰበክሁ ገና በገንዘብ ካልታመንሁ በእውነት ከንቱ ነኝና ይህን ግብዝነት አርቅልኝ ።
በሰጠኸኝ እውቀት ፣ በሰጠኸኝ ጉልበት የማገለግልበት ዘመን አድርግልኝ ። በሚያልፍ ዕድሜ የማያልፈውን ለመሥራት አብቃኝ ። መስጠት ዕድል ነው ። መስጠት ያልቻለ ተቀባይ ይሆናልና እባክህን መስጠትን አለማምደኝ ። ስለ ድሆች ፣ በየመንገዱ ስለወደቁ ያንተ ሕንፃዎች እንዳዝንና እንድተጋ እርዳኝ ። እኔ ጥዋት ለከሰዓት እየራበኝ ምንም የሌላቸውን ድሆች እንዳስብ አግዘኝ ። አሁንም ብሰጥ እንኳ ደግነቴ ሳይሆን ግዴታዬ መሆኑን አስተምረኝ ። ሁሉ ያንተ ነውና ያንተን ላንተ እንድሰጥ በሁለንተናዬ አንተን እንዳከብር እርዳኝ ። ስላደረግህልኝ ነገር ሁሉ ምስጋና ላንተ ይሁን ። ለዘላለሙ አሜን ። 

ያጋሩ