የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ያንተ ፍቅር

  
ወደ ዙፋንህ ለመቅረብ ፣ ወደ ህልውናህ ለመድረስ አልችልም ። ከዙፋንህ መራቅ ፣ ከህልውናህም መሰወር አይሆንልኝም ። ሊቀርቡህ ግርማዊ ፣ ሊርቁህ ሞገሳዊ ነህ ። ማስፈራትን ከውበት ጋር ፣ ፍቅርን ከፍርድ ጋር ፣ ዙፋንን ከበረት ጋር ፣ ሞትን ከሕያውነት ጋር ያስተባበረ እንደ አንተ ማን አለ ! አንተ የእኔ የሆንከው በፍቅር ነው ። እኔ ያንተ የምሆነው በግድ ነው ። አንተ ግን ራስህን ስትሰጠኝ እኔ ርቄሃለሁ ። አስገድደህ ልታሰግደኝ ስትችል በፍቅር ታባብለኛለህ ። እሳቴ እንዳይጠፋ ፍቅሬን አበርታ ። መቅረዜ እንዳይወሰድ መንፈስህን ከማሳዘን ጠብቀኝ ። በሌለህበት ከመገኘት ፣ ባለህበት ከመታጣት ጠብቀኝ ። ጎበዝ ሁሉ ሲቆረጥ ደካማውን እኔን ትከለኝ ። የጠገቡ በሚራቡበት ቀን እኔን ችግረኛውን ዋስ ሁነኝ ። አገሩን የሞሉ አድራሻቸው ሲጠፋ ለእኔ ጥግ ስጠኝ ።
ካንተ ውጭ ማንም የለም ። ካንተ ውስጥም ምንም አይታጣም ። የሚሞቱ ነገሥታትን የምትሾም ሕያው ንጉሥ ፣ የሚሻሩትን የምትቀባ የዘላለም ቅዱስ አንተ ነህ ። እስከ ሞት ብናገለግልህ እስከ በሌለው ዘላለም ታገለግለናለህ ። ከምንሰጥህ የምትሰጠን ይበልጣል ። ሠረገላዎችህ አይነኩም እሳት ናቸው ። ቅጥርህ አይደፈርም ነበልባል ነው ። የቤትህ ግድግዳና ጠፈር በውኃ የታነፀ ነው ። መሠረቱም የደም ነው ። ልዑል ሆይ ማደሪያዎችህን ነፍሴ ወደደቻቸው ። የሃይማኖት መሠረት ፣ የደናግል ንጽሕና ፣ የሰማዕታት ጭከና አንተ ነህ ። ፍቅርህ ከሞት ይልቅ ይበረታል ። እንዲህ ባትወደን አንድንም ነበር ። መርከቤ ሲናወጥ ሥላሴ ሆይ መቅዘፊያውን ያዝልኝ ። ግራና ቀኝ ማዕበል ሲያማታኝ የቃልህ መልሕቅ ያጽናኝ ። ሞት ከፊቴ ቆሞ ሲፎክር ትንሣኤህ ብርታት ይሁነኝ ። ወደቡ ሲርቀኝ የመንፈስህ ተስፋ ይደግፈኝ ። ጭነቱ ሲከብደኝ መስቀልህ ቤዛ ይሁነኝ ። መሐል ባሕር ላይ አቅጣጫ ሲጠፋኝ ብርሃንህና እውነትህ እነርሱ ይምሩኝ ። መሠረቴ ውኃ ፣ ዙሪያዬ ማዕበል ሲሆን የጠራኸኝ ጌታ አጽናኝ ።
አማኑኤል ሆይ በክንፍህ መዘርጋት ይህን ትውልድ አንተ ጋርድ ። ከጣፈጠን ስህተት አውጣን ። የመረረንን እውነት አጣፍጥልን ። ዛሬን ያለፉት ዘመኖች ካሣ አድርግልን ። የቤተ ክርስቲያንን ምርኮ መልስ ፤ የሄዱብንን መልካም ነገሮች ሁሉ እንደገና ገንዘብ አድርግልን ። ከትእዛዝህ አታርቀን ፣ ከመውደድህ አትለየን ። ጣዕም ካለው ዜማ ፣ ምዑዝ ከሆነ ዕጣን ፣ ከሚያውድ የናርዶስ ሽቱ የሚበልጠው ያንተ ፍቅር ነፍሴን ይቆጣጠር ። የማይረዱኝን ፍለጋ ፣ የማያድኑኝን አሰሳ ይብቃኝ ። በዚህ ዓለም ሹሞች ሳይሆን ማመኔን ባንተ አድርግልኝ ። ልቤን ባንተ አሳርፍልኝ ።
ምስጋናህ ከመላእክት ትጋት በላይ ነው ። ከተፈጠሩ ቀን ጀምሮ እስከዚች ቅጽበት ያለ ዕረፍት ፣ ምስጋናህ ዕረፍት ሁኗቸው ያመሰግኑሃል ። ክብርህን መዝለቅ ፣ ታላቅነትህን በዜማ መደምደም አልተቻላቸውም ። የደናግል ንጽሕና ያንተን ቅድስና አይገልጥም ። የሰማዩ ስፋት ለትልቅነትህ ፣ የምድር ጽናት ለብርታትህ መግለጫ አይሆንም ። እኔም ያቀረብሁልህ ምስጋና ምንኛ ትንሽ መባ ነው ። አንተ ሆይ ፣ ጌታው ሆይ አብዝተህ ተቀበለው ። ለዘላለሙ አሜን ።
የነግህ ምስጋና /9
መጋቢት 1 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ