“አምልኮት በእውነትና በመንፈስ መሆን አለበት (ዮሐ. 4፡24) ።
የአዲስ ኪዳን የአምልኮ መስፈርቱም ይህ ነው ።”
አምልኮ እግዚአብሔርን እያዩ በእውነተኛ ልብ መደረግ ይሻል ።
በምድራዊቷ ቤተ ክርስቲያን በአካል ፣ በመንፈስ ደግሞ በሰማያዊቷ ቤተ
ክርስቲያን ተገኝቶ መቅረብ አለበት ። መንፈሳችን በጸሎት ሰዓት ከብዙ
ቅዱሳን ጋር በሰማይ ትገኛለች ። አጠገባችን ከምሥራቅ አገር ፣ ወይም
ከደቡብ የዓለማችን ክፍል የመጣች መንፈስ ቆማለች ።
እኛ ባናይም ብቻችንን ጸሎት አቅርበን አናውቅም ። እግዚአብሔር ጸሎትን
የሚሰማው በእውነተኛ ልብ ፣ ዋጋ ከፋይነቱን በማመን ፣ በኅብረት ሲቀርብ
ነው ። ጸሎትን በሚመለከት አፋዊ ማነብነብ የሆነበት፣ ልባችን ግን
የሌለበት ልመና አለ ።
ሁለተኛው ከሰው የውዳሴ ከንቱ ዋጋ ለመቀበል ፣ ጸሎተኛ ነው ለመባል
የሚደርስ አለ ። ሦስተኛው ሰዎችን በመፍራት የሚደረግ የይሉኝታ ጾምና
ጾሎት አለ ። በአገራችን አንዱ የአንዱ የጾም ፖሊስ ስለሆነ ምን ይሉኛል
ብሎ የሚጾም ብዙ ሰው አለ ።
የጾም ዋጋ ከፋይ ግን እግዚአብሔር ነው ። አምልኮ ከፈሪሀ እግዚአብሔር ወደ
ሰው መፍራት ከወረደ ከንቱ ልፋት ይሆናል ። ይሉኝታ አምልኮን የመበጥበጥ
አቅሙ ከፍተኛ ነው ። ሰማይን እያየን ምድር እንድንቀር የሚያደርገን
በመጠባበቅ ላይ የተመሠረተ አምልኮ ነው ።
በዛሬ ዘመን ሰዎችን ለማብሸቅ የሚደረሱ መዝሙራት አሉ ። ለውድድር ፣ የእኔ
ይበልጣል ለማለትም በእግዚአብሔር ስም የሚቀርቡ አምልኮዎች አሉ ።
ደመወዛቸውን ታሳቢ አድርገው የሚቀድሱና የሚያስቀድሱ ፣ መቅደሱን እንደ
ቢሮ የሚቆጥሩም አሉ ።
አድናቂዎቻቸውን ለማስደሰት መቅደስ ውስጥ በማኅበራዊ ሚዲያ እያስተላለፉ
የሚቀድሱ ፣ ኔትወርኩ ሲቋረጥ ሰው አላየኝም ብለው የሚረበሹ ካህናት
እያፈራን ነው ። ትላንት ድምፅ ማጉያው የነጠቀንን ተመስጦ አሁን ደግሞ
የማኅበራዊ ሚዲያው ሱስ ጨምሮ ወስዶብናል ።
እግዚአብሔርን እያየ የሚዘምር የሚያመልክ እየጠፋ ነው ። ድካሙ አለ ፣
የሥላሴ በረከት ግን የለም ። እግዚአብሔርን ብንፈልገው ይገኝልን ነበረ ፣
የምንፈልገው ሰውን ስለሆነ የሰማይ በረከት አልተገኘም ።
ቤተ ክርስቲያንና በዓላት ፎቶ መነሻ ከሆኑ ሰንብተዋል ። በዓላቱ በዩኔስኮ
መመዝገቡ የሚደንቀው መንፈሳዊ አባት እያተረፍን ነው ። ለቱሪስት መስሕብ
ተብሎ የሚደረግ ምንም ዓይነት መንፈሳዊ በዓል የለንም ።
በዓል ማለት እግዚአብሔርን በቤታችንና በአገራችን ላይ መጋበዝ ማለት ነው ።
የበዓሉ እንግዳ እግዚአብሔር ነው ። በበዓላት ቀን የሚጎበኙን ሳይሆን
አምነው የሚጠመቁ ካፈራን ለእንግዳው እግዚአብሔር ልጆችን እናበዛለት ነበር ።
አምልኮቱና በዓላቱ ይሉኝታ ላይ ስለ ታሰሩ ፣ የልብስ ውድድር ፣ የግሪክ
ቆብ ፣ የኢየሩሳሌም ካባ የምንባባልበት ስለሆነ እግዚአብሔር አልተቀበለውም ።
ይሉኝታ ግዛቱን እያሰፋ ሲመጣ ባለጠጋ የሆነች አገር ሳይሆን የምትመስል አገር
እየፈጠርን እንመጣለን ። በአገራችን በብዙ አካባቢዎች ግጭቶች አሉ ። አንድ
የውጭ ዜጋ ቢሄድ የሚነካው ማንም የለም ። ኢትዮጵያዊ ግን በገዛ መልኩ
በገዛ ወንድሙ ሊጎዳ ይችላል ።
ግብዝነታችን ባዕድን የሚያከብር ፣ ራሱን የሚንቅ አድርጎናል ። እንግዳ ተቀባይ
ነን ፣ ራሳችንን ግን ገና አልተቀበልንም ። እንግዶቻችንን በብዙ ዋጋ
እንቀበላለን ፣ ድሆቻችን እንዳይታዩብን እንሰውራለን ። ውጤቱን ስናየው
ከሚሰጡን የምንሰጣቸው ይበዛል ።
“የስሙኒ ዶሮ የብር ካምሳ ገመድ ይዛ ጠፋች” ይባላል ። ይሉኝታዎቻችን በጣም
ስጉ አድርገውናል ። ዝግጅቶቻችን ከመጠን ያለፉና ራሳችንን
የምናስጨንቅባቸው ናቸው ። ይሉኝታ አባወራውን ትቶ እንግዳውን ወደ ማክበር ፣
የቤቱን ሰው ጥሎ የውጭውን ለማጥገብ ይሰደናል ።
እዚህ ያለው ሙስሊም ስለ ፍልስጤም ፣ እዚህ ያለው ክርስቲያን ስለ እስራኤል
አለሁ ይላል ። ፍልስጤምና እስራኤል ጠባቸው የመሬት እንጂ የሃይማኖት
አለመሆኑን የሚገነዘብ ጥቂት ነው ። የራሳችን ስንት ችግር እያለብን
ተንጠራርተን እናጨበጭባለን ።
ቅድሚያ ለራሳችን አገርና ወገን መስጠት አለብን ። በዓለም ላይ ስመ ጥር የሆኑ
አገራት ለዜጎቻቸው ቅድሚያና ክብር የሰጡ ናቸው ። ራሳችንን ከናቅን
የሚያከብረን የለም ። ሃይማኖት ለዋጮችን ሥራቸውን እንጠየፋለን ።
በሃይማኖቱ የማይጸና ሰው በምድር ላይ የረከሰ ሰው ነው ።
ይህ ትውልድ ምግብ ቤት እንደ መቀያየር ሃይማኖቱን ሲለውጥ ቅር የሚለው
አይደለም ። ታዲያ አንድ ወጣት ሲነግረኝ የሄደባቸው ሃይማኖቶችና
አስተማሪዎች ቅር እንዳይላቸው እስካሁን ሦስት ጊዜ ተጠምቄአለሁ ብሎኛል ።
በጣም ያስፈራል ።
ሦስት ጊዜ የሚያስጠምቅ ይሉኝታ ፣ የሄደባቸው ስለ ጎተጎቱት ነው ። ይሉኝታ
ሃይማኖትን እንድናፈርስ እያደረገን ነው ። አልኮል መጠጥ መጠጣት ውድቀታችን
እንጂ የእኛ መገለጫም አይደለም ። ሌላ ይሉኛል ብሎ የሚጠጣ ሰው አለ ።
ኦርቶዶክሳዊነት በነቢያትና በሐዋርያት መንገድ መሄድ ነው ። መገለጫውም ቃለ
እግዚአብሔርን በኑሮአችን ተዳሳሽ ማድረግ ነው ። ጾምን በኃጢአት የሚቀበል ፣
ጾሙንም በዓመፃ የሚፈስክ በእግዚአብሔር ስም የሚበድል ነውና ለራሱና ለአገር
ትልቅ መከራ ያመጣል ።
እግዚአብሔር ከይሉኝታ ሊፈታን ፣ ለእውነታ ሊያኖረን ይቻለዋል ።
“እግዚአብሔር የታሰሩትን ይፈታል ።” (መዝ. 145 ፡ 7) ።
ይቀጥላል…
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 18 ቀን 2017 ዓ.ም