የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ያየኸው ይድናል

የልብን ጩኸት ፣ የነፍስን መቃተት ፣ የመንፈስን አሰሳ የምታስተውል ጌታ ፣ የለም ያሉህን እየሻርህ አንተ ግን በሚያበራ ሕልውና ትኖራለህ ። ከተድላ ርቆ ልቅሶን ለተዛመደው ፣ ከሕያዋን ሸሽቶ ከመቃብር መንደር ለሚኖረው ፣ እኔ ምልምል ዛፍ ነኝ ብሎ በረሃ ላይ ብቻውን ለቆመው አንተ በፍቅር ድምፅ ታነጋግረዋለህ ። ስንጥቅ ልቡንም ገጥመህ ትይዝለታለህ ። የሚያፈሰውን ብሶት ትገድብለታለህ ። ከልቡ የትካዜን ዙፋን ትሽራለህ ፣ ከፊቱ የእንባን ጅረት ታደርቃለህ ። የእጁን ሰንሰለት ቆርጠህ ፣ የጠሉትን ወዳጅ አድርገህ ፣ በተሰደደበት ቤት ሹመህ ፣ የገዛ ነፍሱን ምርኮ አድርገህ ሰጥተህ ታኖረዋለህ ። ዓለም ቤቴ አይደለም ላለው ዓለም ሁነህ ታኖረዋለህ ። ተስፋ ሁነህ ልቡን ታበራለታለህ ። የልቅሶ ዜማን በቅዳሴ ፣ የኀዘን እንጉርጉሮን በቅኔ ፣  ደረት መድቃትን በልብ ሐሤት ትለውጥለታለህ ። የተከደነውን ሳትከፍት ፣ የተጋረደውን ሳትገልጥ ታያለህ ። ለመርዳት እንጂ ለመታዘብ አታይም ። ለማቀፍ እንጂ ለመገፍተር አትጠጋም ። አንተ የልብስ ወዳጅ አይደለህም ፣ አንተ የሰው ወዳጅ ነህ ። አንተ የሽቱ ወዳጅ አይደለህም ፣ አንተ የነፍስ ወዳጅ ነህ ። ያንተ ኅብረት ከመቆም ከመነሣት ፣ ከጤና ከበሽታ ጋር አይደለም ፣ አንተ የምታከብረው ሕይወትን ነው ። ሕይወት በአልጋም  በጎዳናም ያው ሕይወት ናት ። እኔ ግን የቁመና ወዳጅ ነኝና ሲወድቁ የለሁም ። እኔ ግን የጤና ወዳጅ ነኝና ሲያቃስቱ እሸሻለሁ ።
ጌታ ሆይ በነቀፋና በወቀሳ የደነቆረውን በፍቅርህ ዜማ ታነቃዋለህ ። እኔ ላንተ አልሆንም ያለህን ይበልጥ ትወደዋለህ ። ሊርቅህ ምክንያት የሚያቀርበውን ያለ ምክንያት ታፈቅረዋለህ ። እንደ ባሪያው እንኳ በሆንሁ ለሚልህ የልጅነት ቀለበት ታስርለታለህ ። ተርቦ ለመጣው ፍሪዳ አርደህ ትቀበለዋለህ ። የእርያ ጓደኛ የነበረውን የመላእክት ማኅበረተኛ ታደርገዋለህ ። በሰማይ በምድር በደልሁህ ላለህ ፣ በሰማይ በምድር ርስት ትሰጠዋለህ ። በገዛ እልሁ የደከመውን ፣ የገዛ ጉልበቱ የከዳውን ፣ የልጅ ባላጋራ የገጠመውን ፣ ከራሱ የተሰደደውን ያንን ፈሪ ጨለማውን ታነጋለታለህ ። ቅድስናን አልብሰህ ጽልመታዊውን ድሪቶ ትገፍለታለህ ።
የደረቀ መሬትን የምታለመልም ፣ ፍሬ አልባዋን ዛፍ የምትባርክ ፣ ደረቅ ነኝ ያለውን ጃንደረባ በቤትህና በቅጥርህ የማይጠፋ መታሰቢያና ስም የምትሰጥ አንተ ነህ ። አንተን ላለ አንተ አለህ ። እጅግ እንወድህ ዘንድ እርዳን ። በተመረጠች ቀን እንዳንተኛ አንቃን ። ክፉ ሲመለስልንም ደግ መሆንን አስተምረን ። ያየኸው ይድንልሃል ፣ እባክህ እየንና እንዳን ። ለዘላለሙ አሜን ።
የነግህ ምስጋና /7
የካቲት 23 ቀን 2012 ዓ.ም
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ